የወሊድ መከላከያ ኪኒን ሐምሳኛ አመትና ዉጤቱ | ዓለም | DW | 11.05.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የወሊድ መከላከያ ኪኒን ሐምሳኛ አመትና ዉጤቱ

ጧት ከእንቅልፍ-ብድግ ትንሿን እንክብል ዋጥ ከዚያ---በቃ።ከትልቁ የሕይወት ሒደት ወደ-እራፊዋ ዕለት ምግባር-ዉልቅ ወይም ግብት።ለከሐምሳ-አመቶቹ በፊት ወላዶች ግን ሕወይት እንዲሕ ወዛ አልነበረም

default

05 05 10

የወሊድ መከላከያ ኪኒን አገልግሎት ላይ ከዋለ ባለፈዉ ሳምንት አርብ ሐምሳኛ አመቱን ደፈነ። የመዋለድን ነባር ተፈጥሯዊ ዑደት የቀየረዉ ሳይንሳዊ ግኝት በአደጉት ሐገራት አሁን ለሚታየዉ የወሊድ ምጣኔ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።የሕዝቡን በተለይም የሴቶችና የሕፃናትን የአኗኗር ዘይቤም በጅጉ ለዉጦቷል።በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙት ሐገራት ሕዝብ ቁጥር ግን ኪኒኑ ከታወቀ ከሐምሳ አመት በሕኋላ አሁንም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነዉ።ኬይለ ጀምስ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተለዉ አጠናቅሮታል።

የዩናይትድ ስቴትስ የምግብና የመድሐኒት አስተዳደር የነገ-ሐምሳ አመት ኪኒኑ እንዲዋጥ ሕጋዊ ፍቃድ ሲሰጥ ድሕነት፥ የሕዝብ መጨናነቅ፥ የሰዉ በጣሙን የሴቶች ጉስቁልና ብቻ ብዙ ችግር-ደሕና ሰንብት ተብሎ ተዘፍኖ-ተደንሶለት ነበር።

አለም ያኔ የተባለዉን ያክል ለዉጥ በርግጥ አላየችም።እንግሊዝኛ ተናጋሪ-ወይም እንግሊዝኛ ቀመሶች-ፒል ብለዉ የሚጧሯት (አንቺ ብለናታል) ኪኒን ትንሽ ናት።ምሥር ብጤ፥ ምሥር አከሏ-ኪኒን ያኔ ከተባለላት ብዙ፥ ብዙዉ መለወጧ ግን አንድ ሁለት አያሰኝም።እንደ ትንሽ እነቷ ሁሉ-የሚያዉቁ እንደሚሉት አጠቃቀሟም-ቀላል ነዉ።

ጧት ከእንቅልፍ-ብድግ ትንሿን እንክብል ዋጥ ከዚያ---በቃ።ከትልቁ የሕይወት ሒደት ወደ-እራፊዋ ዕለት ምግባር-ዉልቅ ወይም ግብት።ለከሐምሳ-አመቶቹ በፊት ወላዶች ግን ሕወይት እንዲሕ ወዛ አልነበረም።የቤተ-ሰብ ምጣኔ ተቋም የቀድሞ ሐላፊ ኢንጋር ብሩግማን እንደሚሉትማ መራር ነበር።
ድምፅ
«ታላቅ መቅሰፍት ነበር።አጥፊ ነበር።በእዉነት መከራ ነበር።»

ያልተጠበቀ እርግዝና በተለይ ትዳር ላልያዘች ሴት ኑሮ-ሕይወትን የሚያበላሽ፣ የሚያጠፋ ይሕ ቢቀር የወደፊት እጣ ፈንታን ብዙ ጊዜ ባልተፈለገ አቅጣጫ የሚዘዉር ነበር።ቀጠሉ ወይዘሮ ብሩግማን።
ድምፅ
«ጋብቻ ብቸኛዉ ግዴታ ነበር።እና እንዲት የተዛባች ሌት-ከተዛባ ትዳር ትጥላለች።ጫናዉ ደግሞ በጣም ከባድ ነበር።በማርገዛቸዉ ምክንያት ብቻ ሕይወታቸዉን ያጡ ብዙ ወጣት ሴቶች አዉቃለሁ።»

ወጣቷ ካረገዘች ምርጫዋ-ሰወስት ነዉ።ከሆነላት ማስወረድ።ከተሳካላት ትምሕርት፥ሥራዋን አቋርጣ ማግባት።ሰወስተኛዉ ሁለቱን እየሞከሩ ወይም እያሰቡ ከተወዳጁ አለም-ሕይወት---አዲዮስ።በዘመናችን ሚሊዮኖች ከእናት አያቶቻቸዉ መከራ ተላቅቀዋል።አንድ መቶ ሚሊዮን ሴቶች ኪኒኗን ይዉጣሉ።ብዙዎቹ የበለፀጉት ሐገራት ዜጎች ናቸዉ።ለድሆቹ ሐገራት ብጤዎቻቸዉ ግን ብዙ ለወጥ የለም። የአንዲት አለም ሁለት ገፅታ ሐቅ።የደስታ-ሐዘኑ ቅይጥ-እዉነት።ይሕ ነዉ።

ናይጄሪያ ዉስጥ ከየሰባቱ ሴት-አንዷ በእርግዝና እና ከግርግዝና ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ትሞታለች። ከሰሐራ በስተደቡብ የሚገኙ ሐገራት ሴቶች በአማካይ ከአምስት ልጅ ይወልዳሉ።የበለፀጉት ሐገራት አቻዎቻቸዉ ግን አንድ ግፋ ቢል ሁለት-ቢወልዱ ነዉ።የጀርመኖች የመዋለድ ሒደት ቀንሶ ቀንሶ-ትዉልድ እራሱን ከማይተካበት ደረጃ ደርሷል።

በረሐብ በሽታ የሚሰቃየዉ የአፍሪቃ ሕዝብ ቁጥር ግን በሚቀጥሉት አርባ አመታት በእጥፍ-ይጨምራል።የዚያች ጉደኛ ኪኒን የወሲብ አብዮት-አለምን አዳርሶ-ፈዉሳል ማለት ይቻላል?-በሩግማን-አይቻልም አይነት ነዉ-መልሳቸዉ።
ድምፅ
«የፒል ሐምሳኛ አመት ለምዕራቡ የሐምሳ አመት ነፃነት፥ ለአዳጊዉ አለም ባንፃሩ የሐምሳ አመት ዉድቀት ነዉ።»
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚገምተዉ ፅንስን በመከላከል ወላጆችን ብቻ ሳይሆን በየአመቱ የሚሞቱ የሰወስት ሚሊዮን ሕፃናትን ሕይወት መታደግ ይቻል ነበር።ድሕነት፥ የሕዝብ ቁጥር እድገት፥ የዘፈጥሮ መዛባት ይቀንሳል።የአዳጊዊቹ ሐገራት ሴቶች ትንሿን ግን ትልቅ ለዉጥ አምጪዋን ኪንን የሚወስዱበት ምክንያት ብዙ ነዉ።ሐይማኖት፥ ባሕል፥ የወንዶች በተለይም የባሎች ተፅዕኖ ሌላም።የብዙዎቹ ምክንያት ግን አንድ ነዉ።አለማወቅ።
ድምፅ
«ኪኑን መዋጥ ልክ እንደ ኮንዶም ሁሉ ከባድ ነዉ።ምክንያቱም በተከታታይ በየዕለቱ መወሰድ እንዳለበት ሊታወቅ ይገባል።ብዙዎቹ ሴቶች ሥለጎንዮሽ ጉዳቱ፥ በጤና ላይ ሊያደርስ ሥለሚችለዉ አደጋ የተሳሳተ እምነት ነዉ-ያላቸዉ።በዚሕ የተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት ከየአራቱ፥ አንዳዴም ከየሁለቱ ሴቶች አንዷ የወሊድ መቆጣጠሪያ ኪኑን አይወስዱም።»

ይላሉ የጀርመኑ የሥነ-ሕዝብ በጎአድራጎት ድርጅት የበላይ ኡተ ሽታልማይስተር።

ለአካለ መጠን ከደረሱ አፍሪቃዉያን ወጣት ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚወስዱት ከመቶ ሃያዎቹ ብቻ ናቸዉ።አፍሪቃን ቢያንስ በዚሕ መስክ ለመለወጥ መፍትሄዉ-ለዘንቁ የአፍሪቃ ችግሮች የሚነገረዉ ነዉ።ትምሕርት-ይላሉ አዋቂዎች።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic