የወለጋ ሀገር ሽማግሌዎች የሰላም ጥሪ
ረቡዕ፣ ኅዳር 18 2017በወለጋና ሌሎች የተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች መንግሥት እና ተፈላሚ ኃይሎች በውይይት እንዲፈቱ የሀገር ሽማግለዎች ዛሬም የሰላም ጥሪ እያቀረቡ ነው። በወለጋ የተለያዩ ዞኖች ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች ረጅም ጊዜ ከመውሰዳቸው ጋር ተያይዞ የተለያዩ ዘርፍ ብዙ ችግሮችን እያስከተለ እንደሚገኝ ከነቀምቴ እና ዲምቢ ዶሎ ከተማ ያነጋርናቸው ሀገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል። ዜጎች በሰላም ወጥቶ እንዲገቡ በወለጋም ሆነ በክልሉ ያለው ግጭት በውይይትና ድርድር እንዲቋጭ ጥሪ አቀርቧል።
የምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ምትኩ ደበላ አካባቢው ለተራመ ጊዜ በግጭት ውስጥ መቆየቱ በነዋሪው ላይ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽህኖ ማሳደሩን ተናግረዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ እና ለንብረት መውደም ምክንያት መሆኑን አንስተዋል። በምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ እንደ ኪረሙ፣ ጊዳ አያና ሳሲጋ እና አኖ የሚባሉ ቦታዎች በሸማቂዎችና መንግሥት ጸጥታ ኃይሎች መካከል በተከሰቱ ግጭቶችና በተለያዩ ስም የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች በሚደርሱት ጥቃቶች አካባቢው ለከፍ ችግር ተጋልጦ መቆየቱን አመልክተዋል። ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በዞኑና ዙሪያው የሚንቀሳቀሱ ሸማቂ ቡድኖች መንግሥት ልዩነታቸውን አሁንም ወደ ድርድርና ውይይት በማቅረብ ለተፈጠሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያበጁ ጥሪ አቅርቧል።
በቀሌም ወለጋ ዞን የተለያዩ አካባቢዎችም ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት የተከሰቱ ጸጥታ ችግሮች በግብርና እና ንግድ፣ ጤና እንዲሁም በትምህት ዘርፍ ላይ ተጽህኖ መሳደራቸውንና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት ሳይሰጡ መቆየታቸውን አንድ ከደምቢዶሎ ከተማ ያነጋርናቸው ነዋሪ አብራርተዋል።፡ ከፍተኛ የቡና ምርት የሚገኝበት ቀሌም ወለጋ ከሁለት ዓመት በፊት የጸጥታ ችግሩ የመጓጓዣ አገልግሎትን አስተጓጉሎ እንደነበር ተናግረዋል። በአካባቢው ሕዝቡን ማኅበራዊ እረፍት የነሳውን ግጭት ለማስወገድ ከዚህ ቀደም የተቋረጠውን ድርድር ለሦስተኛ ዙር እንዲቀጥል ሀሳብ አቅርቧል።
ሌላው የነቀምቴ ከተማ ነዋሪም በሰጡን ሀሳብ በወለጋ እዚህም እዚያም በነበሩት ግጭቶች ምክንያት ሰዎች ተፈናቅለው መቆየታቸውን እና የምርት መጠን በአሁኑ ወቅት መቀነሱን ጠቁመዋል። በምሥራቅ ወለጋ በአንዳንድ አካባቢ የኑሮው ውድነት በጣም በመጨመሩ ከኅብረተሰቡ የመግዛት አቅም በላይ መሆኑን ገልጸዋል። ይህንን ዘርፍ ብዙ ችግር ለመፍታት ከመወነጃጀል የሕዝቡን ጥቅም በማስቀደም ሁለቱ ኃይሎች በውይይት ለችግሮቹ መፍትሄ ማበጀት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በኦሮሚያ ክልል እየተስተዋለ ያለው ግጭት ሰላማዊ በሆነ መልኩ በውይይት እንዲፈታ ከተለያዩ የክልሉ ዞኖች ተመሳሳይ ጥሪዎች እየቀረቡ ይገኛሉ። ባለፈው እሑድ በዶቼቬለ እንወያይ ዝግጅት ላይ በመቅረብ የተወያዩት የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐይሉ አዱኛ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ አማካሪ አቶ ጂረኛ ጉዴታ በክልሉ ሰላም ለማስፈን በሚለው ጉዳይ ላይ ለድርድና ውይይት የተለያዩ ቅደመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ሀሳብ ሰጥቷል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ
ፀሐይ ጫኔ