የወጣቶቹ የጣራ ላይ እንጀራ | ባህል | DW | 03.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የወጣቶቹ የጣራ ላይ እንጀራ

የቴሌቭዥን ስርጭት ሞገድ መቀበያ መገጣጠም ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሥራ እድል እየፈጠረ ነው። ከሥራው የሚገኘው ገቢ ቋሚ ባይሆንም በትምህርታቸው ላልዘለቁ እና ሌሎች አማራጮች ለሌላቸው ወጣቶች ገቢ በማስገኘት ላይ ይገኛል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:43

የጣራ ላይ እንጀራ

ሙሉ ስሙ ፉዓድ ብሩ ሐሰን ይባላል። የ20 አመቱ ወጣት ተወልዶ ያደገው ደሴ ከተማ ነው። የፉዓድ እንጀራ ከጣራ ጣራ ያዘልለዋል። «ደሴ ከተማ ልዩ ስሙ መድሐኔዓለም የሚባል ልዩ ሰፈር አለ። ጣራው ደካማ የሆነ ቤት ላይ ወጥቼ ስሰራ ወድቄ ኮርኒሱ ላይ አረፍኩ።ኮርኒሱም ደካማ ነው ትርትር አለ።» ይላል ፉዓድ።ይህ የፉዓድ ብቻ ሳይሆን የብሩክም ትዝብት ነው። አዲስ አበባ ላይ የቴሌቭዥን ስርጭት ሞገድ መቀበያ በመገጣጠም የሚተዳደረው የ 26 ዓመት መሰላል ከድቶት ያውቃል። «ብዙ አይነት ጣራ አለ። ብዙ አይነት መሰላል አለ። ተማምነኸው ላይ ወጥተህ ይሰበራል። ወይ የጣራው ማገር ይሰበራል። ትወድቃለህ።»
ብሩክ እና ፉዓድ ራሳቸውን በተለምዶ 'ዲሽ ሰራተኛ' ብለው ይጠራሉ። ሁለቱ ወጣቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣው የአማራጭ የቴሌቭዥን ስርጭት ፍለጋ የስራ እድል ከፈጠረላቸው መካከል ይገኙበታል።
ፉዓድ የኑሮን ፈተና መጋፈጥ የጀመረው ገና በልጅነቱ ነው። ወላጅ አባቱን በሞት ከተነጠቀ ጀምሮ ቤተሰቡን ለመደጎም የሻይ ቅመም እና ኦቾሎኒ በማሸግ ለሱቆች ያከፋፍል ነበር። የአስረኛ ክፍል ፈተና ከተፈተነ በኋላ ሌሎች የሥራ አማራጮች ቢልግም አልተሳካለትም። ድንገት ዲሽ ወደ መገጣጠም እና ጥገና ሙያ ገባ።

እነ ፉዓድ እና ብሩክ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የሥርጭት ሞገዶቻቸውን ሲቀይሩ ይከታተላሉ። የሥር ጭት ሞገድ ለውጥ አሊያም የአዲስ ስርጭት መጀመር ለእነሱ ስራ ይዞ ይመጣል። ፉዓድ በፌስቡክ ማህበራዊ ድረ-ገጽ የከፈተው ኢትዮ-ዋልያ ዲሽ እና ሪሲቨር የተሰኘ ገጽ ከፍቷል። ገጹ ከአምስት ሺህ በላይ ተከታታዮች አሉት። በገጹ የሞገድ ለውጥ መረጃን ያቀብላል። አዲስ ስለተከፈቱ የቴሌቭዥን ስርጭቶች መረጃ ይሰጣል። ከዚህም በላይ ከእርሱ ራቅ ካሉ አካባቢዎች የሚቀበላቸውን የሥራ ጥያቄዎች ለመሰል ባልደረቦቹ ያስተላልፋል.።

እነ ፉዓድ ለደንበኞቻቸው የስፖርት ፤መዝናኛ እና ሐይማኖት የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን ደንበኞቻቸው እንዲከታተሉ ያመቻቻሉ። ፉዓድ ሥራው ከባድ ባይሆንም ገቢው ቋሚ እንዳልሆነ ይናገራል።
ለቴሌቭዥን ሥርጭት መቀበያ የሚያገለግሉት ቁሳቁሶች በሙሉ ከውጭ የሚገዙ ናቸው። በአንድ ወቅት የስርጭት ሞገድ መቀበያ ሳህኑን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም አልዘለቀም። ፉዓድ የስርጭት መቀበያ ቁሳቁሶቹን በራቸው ለመስራት የሞከሩ ጓደኞች አሉት። ነገር ግን ሙከራቸውን የሚያግዝ ባለማግኘታቸው እና በገበያም ተወዳዳሪ ባለመሆናቸው እርግፍ አድርገው ትተውታል።ብሩክ አሁን የሚሰራውን ስራ የማሳደግ ህልም አለው። ስራው ግን የመሸጫ ቦታ እና የመነሻ ገንዘብ ያስፈልገዋል። ይህን ማሟላት ደግሞ ቀላል አይደለም።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic