የወሰን ግጭት በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች | ኢትዮጵያ | DW | 28.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የወሰን ግጭት በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች

በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ድንበር ግዛት ይገባኛል ሰበብ በተቀሰቀሰ ግጭት በትንሹ 13 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸው ተሰማ፡፡ ግጭቱን በአካባቢው እንደነበር የሁለቱም ክልል ባለስልጣናት ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ አና የመከላከያ አባላት ከተሰማሩ በኋላ ግን ግጭቱ መብረዱን ጠቁመዋል፡፡ 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:34

ፖሊስ አና መከላከያ በስፍራው ተሰማርቷል ተብሏል

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ነዋሪዎች እና በደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ የኮሬ ማህብረሰብ ነዋሪዎች መካከል ግጭት የተቀሰቀሰው ባለፈው እሁድ ሐምሌ 16 ነበር፡፡ እስከ ረቡዕ ድረስ በዘለቀው ግጭት ሰዎች መሞታቸውን፣ በርካቶች መቁሰላቸውን እና ቤቶች መቃጠላቸውን የክልሎቹ ባለስልጣናት ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በግጭቱ ስለደረሰው ጉዳት ተከታዩን ተናግረዋል፡፡ “በሁለቱም ወገን 13 ሰዎች እንደሞቱ ነው እስካሁን በደረሰን መረጃ ማረጋገጥ የቻልነው፡፡ ከጉጂ ወገን ወደ ዘጠኝ ሰዎች እንደገና ከኩሬ ብሔረሰብ ወገን ደግሞ አራት ሰዎች ሞተዋል፡፡ በርካታ ሰዎችም እንደቆሰሉ ነው መረጃው” ብለዋል አቶ አዲሱ፡፡   

በግጭቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰው በደቡብ ክልል የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ውስጥ እንደሆነ አቶ ተሰማ ታምሩ የአማሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል፡፡ ጭግቶቹ በአማሮ ወረዳ ቆሬ፣ ዳኖ፣ ጀሎ፣ ዶርባዴ፣ ሻሮ እና ወደ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ ባሉ ቦታዎች ላይ እንዳሉ ለዶይቸ ቬለ አስረድተዋል፡፡ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ስለደረሰው ጉዳት ደግሞ ተከታዩን ብለዋል፡፡   

“ከእኛ በኩል የሰው ሞት እየተጣራ ነው፡፡ ያልደርስንበት ዳኖ ቀበሌ ላይም ሰራዊትም እየገባ ስላለ ሰራዊቱ ሲያጣራ የሞተውን ቁጥር በትክክል መንገር ይቻላል፡፡ ለጊዜው አሁን ሰባት ቁስለኛ እኛ ጋር ሆስፒታል የተላኩ እንዳሉ ነው፡፡ አሁን በእኛ በኩል ጀሎ የምንለው ቀበሌ በአብዛኛው የተቃጠለበት፣ አንድ እዚያ የነበረ የመንግስት የጤና ኬላ የወደመበት፣ በርካታ እህሎች የተቃጠሉበት ነው፡፡ ከወዲህ ደግሞ ዶርባዴ  የምንለው ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል ልክ የቀበሌዎች ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ንብረት፣ እህል ወድሟል፡፡ ወደ ሻሮ በተመሳሳይ በእህል ላይ ከፍተኛ ቃጠሎ ነበር፡፡ ዳኖ በሚባል ቀበሌም ተመሳሳይ ነው፡፡ በስፋት ኦሮሚያ በህዝባችን ላይ ጉዳት አድርሶ ህዝቡ ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ ነው ያለው” ይላሉ አቶ ተሰማ፡፡ 

የሁለቱ አካባቢዎች ነዋሪዎች በግጦሽ መሬት እና የውሃ ቦታ ይገባኛል ሰበብ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ይጋጩ የነበረ ሲሆን የአሁኑ ግን ጠንከር ያለ እንደሆነ ከስፍራው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ከሌሎች  ክልሎች ጋር የሚያዋስኑትን እና የግጭት መነሻ የሆኑ ቦታዎችን የማካለል እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ የሚያስታውሱት አቶ አዲሱ የሰሞኑ ግጭትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ 

“የኮሬ ማህብረሰብ የሚገኝበት የአማሮ ወረዳ ከጉጂ ገላና እና አባ ወረዳዎች ጋር ነው የሚዋሰነው፡፡ ስለዚህ በዚህ አካባቢ ላይ የተወሰኑ ቀበሌዎች ላይ የድንበር ማካለል ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ከዚያ ጋር ተያይዞ ስብሰባዎች እና ተከታታይ ውይይቶች ሲደረጉ ነበር፡፡ በ16 የተከሰተው ምንድነው? በዚህ ጉዳይ ላይ እያሉ ከጎጂ ማህብረሰብ አካባቢ የጠፉ ከብቶችን ፍለጋ ወደ ኮሬ ማህብረሰብ የተሻገሩ ሰዎች ሶስት ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡ ግጭቱ መነሻው ይሄ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የጸጥታ አካል እስኪገባ ድረስ ችግሩ ወደ መባባስ ነው የሄደው” ሲሉ መንስኤውን ገልጸዋል፡፡

የአማሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ግን ችግሩ ከወሰን ይገባኛል በላይ የተፈጥሮ ኃብት ጉዳይም ነው ይላሉ፡፡“ግጭቱ የድንበር ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር እርሶ አደሩ መነሻ ነው የሚላቸው የግጦሽ፣ የውሃ ችግሮች ናቸው፡፡ በኋላ ግን ድንበርም ይውጣ የሚል መነሻ ነበር፡፡ ድንበር ከማካለል ጋር ደግሞ ተያይዞ መጀመሪያ የተወሰኑ ነገሮችን መነሻ አድርጎ ሰው ያለመግባባት ነበር” ብለዋል አቶ ተሰማ፡፡  

ሁለቱም የክልል ኃላፊዎች በአካባቢው የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት ከተሰማራ በኋላ ዛሬ ግጭቱ ጋብ ማለቱን ተናግረዋል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሐመድ
   

Audios and videos on the topic