የወቅቱ የከተሜ ወጣቶች ዝንባሌ - ኢንስታግራም | ወጣቶች | DW | 24.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

የወቅቱ የከተሜ ወጣቶች ዝንባሌ - ኢንስታግራም

የ26 ዓመቷ ማርታ ታደሰ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ንቁ ተሳታፈዎች ከሚባሉ ወጣቶች ዘንድ ትመደባለች፡፡ ፌስ ቡክ ላይ ትፅፋለች፡፡ ለአንድ መልዕክት 140 ፊደላትን ብቻ የሚፈቅደው ምጥኑ ትዊተር ላይም አለች፡፡ ይበልጥ የምትታወቀው ግን ኢንስታግራም ላይ በምታጋራቸው ፎቶዎች ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:07

የፎቶዎች ማጋሪያው ኢንስታግራም በወጣቶች ተወዳጅ ሆኗል

ማርታ ፎቶግራፍ ማንሳት አጥብቃ ብትወድም በዩኒቨርስቲ ያጠናችውም ሆነ ኋላ የተሰማራችበት የሙያ መስክ ከጥበቡ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ያገኘችው በኮምፒውተር ሳይንስ ነው፡፡ ሁለተኛ ዲግሪዋ ደግሞ ማህበረሰብ ልማት ላይ ያተኩራል፡፡ ፎቶግራፍ ማንሳት የጀመረችው ከአራት ዓመት በፊት ሲሆን ኢንስታግራምን የተቀላቀለችው ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ አጀማመሯ እንዴት እንደበር እንዲህ ታስረዳለች፡፡ 

“በስልክ ነው [ፎቶ ማንሳት] የጀመርኩት፡፡ እንደማንኛውም የፎቶግራፍ ጀማሪ አበባ ፣ እንስሳት፣ ቤት ውስጥ በማንሳት ተጀመረና ከዚያ ኢንስታግራም ጋር ከተዋወቅኩኝ በኋላ ግን በሆነ ርዕስ ዙሪያ ሳይሆን ያሉኝን ፎቶዎች ነበር የምለጥፈው፡፡ ከዚያ በኋላ እንግዲህ አሁን ፎቶግራፍ አንሺዎች ብዙ የሚጠቀሟቸው DSLR የሚባሉት ካሜራዎችን ከተዋወቅኩ በኋለ ግን ሌላውን እንደመነጋገሪያም፣ እንደመግባቢያም፣ የተለያዩ ጉዳዩችንም እያነሳሁ ከኢንስታግራም ማህብረሰብ ጋር በደንብ ሀሳብ እንድለዋወጥ ረድቶኛል” ትላለች፡፡

ማርታ የኢንስታግራም ማህብረሰብ የምትለው እንደ ሀገር ቢወሰድ በህዝብ ብዛት ከህንድ እና ቻይና ቀጥሎ የዓለማችን ሶስተኛ ሀገር ነበር የሚሆነው፡፡ መቀመጫውን በጀርመን ሀምቡርግ ያደረገው የስታስቲክስ ጥናት ተቋም ስታቲስታ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው የኢንስታግራም ንቁ ወርኃዊ ተጠቃሚዎች ቁጥር 600 ሚሊዮን ደርሷል አሉ፡፡ እንደ ጎርጎሮሳዊው 2010 አገልግሎት መስጠት የጀመረው ኢንስታግራም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁንጮ ከሚባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተርታ ለመሰለፍ ብዙ ዓመታት አልወሰደበትም፡፡

የእንግሊዘኛዎቹን “ፈጣን ካሜራ” እና “ቴሌግራም” ቃላት በአንድ ባማጣመር ስያሜውን ያገኘው ኢንስታግራም የራሱ የሆኑ ልዩ ባህሪያት አሉት፡፡ አንድ ተጠቃሚ ፎቶዎችን ለተከታዩቹ እንዲያጋራ ታቅዶ ቢሰራም ፎቶዎቹ ግን በየትኛውም ሁኔታ ይነሱ ኢንስታግራም ላይ የሚወጡት በአራት በካሬ ቅርጽ ብቻ ነው፡፡ ተጠቃሚዎች ፎቶዎቹን እንዳሻቸው እንዲያበጃጁት የሚያስችል ማስተካከያ አለው፡፡ ኢንስታግራም በዋናነት የተሰራው ለተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች በመሆኑ ፎቶዎቻቸውን በአድራሻቸው ማጋራት የሚፈልጉ አፕልኬሽኑን በስልካቸው መጫን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢንስታግራም የግለሰብ ገጾችን ግን በኮምፒውተር አሊያም በላፕቶፕ መመልከት ይቻላል፡፡

ኢንስታግራም አግልገሎት መስጠት ሲጀምር ፎቶዎች ላይ ብቻ ትኩረት ቢያደርግም ከምስረታው ሶስት ዓመት በኋላ ግን ተጠቃሚዎቹ እስከ 15 ሰከንድ ርዝመት ያላቸውን ቪዲዮዎችን እንዲጭኑ ዕድል ሰጥቷል፡፡ እንደስታቲስታ መረጃ ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ 41 በመቶ የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ከ16 እስከ 24 ያሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከ25 እስከ 34 ዓመት ያሉ ወጣቶች ደግሞ 25 በመቶውን የተጠቃሚዎች ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ርካሽ እና ለአጠቃቀም ቀላል የሆኑ ዘመናዊ ስልኮች መስፋፋት ኢንስታግራም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ጭምር የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እንዲበዛ አድርጓል፡፡

የፊት እና የኋላ ካሜራ የተገጠመላቸውን ዘመናዊ ስልኮች ተጠቅመው የሚነሱ የራስ ፎቶዎች ከኢንስታግራም መምጣት ጋር ይበልጥ ቦታ አግኝተዋል፡፡ ብዙዎች ኢንስታግራም ሲባል “ሰልፊ” የሚል ጥቅል ስያሜ ያላቸው እንዲህ አይነት ፎቶዎች ከፊታቸው ድቅን የሚለውም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የአዲስ አበባዋ ማርታ “ኢንስታግራም ከሰልፊም በላይ” መሆኑን የራሷ ስራዎች ምሳሌ በማድረግ ትከራከራለች፡፡  

“የሰልፊ ልምድ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ የእውነት መውሰድ አልቻሉም ኢንስታግራምን፡፡ እኔም ስጀምር በጣም ብዙ ሰልፊ ነበሩኝ ከዚያ በኋላ ግን ኢንስታግራም ጥሩ ነገር ያደረገው ምንድነው የግለሰብ እና የስራ ገጽ የሚባል ነገር መጣ፡፡ ስለዚህ ሰዎች የስራ ከሆነ የስራ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የግለስብ ገጻቸው ላይ የግል ነገራቸውን ማድረግ ይችላሉ፡፡ ድረ-ገጽ ላይ የተለያየ አይነት ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ሁሉም ግን የራሱ የሆነ አቀራረብ ይኖረዋል፡፡ እኔ ግን ልዩ ያደርገኛል የሚል ነገር ኖሮ ሳይሆን የማነሳቸው ሀሳቦች ግን ከሌላው ሰው በተለየ የራሴ የሆነ መንገድ አለኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ የተለያዩ ነገሮችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ የሴቶች እኩልነት፣ ድህነት እና ማህበራዊ ፍትህ ላይ በእነዚህ ዙሪያ በደንብ ሰርቺያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ እየሰራሁም ነው” ትላለች ከሰልፊ ባሻገር እንዴት ኢንስታግራምን ላቅ ላሉ ነገሮች መጠቀም እንደሚቻል ስታብራራ፡፡

በእርግጥም የማርታን የኢንስታግራም ገጽ የጎበኘ የተናገረቻቸውን ጉዳዮች በፎቶዎች ይመለከታል፡፡ የምትሰራበት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የማህብረሰብ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ መሆኗም የጠቀማት ይመስላል፡፡ “የከተሜ ጉዳዮችን ይበዙበታል” ተብሎ ለሚተቸው የኢትዮጵያ ኢንስትግራም ምህዳር ወጣ ያሉ ዕይታዎችን ከሚያቀርቡት ውስጥ እንዷናት፡፡ በምትጓዝባቸው ቦታዎች ያሉ ጥሬ ዕውነቶችን ጠያቂና ሳቢ በሆነ መልኩ ታሳያለች፡፡ የ“ሰዎች ታሪኮች ይስቡኛል” የምትለው ማርታ “በማንኛውም ደረጃ ወይም ዘርፍ ይሁኑ ምን ሀሳብ አላቸው እና ለሰው ምን መናገር ይችላሉ?” የሚለውን በእኩል ደረጃ ለማሳየት እንደምትሞክር ትናገራለች፡፡

