የዉቅያኖሶች መበከል | ጤና እና አካባቢ | DW | 10.06.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የዉቅያኖሶች መበከል

ግሎባል ኦሽን ኮሚሽን የተሰኘ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባለፈዉ ሳምንት ያወጣዉ ጥናት ከከባቢ አየር 500 ሚሊዮን ቶን ካርቦን በዉቅያኖስ እንደሚመጠጥ አመለከተ።

ምንም እንኳን የምድራችን ዉሃማ አካላት እንዲህ ያለዉን የተፈጥሮ ሚዛናዊነት ለመጠበቅ የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ በተፈጥሮ መንገድ ቢያደርጉም በሠዉ ሠራሽ ችግር በቆሻሻ ተበክለዉ እንኳን የዉጭዉን ዓለም ቀርቶ በዉስጣቸዉ የተሸከሟቸዉን ፍጥረታትም መታደግ ወደማይችሉበት እያዘገሙ እንደሚገኙም ጥናቱ ጠቁሟል።

ከወራት በፊት ከሁለት መቶ በላይ ተሳፋሪዎችን ጭኖ የተነሳዉ የማሌዢያ አዉሮፕላን የደረሰበት ሳይታወቅ፤ የተሳፋሪዎቹ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመዶቻቸዉም ምን እንደተከሰተ በዉል ሳይረዱ ቆይተዋል። ወደፊትም ምን ያህል ጊዜ ሊቆዩ እንደሚችሉ በዉል የሚታወቅ ነገር የለም። የዉቅያኖሶች በቆሻሻ መሞላትን አበክረዉ የሚያስገነዝቡ ወገኖች ምንም እንኳን አዉሮፕላኑ ደቡባዊ ህንድ ዉቅያኖስ ላይ ተከስክሷል የሚለዉ ጥርጣሬ የታመነ ቢመስልም ስብርባሪዉ ሊገኝ ያልቻለዉ ዉሃዉ ዉስጥ በተከማቹ ሌሎች ቅራቅንቦዎች በመሞላቱ ነዉ እያሉ ነዉ። የዚህን አዉሮፕላን ስብርባሪ ለማግኘት የተደረገዉንም ሙከራ ሌሎች ስብርባሪ አካላት እያደናቀፉ፤ አንዳንዴም ተገኘ የተባለዉ ጉማጅ የሌላ ነገር መሆኑ መደጋገሙ ፍለጋዉንም ሆነ ከአሰሳዉ አንዳች መረጃ ጠብ ይላል በሚል ተስፋ የሚጠብቁትን የሰለባዎቹን ቤተሰቦችና ፈላጊዎቹን እንዳሳቀቀም ታይቷል።

ይህ እንቅፋትና አጋጣሚም ዉቅያኖሶች ምን ያህል በቆሻሻ ጥርቅም እንደተሞሉ ብሎም ለብክለት እንደተዳረጉ ማመላከትም አስችሏል። ችግሩ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ዶክተር ዌንዲ ዋትሰን ራይት ፓሪስ የሚገኘዉ ስለዉቅያኖስ የሚያጠና፣ የሚከታተልና መረጃዎችን የሚሰበስብና የሚያከማች እንዲሁም ዉቅያኖስ ላይ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለምሳሌ ሱናሚን አስቀድሞ የሚያስጠነቅቀዉ የተመ የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት የባህር ጥናት ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ እንዲህ ያስረዳሉ፤

«ችግሩ በጣም ከፍተኛ ነዉ፤ እንደዉ አንዳንድ ተንታኞች እንደሚገምቱት በቁጥሮች መጠንና አቀራረብ የሌሎችን ጆሮ ለመሳብ የምንናገረዉ ነገር አይደለም። በእርግጥ በፓስፊክ ዉስጥ የተከመረ ቆሻሻ የሚል አገላለል መጠቀሙ በመጠኑም ቢሆን እዉነታዉ ሌላ ትርጓሜ እንዲሰጥ ስለሚያደርግ ሊያደናግር ይችላል። ምክንያቱም ከአየርም ሆነ በሳተላይት ፎቶግራፍ ሊነሳ የሚችል በቆሻሻዉ ብዛት የተፈጠ ደሴት የለምና። የሚያሳዝነዉ ግን ሃቁ እጅግም የሚስብ አይደለም። ያሳዝናል የምለዉ በዉቅያኖሱ የላይኛዉ አካል ላይ በመንሳፈፍ ዉሃዉን ከሸፈኑት የፕላስቲክና ጎማ ዉዳቂዎች ይልቅ የቆሻሻ ደሴቱ ቢፈጠር ይሻላል ማለቴ አይደልም። ምናልባትም እነዚህ የማይሟሙና ተንሳፋፊ ቆሻሻዎችን ከባህሩ ላይ ማፅዳት ከተፈለገ ለፅዳት ይቀሉ ይሆናል። እዉነቱ ግን እነዚህ ተንሳፋፊ ዉድቅዳቂዎች በማዕበልና ወጀቡ አማካኝነት ያለማቋረጥ ይንቀሳቀሳሉ፤ በዚህ ምክንያትም በየስፍራዉ ይበታተኑና ሰፊዉን የዉሃ አካል ይይዛሉ።»

እሳቸዉ እንደሚሉት እነዚህ ቆሻሻዎች በተከማቹበት አካባቢ በዉሃዉ ላይ መንሳፈፍም ሆነ መንቀሳቀስ ይቻላል፤ አንዳንዴም ትንሽ ሌላ ግዜም ምንም ተንሳፋፊም ሆነ ስብርባሪ ነገር ላይታይ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ መጠናቸዉ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅም አስቸጋሪ ነዉ ይላሉ የሚንቀሳቀሱበት የዉሃ ድንበርና የንፋስ ሁኔታዉ አዳጋች ያደርገዋልና። በዚህ ምክንያትም ይህን ያህል ነዉ መጠናቸዉ ማለት ቢያዳግትም በደፈናዉ በሰዎች ምክንያት ዉቅያኖስን የሞሉት ዉዳቂዎች እጅግ ብዙ በመሆናቸዉ መልካም ዜና ሊሆን እንደማይችል ያመለክታሉ። ለመሆኑ ዉቅያኖሶች ዉስጥ በብዛት የሚገኘዉ ቆሻሻ የትኛዉ ይሆን? ዶክተር ራይት መልስ አላቸዉ፤

«በአሁኑ ጊዜ በሰፊዉ የሚነገርለት የዉቅያኖስ ቆሻሻ ፕላስቲክ ነዉ። በበርካታ አካባቢዎች በዉሃ ዳርቻ ሲኬድ የሚገኘዉ ይኸዉ ነዉ። ኅብረተሰቡ የፕላስቲክ ዉጤቶችን በተለያየ መልኩና በብዛት መጠቀሙንም በየባህሩ ዳር የወደቀዉን መጠን መመልከቱ በቂ ነዉ። ከተለመደዉ የቤት ዉስጥ መጠቀሚያ እስከ ኢንዱስትሪ ምርት፣ እንዲሁም የጠፋ ወይም የተጣለ የዓሣ ማስገሪያ አካል፤ እነዚህ ሁሉ ወደዉቅያኖስ ስለሚጣሉ የዉሃዉን አካል በማበላሸት በቅርቡም ሆነ ቆየት ብሎ የሰዉን ልጅ ለሚጎዱ ችግሮች የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ እያደረጉ ነዉ። »

ዶክተር ራይት አያይዘዉ ያመለከቱት የፕላስቲክን በዉሃ ያለመሟሟት ወይም በአፈርም ቢሆን ያለመበላት ባህሪ ሊያስከትል የሚችለዉን መዘዝ ነዉ። አንዳንድ የፕላስቲክ ዓይነቶች በዉሃዉ ወደሌላ ነገር የሚለወጡ ቢሆንም እንኳ ያ እራሱን የቻለና ረዢም ጊዜ የሚወስድ የመሰባበር መንገድ እንዲሁም የተለየ ኬሚካላዊ ሂደት የሚጠይቁ መሆናቸዉንም ጠቁመዋል። እንዲህ ባሉ ቆሻሻዎች የተሞሉት የዓለማችን የዉሃ አካላት በየትኛዉ አካባቢ መገኘታቸዉ ሳይሆን ሊያሳስብ የሚገባዉ የሚያስከትሉት ተፅዕኖ መሆኑንም ያመለክታሉ።

