የ«ዊንዶ 7»ተጠቃሚዎች ስጋት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 15.01.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የ«ዊንዶ 7»ተጠቃሚዎች ስጋት

የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ ምርት የሆነዉ «ዊንዶ 7» የተባለዉ የኮምፒዩተር ፕሮግራም ከኩባንያዉ ይደረግለት የነበረዉ የሳይበር ደህንነት ድጋፍ ዛሬ ማለትም በጎርጎሮሳዉያኑ ጥር 15ቀን 2020 ቀነ ገደቡ ያበቃል። በመሆኑም ከዛሬዉ ቀን በኋላ «ዊንዶ 7»ን መጠቀም የተጠቃሚዎችን መረጃ ለጥቃት ያጋልጣል ሲል ኩባንያዉ አስጠንቅቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:27

የ«ዊንዶ 7»ተጠቃሚዎች ስጋት

በመሆኑም ከዛሬዉ ቀን በኋላ «ዊንዶ 7»ን መጠቀም የተጠቃሚዎችን መረጃ ለጥቃት ያጋልጣል ሲል ኩባንያዉ አስጠንቅቋል።
ከማይክሮሶፍት ኩባንያ ምርቶች ዉስጥ አንዱ የሆነዉ «ዊንዶ 7» የተመረተዉ ከ10 ዓመት በፊት በጎርጎሮሳዉያኑ ሀምሌ 22 ቀን 2009 ዓ/ም ሲሆን ጥቅም ላይ የዋለዉ ግን ከ10 ወራት በኋላ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ/ም ነበር።ይህም ቀደም ሲል « ዊንዶ ቪስታ» የተባለዉ የኮምፒዩተር መከወኛ ስርዓት ከተመረተና ጥቅም ላይ ከዋለ ከ3 ዓመት ባነሰ ጊዜ ዉስጥ ማለት ነዉ።ኩባንያዉ በተመሳሳይ ጊዜም ሰርቨር 2008 /R2 የተባለዉን የ«ዊንዶዉ 7» ተጓዳኝ ሰርቨር አገልግሎት ላይ አዉሏል። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት «ዊንዶ 7» ግለሰባዊ የኮምፒዩተር አጠቃቀም ስርዓት ሲሆን «ዊንዶ NT» የተባለዉ የክወና ስርዓት አካል ነዉ።
በወቅቱ ማይክሮሶፍት  በዚህ ምርት ላይ የሚያደርገዉ የሳይበር ጥበቃ ጥር 13 ቀን 2015 ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ዘግይቶ ግን እስከ ዛሬዋ ቀን ማለትም በጎርጎሮሳዊዉ ጥር 15 ቀን 2020 ድረስ እንዲቀጥል ተደርጓል። ከዛሬ ጀምሮ ግን የዚህ ምርት የሳይበር ጥበቃ ድጋፍ መቋረጡን ኩባንያዉ አስታዉቋል። DW ያነጋገራቸዉ በገንዘብ ሚንስትር የመንግስት መረጃ ስርዓት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ከድር ዓሊ እንደሚሉት ኩባንያዉ ከዚህ ቀደም «ዊንዶ ኤክስፒ»ን፣«ዊንዶ ቪስታ»ን በመሳሰሉ ምርቶቹ ላይ ተመሳሳይ ድጋፍ ማቆሙን ገልፀዉ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የ«ዊንዶ 7»ን ቴክኒካዊ ድጋፍ ማቋረጡን አመልክተዋል።ለመሆኑ ቴክኒካዊ ድጋፍ ተቋረጠ ማለት ምን ማለት ነዉ? 


«ያማለት ምን ማለት ነዉ።«ዊንዶ-7»ድጋፌን አቆምኩኝ ብሎ ሲናገር» ካሉ በኋላ ማይክሮሶፍት ለ«ዊንዶ-7» በየጊዜዉ  የሚሰራቸዉን የክፍተት መሙያዎችና ማዘመኛዎችን ያቆማል ማለት ነዉ ብለዋል። ቀጥለዉም «በዊንዶ 7» ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎችን አያደርጉም ማለት ነዉ።ይህንን ድጋፍ ነዉ በዋናነት የሚያቆመዉ።ስለዚህ ይህንን ድጋፍ አቆሙ ማለት ከዚህ በፊት ዊንዶ 7 ይጠቀሙ የነበሩ ተጠቃሚዎች ከማይክሮሶፍት በቂ ድጋፍ አያገኙም።» ነዉ ያሉት።  በዚህ የተነሳ «ዊንዶ 7 » በቀላሉ ለጥቃት የሚዳረግበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነዉ በማለት ገልፀዋል።
«ዊንዶ 7 » ቀድሞ ጥቅም ላይ ከዋለዉ ዊንዶ ቪስታ በአጠቃቀም ዘዴዉ ተሻሽሎ የተመረተና ለአሰራርና ለአጠቃቀም ምቹ ስለነበር በወቅቱ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈ ሲሆን ፤ይህ በአሰራር ስርዓቱ ላይ የተደረገዉ መሻሻል  ለማይክሮሶፍት ኩባንያ በወቅቱ እንደ ትልቅ ስኬት ተቆጥሮ ነበር። ከዚህ የተነሳ ምርቱ በይፋ ለአገልግሎት ከመለቀቁ በፊት አማዞንን ለመሳሰሉ 7 ትልልቅ ኩባንያዎች በወቅቱ የቅድመ ሽያጭ ትዕዛዝ አከናዎኖ ነበር።በ6 ወር ጊዜ ዉስጥም ከመቶ ሚሊዮን በላይ ቅጅዎችን በዓለም ዙሪያ ለመሸጥ በቅቷል።ይህ ቁጥር ቆይቶም በ2012 ዓ/ም ወደ 630 ሚሊዮን ያደገ ሲሆን እስከ ጥቅምት 2019 ዓ/ም ድረስ ከኮምፒዩተር ተጠቃሚዎች ዉስጥ 27 ነጥብ 98 በመቶ «ዊንዶ 7»ን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገሮችም ይህንን ምርት የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ቀላል አእንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።ባለሙያዉ አቶ ከድር ዓሊ እንደነገሩን በኢትዮጵያም ሌሎች ምርቶችን የሚጠቀሙ የመኖራቸዉን ያህል «ዊንዶ 7» ን የሚጠቀሙ ሰዎችም በርካቶች ናቸዉ። 


ስለሆነም «ለዊንዶ 7» የሚደረገዉ ቴክኒካዊ ድጋፍ ብሎም ሶፍትዌሩን የማደስ ተግባራት ከዛሬ ጀምሮ በመቋረጣቸው በኢትዮጵያ ይህንን ምርት የሚጠቀሙ ግለሰቦችም ይሁን ተቋማት በመረጃዎቻቸዉና በሚጠቀሙት ኮምፒዩተር ስርዓት ላይ እክል እንዳይገጥማቸዉ በኩባንያዉ የደህንነት ማዘመኛዎች፣የክፍተት መሙያዎችና ሌሎች ዘመናዊ ድጋፎች ወደሚደረጉለት «ዊንዶ 10» ወደ ተባለዉ ዘመናዊ የኮምቲዩተር አጠቃቀም ስርዓት ቢሸጋገሩ የተሻለ አማራጭ መሆኑን  አቶ ከድር  ያስረዳሉ። 
ነገር ግን ያ ሳይሆን ቀርቶ ተጠቃሚዎች ቀደም ሲል ይጠቀሙበት የነበረዉን «ዊንዶ7» መጠቀም ቢቀጥሉ በሁለት መንገድ ችግሮች ሊገጥሟቸዉ  እንደሚችሉ  ባለሙያዉ አብራርተዋል።

«በሁለት ነገር ላይ ነዉ የምናየዉ። አንደኛዉ «ኩሪቲ ኮንሴፕት ነዉ።»ካሉ በኃላ ሁለተኛዉ ኩባንያዎች አዳዲስ መተግበሪያዎችን«ዊንዶ 10»ን መሳሰሉ አዲስና ዘመናዊ የኮምፒተር መከወኛ ስርዓቶች ብቻ ስለሚያመርቱ  «ዊንዶ- 7 »ላይ የምንጭናቸዉ መተግበሪያዎች  /Applications/ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል አመልክተዋል።

Microsoft Betriebssystem Windows Vista Computer (AP)


ያማለት ግን የ«ዊንዶ 7»ተጠቃሚዎች በአንድ ጀምበር የተጠቀሰዉ ችግር ያጋጥማቸዋል ወይንም ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የቆየዉ ግልጋሎት በአንዴ ይቆማል ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል። ማይክሮሶፍት ኩባንያም ቢሆን ከአሁን ቀደም የድጋፍ ጊዚያቸዉ ባለፈባቸዉ እንደ «ዊንዶ ቪስታ»ና «ዊንዶ ኤክስፒ» በመሳሰሉ ምርቶቹ ላይ በቂ ባይሆንም የተወሰነ ድጋፍ ማድረጉን አስታዉሰዋል።
ያም ሆኖ ግን ዊንዶም ሆነ ሌሎች የኮምፒዩተር አጠቃቀም  ምርቶችን በተለምዶ ከበይነ መረቦች ላይ በነፃ  ከመጫን ይልቅ ህጋዊ ምርቶችን ገዝቶ መጠቀም መረጃዎችን ከጥቃት ለመጠበቅ  ዋናዉ መፍትሄ መሆኑን የሳይበር ደህንነት ባለሙያዉ አቶ ከድር ዓሊ ለተጠቃሚዎች መክረዋል።
 የዊንዶ የክወና ስርዓት /window operating system/ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ የደህንነት ስጋቶች ሲጋለጡ የነበሩ ሲሆን፤  በጎርጎሪያኑ 2019 ብቻ ፤ 499 ለሚደርሱ  የሳይበር ጥቃቶች ተጋላጭ ሆነዋል።ከነዚህም መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑት ጥቃቶች እጅግ አደገኞች እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።ለጥቃቶቹ በወቅቱ ከማይክሮሶፍት ኩባንያ የክፍተት መሙያ  ሲቀርብ የነበረ ሲሆን፤98 በመቶ የሚሆነዉ ጥቃትም በዛሬዉ ዕለት የቴክኒክ ድጋፉ በተቋለጠዉ «ዊንዶ-7» ላይ የደረሰ ነበር። 

 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

 

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic