የኮፊ አናን ማስገንዘቢያ ለአውሮጳ | ኤኮኖሚ | DW | 30.01.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኮፊ አናን ማስገንዘቢያ ለአውሮጳ

የአውሮጳው ምክርቤት ለሐሳብ ነፃነት ዘንድሮ የሚሰጠውን ዛኻሮቭ-ሽልማት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለግሷል። ኅብረቱ ይህንኑ ሽልማት የለገሰው፣ የዓለሙ ድርጅት በኢራቅ መልሶ ግንባታ ለሚፈጽመው አገልግሎት ክብደት ለመስጠት፣ በተለይ ደግሞ በነሐሴ ፲፱፻፺፭ ባግዳድ ውስጥ ለተገደሉት ለዓለሙ ድርጅት ልዩ መልእክተኛ ሰርዢዎ ቪየራ ደ መሎ እና ዘጠኝ ባልደረቦቻቸው መታሰቢያ ለማኖር ነው። ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ናቸው በመላው የድርጅቱ ባልደረቦች ስም ሽልማቱን የተቀበሉት። ኮፊ አናን ይህንኑ ድርጊት መነሻ በማድረግ፣ የአውሮጳው ኅብረት ስለ ፍልሰት ጉዳይ የሚከታተለውን መርሕ ነቅፈውታል፥ በብሩክሴል፣ የአውሮጳው ምክርቤት አባላት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ሽልማቱን ለመቀበል በስብሰባው አዳራሽ ውስጥ በተገኙበት ጊዜ የጋለ አቀባበል ነበር ያደረጉላቸው። ግን ኮፊ አናን ለሐሳብ ነፃነት ክብር የሚሰጠውን ዛሃሮቭ-ሽልማት በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ከተቀበሉ በኋላ፣ በአውሮጳው ኅብረት አንፃር ያልተጠበቀ ጉልህ ሂስ ነበር ያቀረቡት። አውሮጳውያኑ በስደተኞችና በፈላስያን አንፃር በራቸውን መጠርቀም እንደማይገባቸው ነበር ዋና ፀሐፊው ሽልማቱን ሲቀበሉ ባሰሙት ዲስኩር በጥብቅ ያስገነዘቡት። በእርሳቸው አመለካከት መሠረት፤ በአውሮጳ ኅብረተሰቦች ዙሪያ ሽማግሌው ትውልድ የሚያመዝን እንደመሆኑ መጠን፣ ለኤኮኖሚውና ለማኅበራዊው ኑሮ መደገፊያ ከውጭ የበለጠ ሕጋዊ ፍልሰት መፍቀድ አስፈላጊ ይሆናል። “...............መልእክቱ ግልጽ ነው፥ ፈላስያን አውሮጳ ታስፈልጋቸዋለች፤ ግን አውሮጳም ፈላስያን ያስፈልጓታል። አንዲት ዝግ አውሮጳ ፍርድ-አጉዳይ፣ የምትደኸይ፣ የምትዳከም እና የምታረጅ ትሆናለች። አንዲት ክፍት አውሮጳ ግን በይበልጥ ፍትሐዊት፤ ርትአዊት፣ ሐብታም፣ ጠን’ካራ እና ወጣት ነው የምትሆነው--ፍልሰትን በትክክል ለመምራት ከበቃች” በማለት ነበር ዋና-ፀሐፊው ያስገነዘቡት። አናን እንዳስታወሱት፣ ባለፉት ምእተ-ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አውሮጳውያን ትውልድ ሀገሮቻቸውን እየተው ወደ ውጭ የፈለሱበት ምክንያት፣ አሁን ሰዎች ከሚደረጁት ሀገሮች ወደዚህ የሚፈልሱበት ምክንያት አቻ ነው። ፈላስያን እንደሙያኞች ብቻ በመታየት ፈንታ፣ በሚኖሩበት ኅብረተሰብእ ውስጥ እንዲዋሃዱ መደረግ አለበት። የስደተኛነት ትርጓሜ አለቅጥ እንዲጠብና የስደተኛነት መብት እንዲገደብ የሚደረግበት ሁኔታ፣ በሰው የሚደረገው ንግድና የገነዘብ አሳዳጆች ሕገወጥ አሸጋጋሪነት የፈጠሩት የሰብዓዊ መብት ቀውስ ዓለምን የሚያሳፍር መሆን አለበት ይላል የኮፊ አናን ምሬት-ቃል። የአውሮጳው ኅብረት ሚኒስትሮች ምክርቤት ወቅታዊ ሊቀመንበር--አየርላንዳዊው ውጭጉዳይ ሚንስትር ብራየን ካውን ከሽልማት አሰጣጡ ሥርዓት ቀጥለው ለአንድ ጋዜጣዊ ጉባኤ ያቀረቡት መግለጫ፥ አውሮጳ የስደተኞችን መብት እና የፍልሰትን ጉዳይ በጋራ ርምጃ ለመፍታት ጥረት ብታደርግም፣ ይኸው ርምጃ ረዥም ጊዜ ነው የሚፈጀው ይላል። የጀርመን መንግሥት በአውሮጳው ኅብረት ዙሪያ የስደተኛነት መብት ጥብቅ ግደባ የሚደረግበትን መርሕ ነው የሚከታተለው። ጀርመን ውስጥ ፍልሰትን በሚመለከተው ሕግ ረገድ ስምምነት ላይ ለመድረስ ፓርቲዎቹ እስካሁን ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። በአውሮጳው ምክርቤት ውስጥ የተወከሉት ወግአጥባቂዎቹ ፖለቲከኞች የሚያጎሉት ማስገንዘቢያ፥ ፈላስያኑ በሚነሱባቸው ሀገሮች ውስጥ የኑሮውን ሁኔታ በጉልህ አሻሽሎ ወደ ውጭ ለመፍለስ የሚያነሳሳውን ምክንያት ማስወገድ ነው የሚያስፈልገው ይላል። ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ሽልማቱን ሲቀበሉ ባሰሙት ዲስኩራቸው ያጎሉት ሌላው ማስገንዘቢያ፥ ዛሬ ከየአሥሩ ስደተኞች መካከል ሰባቱ መጠለያ የሚያገኙት በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ ነው ይላል። በእርሳቸው ስሌት መሠረት፣ ዛሬ ፈላስያን ወደ ትውልድ-ሀገራቸው የሚያስተላልፉት ገንዘብ ሐብታሞቹ እንዱስትሪ-ሀገሮች ከሚያሸጋግሩት መንግሥታዊ የልማት ርዳታ በእጥፍ ያህል የላቀ ሆኖ ነው የሚታየው። የሶቭየት መንግሥት ሃያሲ በነበሩት አንድሬ-ዛኻሮቭ ስም የተሰየው ሽልማት በተሰጠበት ወቅት የአውሮጳው ኅብረት ምክርቤት ሊቀመንበር ፓት ኮክስ ባሰሙት ንግግር፥ የተባ መ ባልደረቦች ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊው መብት የሚያበረክቱትን ከፍተኛ አገልግሎት አወድሰውታል። ባለፈው ነሐሴ ባግዳድ ውስጥ በተባ መ ማዕከላዊ መሥሪያቤት ላይ የሽብርተኞች አደጋ በተጣለበት ወቅት ፳፪ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡት ሁሉ፣ የተባ ወኪሎች ሰብዓዊውን አገልግሎት በሚፈጽሙበት ወቅት ሕይወታቸውንም እስከማጣት የሚደርሱ እንደሚሆኑ ሊቀመንበሩ ጠቅሰውታል። ሽልማቱ ለዋና ፀሐፊው በተሰጠበት ሥርዓት ላይ የሟቹ ሰርዢዮ ቪየራ ደ ሜሎ ባልተቤትም ተገኝተው ነበር። ባለፉት ዓመታት ውስጥ ይህንኑ ዛኻሮቭ-ሽልማት ያገኙት የሰብዓዊ መብት ታጋዮች በሀገራቸው ውስጥ ለእሥርቤት የተዳረጉ በመሆናቸው አሁን በሽልማቱ አሰጣጥ ሥርዓት ላይ አለመገኘታቸውን የምክርቤቱ ሊቀመንበር በከፍተኛ ቅሬታ ነበር ያስታወቁት። እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ሆነው የተጠቀሱት፣ የኩርዳውያኑን ድርጅት ደገፉ ተብለው ቱርክ ውስጥ እንደታሰሩ የሚገኙት ኩርዳዊቱ ፖለቲከኛ ሌይላ ዛና ናቸው።