የኮፐንሃገኑ ጉባኤና ተስፋዉ | ጤና እና አካባቢ | DW | 08.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የኮፐንሃገኑ ጉባኤና ተስፋዉ

ከ192አገራት የተዉጣጡ ተወካዮች በዴንማርክ ኮፐንሃገን በአየር ሁኔታ ለዉጥ ላይ የሚያደርጉትን የ12ቀናት ጉባኤ ከጀመሩ ዛሬ ሁለተኛ ቀናቸዉን አስቆጥረዋል።

default

የተመድ በሚያስተናግደዉ በዚህ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ የተሰባሰቡት 15,000 ሰዎች ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚያበቃዉን የኪዮቶ ስምምነት የሚተካ ዉል ለማዉጣት በዉይይት ተጠምደዋል። የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ጠባይ ጉዳይ ባለስልጣን የሆኑት ኢቮዎ ደቦር ለረዥም ጊዜያት በጉጉት ሲጠበቅ የከረመዉን የኮፐንሃገኑን ጉባኤ ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር ይህ ስብሰባ ታሪክ እንደሚሰራ፤ ያ ደግሞ ትክክለኛ ታሪክ ሊሆን እንደሚገባዉ አሳስበዋል። ይህ ጉባኤ ሲጠናቀቅም እያንዳንዱ ኃላፊነት ያለበት አገር ሊቀንስ የሚገባዉን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት መጠን የሚገልፅ መረጃ ማየት እንደሚፈልጉ ከወዲሁ አሳስበዋል፤

«የሁለት ሳምንቱ ጉባኤ ሲጠናቀቅ ዩናይትድ ስቴትስ ለ2020ዓ,ም፤ የአዉሮጳ ኅብረት እንዲሁ በዚሁ በ2020ዓ,ም እንዲሁም ጃፓን ለ2020ዓ,ም ለማድረግ ቃል የገቡት ይኸዉ ብዬ ትንሽ ወረቀት ላሳያችሁ መቻል ይኖርብኛል ብዬ አስባለሁ። በሌላ አባባል ማን ለምን ኃላፊነት እንደወሰደ የማይጠቁም ጥቅል ነገር ብቻ ማቅረቡ በቂ አይደለም።»

Yvo de Boer

ዩቮ ደቦር በጉባኤዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት

ዩቮ ደቦር ዛሬ ደግሞ የአደገኛ ጋዞች በከባቢ አየር መከማቸት ለጤና አደገኛ መሆኑ በባለሙያዎች መገለፁን ተከትሎ የአሜሪካ ህግ አዉጪ አካል የብክለት መጠንን ስለመቆጣጠር መመሪያ እንደሚያወጣ ያላቸዉን ተስፋ ገልፀዋል። በዓለም ከባቢ አየርን በመበከል በግንባር ቀደምትነት በምትወቀሰዉ ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት የአገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የፕሬዝደንት ኦባማ መንግስት ከተሽከርካሪዎች፤ ከኢንዱስትሪዎችና ከሌሎችም በአገሪቱ ዉስጥ ከሚገኙ የብክለት ምንጮች የሚወጡ አደገኛ ጋዞች መጠን እንዲወሰን እንዲያደርግ መጠየቁ ተሰምቷል። ኦባማ ግን ምክር ቤታቸዉ አዲስ የአየር ንብረት ህግ እስኪያወጣ መጠበቅ እንደሚመርጡ ተጠቁሟል። ያም ሆኖ እስከ 2020ዓ,ም የአደገኛ ጋዞች ልቀት መጠን በ17በመቶ መቀነስ ይኖርበታል ሲሉ ኦባማ ሃሳብ ቢያቀርቡም በአገሪቱ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች በቂ አይደለም በሚል ዉድቅ ተደርጓል።

በኮፐን ሃገን ለ12ቀናት ከሚካሄደዉ ጉባኤ ከፊሉን እንደሚሳተፉ ከሚነገርላቸዉ አንድ መቶ የየአገራት መሪዎች መካከል የጀርመን መራሂተ መንግስ አንጌላ ሜርክል አንዷ ናቸዉ። ሜርክል ከአንድ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጋ ባደረጉት ቃለምልልስ አገራት ለከባቢ አየር ብክለት የሚያደርጉትን አፍራሽ አስተዋፅኦ በጥንቃቄ አጢነዉ ለመቀነስ ዝግጁ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። ከምንም በላይ ቻይናና ህንድ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት ሊወስዱ እንደሚገባም አሳስበዋል። ባለግዙፍ ኢንዱስትሪ አገራት ሊቀንሱት የሚገባዉን የአደገኛ ጋዝ ልቀት መጠን እንዲያስታዉቁ ሲወተወት፤ የአየር ጠባይ ለዉጥ በዚህ ምክንያት መከሰቱ ገና ያልገባቸዉ ወገኖች መኖራቸዉ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል። የብሪታኒያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራዉን ስለአየር ጠባይ መለወጥ እየተነገረ አልፎም በተግባር የሚታዩ ለዉጦች እየተከሰቱ የአየር ጠባይ ለዉጥ መኖሩ እዉነት ለማይመስላቸዉ ወገኖች ጠንካራ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ማሳየት እንደሚያሻ ከጉባኤዉ ቀደም ብለዉ ጠቁመዋል፤

«ፀረ ለዉጥ ቡድን አለ፤ የአኗኗርም ሆነ መዋቅር ፀር የሆነ ቡድን አለ፤ ፀረ ሳይንስ የሆነ ስብስብም አለ፤ አልፎ ተርፎም መሬት የተደላደለች የሚመስለዉ ወገን አለ፤ ይሄ ሁሉ የአየር ጠባይ ለዉጥን የሚያሳይ ህያዉ መረጃ ባለበት እንዲህ የሚሉ ካሉ የሳይንሳዊ መረጃዎችን ጥንካሬ ልናሳያቸዉ ይገባል።»

Klimawandel Eisbären

የአየር ጠባይ ለዉጥ ዉጤት

በኮፐንሃገኑ ጉባኤ ከተሰሙ አዳዲስ መረጃዎች መካከል አንዱ ይህ ያለንበት ምዕተ ዓመት ዓለማችን ከመቼዉም ጊዜ በላቀ ወደጃ ሙቀት የታየባት ወቅት መሆኑን ጠቁሟል። ይህን ለመግታት ደግሞ በዚህ ጉባኤ የተሰባሰቡ ወገኖች ኃላፊነት የተሞላበት ዉሳኔ ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል። በዴንማርክ ኮፐንሃገን የተከፈተዉ ታሪካዊዉ የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ብዙ ተስፋ ተሰንቆ፤ ብዙ ተጠብቆ፤ ብዙም ታስቦበት ነዉ የተጀመረዉ። ከሁለት ዓመታት ባላነሰ ዝግጅት ታቅዶ፤ ከጉባኤዉ እንዲወጣ የሚጠበቀዉ ዉጤት የተጠበቀዉን ያህል ይሁን አይሁን ግን ቆይታዉ ሲጠናቀቅ የሚታወቅ ነዉ የሚሆነዉ። ለዝግጅትና ለድርድር በየጊዜዉ የተካሄዱት ተያያዥ ስብሰባዎች ያስገኙት ተስፋ የበለፀጉትና በኢንዱስትሪም በማደግ ላይ የሚገኙት ለዓለም ከባቢ አየር መበከል ምክንያት የሆኑ አገራት የበካይ ጋዞችን መጠን ለመቀነስ ቃል መግባታቸዉ ነዉ። ተስፋና ቃላቸዉ ምን ያህል ተግባራዊ ወደሆነ ወሳኝ ማሰሪያ ይሸጋገራል የሚለዉ ግን አሁንም ልብ ሰቃይ እንደሆነ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