ካሉት የማህበራዊ መገናኛዎች ለኢንስታግራም ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የ30 ዓመቱ ሚካኤል ፋሲል እንደ ማርታ ሁሉ ሰዎች ዘንድ እንዲደርስ የሚፈልገውን መልዕክት ማስተላለፊያ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ በሙያው ፎቶግራፍ አንሺ የሆነው ሚካኤል በኢንስታግራም ላይ የሚያወጣቸው ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች እምብዛም ትኩረት ያላገኙት ጉዳዮችን የሚዳስሱ ነው፡፡

“የኢንስታግራም ገጼ ላይ የጀመርኩት ‘My city, my people, my passion’ በሚል ሀሽታግ በተጨማሪም ኢትዮጵያኛ በሚል ሀሽታግ ‘እኛ ሰፈር’ ሀሽታግ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ያልተነገሩ ታሪኮችን፣ ያልተነገሩ ታሪኮችን ለመናገር ጥረት እያደረግሁ ያለሁት፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ወይን አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የህይወት ዘይቤ የምናውቀው ወይ በአገር ጎብኚዎች ነው፣ ወይም ህንጻዎችና መንገዶች ሲሰሩ ነው፡፡ ‘ግን የየሰው ትክክለኛው የየቀን ውሎው ምን ይመስላል?’ የሚለውን ለማሳየት ነው ጥረት የማደርገው” ይላል በገጹ ላይ ስለሚያጋራቸው ፎቶዎችና ቪዲዎች ይዘት ሲያስረዳ፡፡    

የሚካኤል የአዲስ አበባን የቀን ተቀን ማስተዋወቅ ጥረት በተከታዩቹ ዘንድ ብቻ ተገድቦ አልቀረም፡፡ ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ድርጅት ራሱ ዕውቅና የሰጠው ነገር እንደሆነ ሚካኤል ይናገራል፡፡ ድርጅቱ በላከለት የኤ-ሜይል መልዕክት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በጥሩ ሁኔታ እንደሚያሳይ እንደገለጸለትና ለዚህም ጥረቱ የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች እንዲከተሏቸው ከሚጠቆሙት አንዱ አድርጎ እንደመረጠው ይገልጻል፡፡ ይህም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ተከታዩቹን እንዳበዛለት ያስረዳል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚካኤል ተከታዩች ቁጥር 66 ሺህ ደርሷል፡

በተከታይ ቁጥር ከተለካ ከኢትዮጵያውያን ኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ውስጥ ወጣቶቹ እንስት ተዋናዮች እና ዝነኞች ዘንድ የሚጠጋ ማግኘት ከባድ ይሆናል፡፡ ራሳቸው የከፈቱትም ሆነ አድናቂዎቻቸው የከፈቱላቸው ሺህዎች ተከታዮች አሏቸው፡፡ ከፍተኛ የተከታይ ቁጥር ካላቸው መካከል የ23 ዓመቷ ተዋናይት አዲስ ዓለም ጌታነህ ትገኝበታለች፡፡ 106,000 ተከታዮች አሏት። የዛሬ አራት ዓመት ግድም ፊልም መስራት የጀመረችው አዲስ ዓለም እስካሁን በ10 ፊልሞች ላይ ተውናለች፡፡ ኢንስታግራም አዘውትራ የምትጠቀመው አዲስ ዓለም የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በአጋጣሚ ብትቀላቀልም ከሁሉም ማህበራዊ መገናኛዎች አብልጣ እንደምትወደው ታስረዳለች፡፡

“መጀመሪያ ስከፍተው ፎቶ አርትኦት ይደረግበታልና የፎቶ አርትኦት የሚሰራበት ነበር የሚመስለኝ፡፡ መጀመሪያ ስለኢንስታግራም ብዙ ግንዛቤውም አልነበረኝም፡፡ ከዚያ በኋላ ግን እየተጠቀምኩ ስመጣ ግን ራስህን እንደሌሎቹ ታስታዋውቅበታለሁ፡፡ አዲስ ስራ ሲኖረህ ለተመልካችህ ‘በቅርብ ቀን’ እያልክ ፖስት ታደርጋለህ፡፡ ራስን ለማስተዋወቅ ይጠቅማል፡፡ ለእኔ ከሁሉም ማህበራዊ መገናኛ ኢንስታግራም ነው የምወደው፡፡ አሁን ለምሳሌ ፌስ ቡክ ስትከፍት ያልሆነ ነገር ታየለህ፡፡ ኢንስታግራም ግን አንተ ደስ ያለህን ነገር ትከተላለህ፡፡ ያልሆነ ነገር ታግ አይደርግብህም፡፡ እና እኔ በበኩሌ ለኢንስታግራም ነው የማደላው” ትላለች የውዴታዋን ምክንያት ስትገልጽ፡፡ 

ቢያንስ በሳምንት አንዴ ፎቶዎችን እንደምታጋራ የምትናገረው አዲስ ዓለም በቀን አንዴ ወደ ኢንስታግራም ጎራ ብላ ፎቶዎችን እና መልዕክቶችን መመልከት ልማዷ እንደሆነ ታስረዳለች፡፡ ከፊልሞቿ ተመልካቾች እና አድናቂዎች ጋር ለመገናኛት ሁነኛ መድረክ በመሆን  እያገለገላት እንደሆነ ትመሰክራለች፡፡ ኢንስታግራም ለማርታም ፎቶዎቿን ከማሳያ መድረክነቱ ሌላ ጥቅሞች ይዞላት መጥቷል፡፡ ፎቶዎቿን በኢንስታግራም የተመለከቱ የግዢ ጥያቄ አቅርበውላት እንዲጠቀሙበት ሸጣላቸዋለች፡፡ ስራዎቿን ያዩ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ሰዎች አነጋግረዋት ከባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ከእነርሱ ጋር የመስክ ስራዎች እየሰራች እንደሆነም ትገልጻለች፡፡ ሚካኤልም ትሩፋቱ ደርሶታል፡፡ የኢንስታግራም ድርጅት ተጠቃሚዎች እንዲከተሉት መጠቆሙ ስራዎች እንዳመጣለት ይናገራል፡፡   

“ብዙ ደንበኞች በእርሱ መልኩ አግኝቻለሁ፡፡ በእርሱ አጋጣሚ ብዙ ስራዎችን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ አንድ በቅርብ የተዘጋጀ ሁነት ነበር፡፡  የአፍሪካ ህብረት 28ኛው ጉባኤ ላይ የአፍሪካ የልማት ባንክ ፕሬዝዳንት የግል ፎቶ አንሺ ሆኜ እንድሰራ ኢንስታግራም ገጼ ጠቅሞኛል፡፡ በአጋጣሚ የእነርሱ creative director ነበር ፎቶዎቼን ያየው፡፡ እርሱ በጣም ስለወደዳቸው የአፍሪካ ህብረት በሚያደርገው ጉባኤ ላይ ፍሪላንስ  ፎቶግራፈር አድርገውኝ በትክክል ተጠቃሚ መሆን ችያለሁ” ይላል ሚካኤል፡፡  

ግርማ በርታ የተባለ ኢትዮጵያዊ ወጣት ፎቶ አንሺም የኢንስታግራም ፎቶዎቹ የ10 ሺህ ዶላር ሽልማት አስገኝተውለታል፡፡ ፎቶ አንሺው Getty Images የተባለ ዕውቅ የፎቶ አቅራቢ ድርጅት ከኢንስታግራም ጋር በመተባበር በየዓመቱ የሚያዘጋጀውን ዓመታዊ ውድድር ካሸነፉ ሶስት የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች አንዱ ሆኖ የተመረጠው በዚህ ዓመት መግቢያ ላይ ነበር፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ 

 ሸዋዬ ለገሰ 

Audios and videos on the topic