የዉሃ ክምችት በኬንያ | ጤና እና አካባቢ | DW | 17.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የዉሃ ክምችት በኬንያ

የተመድ ከፍተኛ የዉሃ እጥረት እንዳለባቸዉ ከሚገልጻቸዉ ሃገራት አንዷ ኬንያ ናት። ካለፈዉ መስከረም ወር አንስቶ ግን በድርቀቱ በሚታወቀዉ ቱርካና ግዛቷ የኬንያን ይህን መሰል ታሪክ የሚቀይር አጋጣሚ ተከስቷል።

የዉሃ እጥረትና ለከብቶች የሚጠጣ ፍለጋዉ የሰሜን ኬንያን ኗሪ ጎሳዎች ሲያጋጭ ኖሯል፤ ዛሬም ያልሰከነ ችግር ነዉ። እንደየተመ ተቋም የሆነዉ የመንግስታቱ የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ UNESCO መዘርዝር ከሆነም አንድ ሶስተኛ የሚሆነዉ የኬንያ ህዝብ ንፁህ የመጠጥ ዉሃ የማግኘት አድል አልተመቻቸለትም። በዚህ ምክንያትም ዉሃ ኬንያ ዉስጥ ዉድ የተፈጥሮ ሃብት ነዉ። ኬንያ በአበባም ሆነ በተለያዩ የእርሻ ዉጤት ምርቶች የምታደርገዉ ተሳትፎ ባይገታም የዉሃ እጥረት እንደታሰበዉ በምርቷ የምትመኘዉን ብልፅግና እንድትጨብጠዉ አላደረጋትም። አሁን ግን የዉሃ ክምችት ያዉም ከከርሠ ምድር እንዳላት ከተሰማ የወራት እድሜ ተቆጥሯል። በድርቀቱ በሚታወቀዉ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ቱርካና ግዛት የተገኘዉ ከሁለት መቶ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የሆነዉ የዉሃ ክምችትም ለግዛቱ ብቻ ሳይሆን ለመላዋ ኬንያ የብልፅግና በር እንደሚከፍት ተስፋ ተጥሎበታል።

የኬንያዉ ቱርካና ግዛት አፍሪቃ ዉስጥ ከሚገኙ እጅግ ደረቅና በረሃማ ከሚባሉ አካባቢዎች አንዱ ነዉ። በUNESCO እበኢትዮጵያ፤ በኬንያና ሶማሊያ መንግስታት ትብብር አማካኝነት ካለፈዉ የጎርጎሪዮሳዊ ዓመት አንስቶ በጋራ የመሬት ዉስጥ ዉሃ ሃብት ክምችት ፍለጋ ተጀመረ። ጥረቱ የሚታገዘዉ በራዳርና በቴክኒዎሎጂ በመጠቁ ሳተላይቶች አማክኝነት ሲሆን ዋና ዓላማዉ በአፍሪቃዉ ቀንድ ድርቅ የሚያስከትለዉን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል የከርሰ ምድር ዉሃ ክምችት መኖሩን ፈልጎ ማየት ነበት።

ፍለጋዉ ተሳካ። ዉጤቱም በዓለማችን በድርቀት በታወቀዉ ሰሜናዊ የኬንያ ግዛት ገጸ ምድር ሥር ነፍስ አድን የሆነዉ ኩል የመሰለ ዉሃ መተኛቱን አመላከተ። በቱርካና በረሃ የተካሄደዉ የሙከራ ቁፋሮዉም ስኬታማ መሆኑ ነዉ የተገለጸዉ። በዚህ መሠረትም 240 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዉሃ በተጠቀሰዉ ስፍራ መገኘቱ ተረጋግጧል። ግኝቱም ለኬንያ መንግስት እጅግ ከፍተኛ ደስታና ተስፋን ነዉ ያመጣዉ። ዉሃዉ ለሀገሪቱ መፃኤ እድል ተጨማሪ የብልፅግና በሮችን እንደሚከፍት የሚናገሩት የኬንያ ምክር ቤት አባልና የሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ ጁዲ ዋኩንጉ፤ ተስፋዉ ለቱርካና አካባቢ ኗሪዎች ብቻ ሳይሆን ለመላ ሀገሪቱ ታላቅ ገጸበረከት መሆኑን ነዉ ያመለከቱት።

በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ አርሶ አደሮችን የሚደግፈዉ ዓለም ዓቀፍ የሆነዉ GRAIN የተሰኘዉ ድርጅት ዳይሬክተር ሄንክ ሆበሊን በበኩላቸዉ ይህ እዉነት ሊሆን እንደሚችል በማመልከት፤ የአሁኑ ደስታና ተስፋ እዉን ሊሆን የሚችለዉ ግን የተገኘዉ የዉሃ ሃብት በብልሃት የሚጠቀምበት ከኖረ ብቻ እንደሚሆን ይገልጻሉ፤

«ከ30 ዓመታት በፊት ይህን መሰል ግልፅ ተሞክሮ ስዑድ አረቢያ ዉስጥ አይተናል። ማለትም በ1980ዎቹ ሳዉዲ ከፍተኛ መጠን ያለዉ ዉሃ ከከርሠ ምድር አግልኝታ ነበር። እናም በአዲስ ማሳ ላይ በመስኖ ስንዴ ሊያመርቱ ዉሃዉን ከምድር እየሳቡ በረሃዉ ላይ ያወጡት ጀመር። ከዚያም እጅግም ሳይሰነብት በሁለት አስርት ዓመታት ዉስጥ የዉሃዉ ክምችት ተሟጦ አለቀ። ስለዚህ ስዑድ አረቢያ አሁን ወደቀድሞዉ ይዞታዋ ተመልሳ ለህዝቧ የሚሆነዉን የምግብ እህል ለማምረት ወደዓለም ገበያና ወደአፍሪቃ ፊቷን አዙራለች።»

ጤናን ከገንዘብ ዉሃን ከቀለብ የሚቆጥረዉ የለም እንዲሉ የባለሙያዉ ከወዲሁ የቀረበ ማሳሰቢያም ሆነ ማስጠንቀቂያ ኬንያ ከበረሃማዉ ግዛቷ የተገኘዉን የዉሃ ክምችት እንደሳዉዲዎች በነፃ ተገኘ ብላ ሳታባክን፤ በብልህነት እንድትጠቀምበት ያስገነዝባል። አሁን ሳዉዲ ዉስጥ ለመጠጥ ከሚሆነዉ ዉሃ 50 መቶዉ የባህር ዉሃን ጨዉነት በማጣራት የሚገኝ ነዉ። ለንፅህና መጠበቂያና ለጽዳት የሚሆነዉ ዉሃም እንዲሁ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ እየተጣራ ዳግም ለአገልግሎት እንዲዉል የሚደረግ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የGRAIN ዳይሬክተር እንደሚሉትም ሳዉዲ ያደረገችዉ ዓይነት የከርሰ ምድር ዉሃ አጠቃቀም ብክነት ኬንያ ላይ መደገም አይኖርበትም። ከመሬት ሥር የሚገኘዉ የዉሃ ሐይቅ ራሱን እያደሰና ከሙላት ሳይጎል እንዲሰነብት ከተፈለገም የአካባቢዉ ማኅበረሰብ በየፊናዉ የየግሉን የዉሃ ማዉጣት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ማስተማርና ዉሃዉን በቁጠባ መጠቀም አማራጭ እንደሌለዉም ያስገነዝባሉ። በሌላ በኩል ግን ባለሙያዎችን ይበልጥ ያሳሰበዉ የኬንያ መንግስት ኢኮኖሚዉን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ካለዉ ፍላጎት የተነሳ ሊወስድ የሚችለዉ ርምጃ ነዉ። የጀርመኑ ብሮት ፊዩር ዲቬልት ማለትም «ዳቦ ለዓለም» የተሰኘዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የእርሻ ንግድና የዓሣ ማስገር ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ፍራንሲስኮ ማሪ፤ መንግስት ለዉጭ ገበያ የሚፈለጉ የግብርና ዉጤቶች ብዙ ዉሃ ሊፈጅ ይችላል የሚል ስጋት አላቸዉ። በምሳሌነትም እጅግ ብዙ ዉሃ የሚጠቀመዉን የኬንያን የአበባ እርሻና ምርት ይጠቅሳሉ።

«ከመላዉ አፍሪቃ በአነስተኛ ግብርና በተለይም በአበባ እርሻ ከፍተኛ ድርሻ ያላት ኬንያ ናት። በዚያ ላይ የሀገር ዉስጥ ባለ ወረቶች ለገበያ የሚቀርቡ ብዙ ዉሃ የሚፈልጉና የሚጠቀሙ ምርቶችን፤ ባቄላ፤ አተር አደንጓሬን ጨምሮ አበቦችን ሁሉ የሚያመርቱ አሉ። ስለዚህ ከወዲሁ ከተገኘዉ የዉሃ ክምችት ማን አትራፊ ይሆናል የሚለዉን ለመገመት ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። ወደዉጭ የሚላክ ምርት የሚያቀርበዉ ዘርፍ የመንግስት ወይም የመዋዕለ ነዋይ አፍሳሾችም ቢሆን ቀዳሚ ምርጫ መሆኑ አያነጋግርም።»

ማሪ አበክረዉ የሚያሳስቡት ደግሞ የቱርካና ማኅበረሰብ ዉሃዉ ለምን ጥቅም ይዋል እንዴትስ ሥራ ይሠራበት በሚለዉ ምክክርና ዉሳኔ ላይ ድርሻ እንዲሆነዉ ነዉ።

«በቱርካና ወንዝ አካባቢ የሚገኙት ህዝቦች በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን ተመልክተዋል። ኖርዌዮች፤ ጀርመኖች እንደዉ ሁሉም እዚያ አካባቢ ነበሩ። እናም የዓሣ ማስገሩ ቢባል ግብርና ቢባል አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ዉጤታማ አልሆኑም። በዚህ ምክንያትም የአካባቢዉ ማኅበረሰብ ካለዉ ተሞክሮ ተነስቶ ለአዲስ እንቅስቃሴዎች አመቺ አይደለም፤ ማንኛዉንም ሥራ ለመሥራት እነሱን ማሳመን ወሳኝ ነዉ።»

በቱርካና አካባቢ የከርሰ ምድር ዉሃ ክምችት መገኘቱ ከታወቀ ከመስከረም ወር አንስቶ የኬንያ መንግስት እስካሁን ዉሃዉን እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚችል የወሰደዉ የመጨረሻ የሚባል ዉሳኔ የለም። የተገኘዉ የዉሃ ሃብት ግን ለመጠጥ ከሚዉለዉ በተጨማሪ ዘርፈ ለብዙ አገልግሎት ሊዉል እንደሚችል ከማሰብ ሌላ፤ መስኖም ሆነ የኢንዱስትሪ ልማት ሊታሰብ እንደሚችል ነዉ የምክር ቤት ጸሐፊ የሆኑት ጁዲ ዋኩሁንጉ ይፋ ያደረጉት። እስካሁን በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለዉ አንድ ነገር፤ ዉሃዉን ጥቅም ላይ ለማዋል በቀላሉ እንደማይቻል፤ መንግስትም በዚህ ረገድ የሚወስነዉ ዉሳኔም የሚያስከትለዉ ነገር እንደማያጣ ግልፅ መሆኑን ነዉ። የቱርካና አካባቢ ኗሪዎች ለራሳቸዉም ሆነ ለከብቶቻቸዉ ዉሃ ፍለጋ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሲጋጩ መኖራቸዉ ዛሬም ያልተለወጠ እዉነት ነዉ። እነሱ ከላይ በደረቁ መሬት ላይ ለምንጭና የዉሃ ኩሬ ሲራኮቱ ተፈጥሮ ያመቻቸችዉ የዉሃ ሃብት ክምችት ግን ከሥር ተኝቶ ስንት ዘመንና ዓመታትን በትዕግስት እንደተቀመጠ ሳይንሱ ቆየት ብሎ የሚለዉ ይኖር ይሆናል። አሁን ግን ቱርካና ላይዋ ቢደርቅም ዉስጧ ረስርሷል፤ ኗሪዎቿ ከቦታ ቦታ ተዘዋዉሮ ዉሃ ፍለጋ ቀርቶላቸዉ ከደጃቸዉ በቧምቧ ይዘዉሩት ይሆን? ቀኑን ያቅርብላቸዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic