የወደቀውን የትምህርት ጥራት ማን ያንሳው ? | ኢትዮጵያ | DW | 21.11.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የወደቀውን የትምህርት ጥራት ማን ያንሳው ?

ቀደምሲል በክልሎች ሲከናወኑ የቆዩት የስምንተኛ እና የስድስተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች ከያዝነው ዓመት ጀምሮ በፌደራል ደረጃ እንደሚሰጡ የትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ ፡፡ ፈተናዎቹ ከክልል ወደ ፌደራል የተዛወሩት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በተዘረጋው የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት ነው ተብሏል፡፡

የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በፌደራል ደረጃ ይሰጣል ተባለ

 

በሀዋሳ ከተማ የተካሄደው 31ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በበርካታ ችግሮች ለተተበተበው የትምህርት ዘርፍ ይበጃሉ የተባሉ መፍትሄዎች ተንጸባርቀውበታል ፤ አዳዲስ የለውጥ እንቅስቃሴዎችም ተስተውለውበታል፡፡ የከፍተኛ ትምህር ተቋማትን ከመንግሥት እጅ በማውጣት በራስ ገዝ አስተዳደር እንዲመሩ ማድረግና የፈተና ምዘናዎች ጥራታቸውን መጠበቅና ከሥርቆት የፀዱ ማድረግ ከተጀመሩት ሥራዎች መካከል መሆናቸው በጉባዔው ላይ ተጠቅሷል፡፡ በተለይም የትምህርቱን ዘርፍ ለማሻሻል ይረዳሉ ተብለው የታመነባቸው የለውጥ ሥራዎች የአፈጻጸም ሂደታቸው በጉባኤው ተገምግሟል፡፡ 

የአንደኛና የመለስተኛ ደረጃ  ፈተናዎች   

ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚንስቴር ዴኤታ ናቸው ፡፡ሚንስትር ዴታው እንደሚሉት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በትምህርቱ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የለውጥ ትግበራ ሥርዓት ገቢራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ቀደምሲል በክልሎች ሲከናወኑ የቆዩት የስምንተኛ እና የስድስተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች ከያዝነው ዓመት ጀምሮ በፌደራል ደረጃ እንደሚሰጡ የጠቀሱት ዶክተር ፋንታ ‹‹ ይህም ተግባራዊ የሚደረገው በተዘረጋው የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት ነው ፡፡ የሚፈለገውን የትምህርት ጥራት ለማሳካት ይህ ብቻውን በቂ አይደለም ፡፡ የተቀናጀ ተግባርን እንደሚጠይቅ እናምናለን ፡፡ ለዚህም ነው  የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ እያደረግን የምንገኘው ፡፡ አምና በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የአዲሱ ስርዓት ትምህርት  ዘንድሮ ወደ ሙሉ ትግበራ ተገብቷል፡፡ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለው ሥርዓተ ትምህርት ደግሞ ዘንድሮ በሙከራ ደረጃ የተጀመረ ሲሆን በቀጣዩ የ2016 ዓ.ም ወደ ሙሉ ትግበራ የሚገባ ይሆናል ›› ብለዋል፡፡ 

የለውጥ ሥራዎቹ አበርክቶ ለትምህርት ጥራት   

አሁን ላይ በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ላይ ለሚታየው ስብራት በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ ፡፡ በተማሪዎች ላይ የሚታየው ከራስ ጥረትና ልፋት ይልቅ በሌሎች ትከሻ ወረቀትን ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ ከምክንያቶቹ በቀዳሚነት ይጠቀሳል ፡፡ በርካቶች እውቀትን ከመሸመት ይልቅ ኩረጃን እንደአቋራጭ መንገድ መጠቀምን ሲመርጡ ይስተዋላል ፡፡ አሁን አሁን ይህ መጥፎ ልምምድ ሥር እየሰደደ መጥቷል የሚሉት የትምህርት ሚንስቴር ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብረሃኑ ነጋ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን ትምህርት ከደረሰበት ውድቀት ማንሳት ከአገር ህልውና ጥያቄ የሚተናነስ አይደለም  ይላሉ ፡፡ለዚህም የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎች አቋራጭ መንገዶችን ለመዝጋት የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ ያሉት ሚንስትሩ ‹‹ ሀገር ለማዳን በሚከፍለው መስዋዕትነት ልክ ትምህርቱን ከወደቀበት ማንሳት የእዚህ ትውልድ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ፡፡ በእኛ በኩል የለውጥ ሥራዎችን ጀምረናል፡፡ ባለፈው ጥቅምት የተሰጠው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማካሄድ ኩረጃን ለመከላከል የተደረገው ጥረት ውጤት ተገኝቶበታል፡፡ በእኛ እምነት ከእንግዲህ ወደ ተቋማቱ የሚገቡትን ብቻ ሳይሆን አጠናቀው የሚወጡትም የሥራ ገበያውን ከመቀላቀላቸው በፊት ብቃታቸው መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ከተያዘው ዓመት ጀምሮ ትምህርታቸውን ላጠናቀቁ ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ የመውጫ ፈተና መስጠት የሚጀመር ይሆናል ›› ብለዋል፡፡  
 

 

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ 

 

Audios and videos on the topic