«የሚያስከትሉት ተፅዕኖ ከፍተኛና አደገኛ ነዉ። የተጣሉ ዓሣ ማጥመጃ መረቦች፣ የፕላስቲክ ወጥመዶች፣ እንዲሁም ሌሎች ስብርባሪዎች ጥንካሬ የሌላቸዉ በዉሃ ዉስጥ የሚገኙ ነገሮችን ይጎዳሉ፤ የባህር ዉስጥ እንሳስትንም አንቀዉ ወይም ተብትበዉ ለጉዳት ይዳርጋሉ። ጥናቶች እንዳሳዩት አሶችም ሆኑ ሌሎች የባህር እንስሳት ፕላስቲክ ይበላሉ፣ በዚህ ምክንያትም የዉስጥ አካላቸዉ ይጎዳል፣ የምግብ መፍጫ ስርዓታቸዉ ይዛባል፣ መመገብ ሳይችሉ ቀርተዉም በርሃብና ምግብ በማጣት ይሰቃያሉ። በተለይም የህክምና እንዲሁም የግል ንፅህና መጠበቂያ የሆኑ ፕላስቲክ ነገሮች በዉስጣቸዉ ባለዉ አደገኛ ባክቴሪያ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ የባህር ዉስጥ ፍጥረታትን ለጉዳት ይዳርጋሉ።»

እነዚህ ዉቅያኖስ ዉስጥ የሚጣሉ የተለያዩ ነገሮች ስብርባሪዎችም ሆኑ ፕላስቲኮች ቀደም ሲል እንደተጠቆመዉ ደብዛዉ የጠፋዉ የማሌዢያዉ MH370 አዉሮፕላን እንዳይገኝ እክል ሆነዋል የሚለዉንስ መላ ምት ዶክተር ራይት ይስማሙበት ይሆን?

«በከፍተኛ መጠን ዉቅያኖስ ዉስጥ የተከማቸዉ ቆሻሻ በእርግጥም ሳተላይቶች ግዙፍ ነገር በተመለከቱ ቁጥር አደገኛና የሃሰት ተስፋዎች እንዲሰሙ አድርጓል፤ እነዚህ ነገሮች ግን ከእሱ ጋ የማይገናኙ ስብርባሪዎች ናቸዉ፤ የዓሣ ማስገሪያ መሳሪያ እና ሌሎች ተንሳፋፊ ነገሮች እየሆኑ ማለት ነዉ። ከዚህ አሰቃቂ አጋጣሚ የታየዉ አዎንታዊ ነገር፣ ምናልባትም ተስፋ የምናደርገዉ ለመላዉ ኅብረተሰብ፣ ለፕረስና ለዉይይት አደራጆች በየቀኑ ዉቅያኖስ ዉስጥ የሚጣለዉ መጠኑ ከፍተኛ የሆነዉ ቆሻሻ በድጋሚ ትኩረት እንዲያገኝ ያስችላል የሚለዉ ነዉ።»

የችግሩ አስከፊነት ከታወቀና እንደተባለዉም አሳሳቢነቱ እየባሰ ከሄደ መፍትሄ መፈለጉ ግድ ነዉ እና ባለሙያዋን መፍትሄ ያሉትንም እንዲህ ይተነትናሉ፤

«ለዚህ ጥያቄ ምላሹ ማንም እንደሚገምተዉ ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ሁሉንም ማፅዳት ስለሚለዉ እንኳ መናገር አንችልምና። የዉቅያኖሶችን የላይ አካል ለማፅዳት ወጪዉ ቀላል አይደለም። ሌላዉ ቀርቶ የሚንሳፈፉትን እንኳ ማፅዳቱ ፈታኝና ለዚህም አስፈላጊዉ ገንዘብ ከፍተኛ ነዉ። የሚያዋጣዉና ብቸኛዉ መፍትሄ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችና ዉዳቂዎችን ማስወገጃዉን ስልት በጥንቃቄ መንደፍ ነዉ። ይህም ማንኛዉም ፕላስቲክም ሆነ አደገኛ ቁሳቁስ በተገቢዉ የቆሻሻ ማስወገጃ መንገድ መሬት ላይ እንዲወገድና ከባህርም እንዲርቅ ማድረግ። ምናልባት ይሄ ለመንግስታት በአካባቢና በብሄራዊ ደረጃ ትልቅ ኃላፊነት ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ዜጋ በየግሉ የየራሱን ኃላፊነት በተገቢዉ መንገድ ቆሻሻዎችን በማስወገድ በየአካባቢዉ በማፅዳት ተግባር ሊሳተፍ ይችላል። የሚጣሉ ቆሻሻዎችን መቀነስ እንዲሁም ሲጣሉም አወጋገዳቸዉን በጥንቃቄ ማከናወን ማለት ነዉ። በዚህም ሶስቱን Rዎች ማስታወስ ይጠቅማል፣ እነሱም መቀነስ፣ ደግሞ ጥቅም ላይ ማዋል እና ወደሌላ ጥቅም ሰጪ ነገር እንዲለወጥ ማድረግ ናቸዉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic