የወባ በሽታ ስጋት በኢትዮጵያ | ጤና እና አካባቢ | DW | 22.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

 የወባ በሽታ ስጋት በኢትዮጵያ

በአየር ንብረት መዛባት ሳቢያ የተከሰተዉ የሙቀት መጠን መጨመር በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢወች የወባ ወረርሽኝ ሊያስከትል  እንደሚችል አንድ ጥናት አመለከተ።በዩኤስ አሜሪካ የሚገኙት የኮሎምቢያና የሜይን ዩንቨርሲቲ የአየር ንብረት ተመራማሪወች ሰሞኑን ይፋ ባደረጉት ጥናት

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:29

6 ሚሊዮን ሰዎች ለወባ ተጋላጭ ይሆናሉ

 በኢትዮጵያ በደጋማና ከፍተኛ አካባቢወች የሚኖሩ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለወባ በሽታ ተጋላጭ ይሆናሉ ።        

በሜይንና በኮሎምቢያ ዩንቨርሲቲ ዓለም ዓቀፍ የአየር ፀባይና የማህበረሰብ ጥናት ተቋም ተመራማሪወች ሰሞኑን ይፋ  ያደረጉት ጥናት እንዳመለከተዉ የኢትዮጵያ ከፍተኛና ደጋማ አካባቢወች እስካሁን የወባ በሽታን አያዉቃቸዉም ነበር።
ከእንግዲሕ ግን ፤አጥኚዎቹ እንደሚሉት፤ ደጋማዉ የኢትዮጵያ አካባቢ ወባ በሚያስተላልፉ ትንኞች መደፈራቸዉ አይቀርም። የሜን ዩንቨርሲቲ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ብራድፊልድ ሊዮን የጥናት ዉጤቱን እንዲሕ ይገልፁታል።
«በአከባቢ አየር  ሙቀት መጨመር የተነሳ በአብዛኛወቹ የኢትዮጵያ አካባቢወች  ሞቃታማ  የመሆን አዝማሚያ እየታየ ነዉ።ይህ ለወባ ስርጭት  አመቺ የሆነዉ ሞቃታማ  የአየር ሁኔታ ቀስ በቀስም ከፍታ ወዳላቸዉ ቦታወችም እየደረሰ ነዉ።»
ከ18 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ የሆነ የሙቀት መጠን  «ፕላዝሞዲየም ፋንሲፈርም» ከከ15 ዲግሪ ሴኒቲ ግሬድ በላይ ደግሞ  «ፕላዝ ሞዲየም ቫይቫክስ» ለተባሉት የወባ በሽታ  አስተላላፊ ለሆኑት ትንኞች  አመቺ መሆኑ ተገልጿል።ከባህር ወለል በላይ ከ1500 እስከ 2500 ሜትር ከፍታ ያላቸዉ የሀገሪቱ ደጋማ አካባቢወች ግን የአየር ፀባዩ ከተጠቀሰዉ የሙቀት መጠን በታች በመሆኑ በተፈጥሮ የወባ በሽታ የማያሰጋቸዉ ቢሆንም በዓለም የከባቢ አየር የሙቀት መጠን መጨመር ሳቢያ እነዚህ ቦታወች ለወባ አስተላላፊ ትንኝ መራቢያ አመቺ እየሆኑ ሊመጡ እንደሚችል በጥናቱ ይፋ ሆኗል።
«ስለዚህ  እነዚህን  መረጃወች በመጠቀም  በመጀመሪያ ደረጃ የአየር ሁኔታ  አካሄድ  መገመት እንችላለን።  በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ  የከፍተኛ ቦታወችን  የአየር ሙቀት  መጠን አዝማሚያ ማየት እንችላለን።በመሆኑም ይህ ጥናት በተለይ የአየር ሙቀት መጠን ከወባ ስርጭት ጋር  ያለዉን ትስስር  አሳይቷል።»
የጥናት ቡድኑ እንደገለጸዉ የመረጃ ማሰባሰብ ስራዉ በጎርጎሮሳዊዉ ከ1981 እስከ 2014 ባሉት አመታት ጊዜ ዉስጥ የተካሄደ ነዉ።መረጃዉ በተሰበሰባቸዉ በእነዚህ 33 አመታት በኢትዮጵያ በየአስር አመታቱ ቢያንስ ዜሮ ነጥብ ሃያ ሁለት ድግሪ ሴኒቲ ግሬድ የሙቀት መጠን ጨምሯል።በዚህ አዲስ  የአየር ንብረት ጠቋሚ መረጃ መሰረትም  በሀገሪቱ  ከፍተኛ  አካባቢወች የሚገኙ  6 ሚሊዮን ሰዎች  በሂደት ለወባ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ በጥናቱ ተመልክቷል ። 
የወባ ትንኝ ለመፈልፈልና ወባን ለማስተላለፍ ራሱን የቻለ ሂደት ስላለዉ  በአጭር ጊዜ ዉስጥ የወባ በሽታ ይጨምራል ማለት እንዳልሆነ ተመራማሪዉ ገልፀዋል። ነገር ግን  ለዉጡ የተከሰተዉ በርካታ ህዝብ በሚኖርበት የሀገሪቱ ክፍተኛ ቦታወች መሆኑ የዓለም የከባቢ አየር ሙቀት መጨመርና  ወቅታዊዉ የኤልሊኖ የአየር ሁኔታ ክስተት በሂደት  እያመጣ ያለዉ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ተመራማሪዉ ገልፀዋል።
  «በተጨማሪም በኤሊኖ  ሳቢያ የሞቃታማ  አካባቢወች  የሙቀት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን በጥናቱ አሳይተናል። ከአመት አመት  በከፍተኛ ቦታወች አልፎ አልፎም ቢሆን ከፍተኛ ሙቀት እየታየ ነዉ።መጥፎዉ ነገር ኤልሊኖ በረዥም የጊዜ ሂደት የሚያመጣዉ ተፅዕኖ ነዉ።»


እንደ ዓለም አቀፉ  የጤና ድርጅት ዘገባ በጎርጎሮሳዊዉ 2015 በዓለም አቀፍ ደረጃ 212 ሚሊዮን ሰወች በወባ በሽታ የተጠቁ ሲሆን 429 ሺህ ሰዎች ደግሞ በዚሁ በሽታ ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት በቅተዋል።ከዚህም ዉስጥ  90 በመቶ የሚሆነዉ የህመምና የሞት መጠን በአፍሪቃ የተመዘገበ መሆኑ ተመልክቷል።

 

 

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ

 

Audios and videos on the topic