የኮንጎ ፕሬዝዳንት ልጅ የሙስና ቅሌት | አፍሪቃ | DW | 10.08.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የኮንጎ ፕሬዝዳንት ልጅ የሙስና ቅሌት

የኮንጎ ፕሬዝዳንት እና ቤተሰባቸው ላለፉት አስርት ዓመታት በሙስና ሲወነጀሉ ቆይተዋል። ግሎባል ዊትነስ በተሰኘ ድርጅት አማካኝነት ይፋ የተደረገ የቅርብ ዘገባ ፕሬዝዳንቱ ካሏቸው ልጆች በዕድሜ አነስተኛው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ከሀገሪቱ መመዝበሩን አጋልጧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:27

የፕሬዝዳንቱ ልጅ 50 ሚሊዮን ዶላር መዝብሯል ተብሏል

በአፍሪካ በተለያዩ ሀገራት የፕሬዝዳንትነት መንበር የተቆናጠጡ ግለሰቦች ስልጣንን የሙጥኝ ብለው “ወንበሩን አልለቅም” ማለታቸው ብቻ አይደለም የሚያሳማቸው። ራሳቸውን ጨምሮ ልጆቻቸው ከዚያም ተሻግሮ ዘመድ አዝማዶቻቸው የሀገራቸውን አንጡራ ሀብት እንዳሻቸው እንደሚመዘብሩ ተደጋጋሚ ስሞታ ይቀርብባቸዋል። እንዲህ አይነት ትችት ከሚያስተናግዱ የአፍሪካ መሪዎች መካከል የኮንጎው ፕሬዝዳንት ዴኒስ ሳሶ ኒጌሶ አንዱ ናቸው። 

ዴኒስ ሳሶ ኒጌሶ ባለፈው ዓመት ለሀገሪቱ ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር ሙስናን መዋጋት ከሁሉ ነገር ቅድሚያ የሚሰጡት መሆኑን አስታውቀው ነበር። በሙስና በተዘፈቁ ግለሰቦች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወሰድ ሲጠብቅ የቆየው የሀገራቸው ህዝብ ትዕግስቱ መሟጠጡን እንደሚረዱም ገልጸዋል። የኢኮኖሚ ወንጀል በፈጸሙት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ፕሬዝዳንቱ “የደለቡ አሳዎች” ሲሉ የጠሯቸውንም ሆነ ተራ ዜጋውን እንደማይምርም አስጠንቅቀዋል።

“ግሎባል ዊትነስ” የተሰኘው ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ፕሬዝዳንቱ በእርግጥ ሙስናን በቁርጠኝነት መዋጋት ከፈለጉ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልጋቸው ከቤተሰቦቻቸው ይጀምሩ ባይ ነው። ዴኒስ ክርስቲል ሳሱ ኒጌሶ የተባለው የፕሬዝዳንቱ ታናሽ ልጅ በጎርጎሮሳዊው 2013 እና 2014 ዓመታት ብቻ ለቅንጡ የአኗኗር ዘይቤው 50 ሚሊዮን ዶላር እንደመዘበረ ይነገርለታል። 

ዴኒስ ክርስቲል የመንግስትን ገንዘብ እንደልብ የማግኘት ችግር የለበትም። ብሔራዊ የነዳጅ ድርጅት የተባለውን የሀገሪቱን ተቋም ከጎርጎሮሳዊው 2011 ጀምሮ በምክትል ኃላፊነት እየመራ ይገኛል። ከዓመት በኋላ በተቀላቀለው የገዢው የኮንጎ ሰራተኞች ፓርቲ አባልም ነው። ኪኪ በተሰኘ ቅጽል ስም የሚታወቀው ይህ የፕሬዝዳንቱ ልጅ በህገወጥ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ ለማድረግ ከሀገሩ ውጭ የሚገኙ ኩባንያዎችን በሽፋን ይጠቀማል የሚል ውንጀላ ይቀርብበታል።   

የምርመራ ጋዜጠኛዋ ማሪያና አብሪዩ ከግሎባል ዊትነስ ድርጅት ጋር በመተባበር የፕሬዝዳንቱ ልጅ ባደረጋቸው የገንዘብ ዝውውሮች ላይ ፍተሻ አካሂዳለች። የገንዘብ ዝውውሮቹ በርካታ ኩባንያዎችን ያሳተፈ እና ውስብስብ አሰራርን የሚከተል ነው። ከኮንጎ የሚወጣውን ገንዘብ መጀመሪያ የሚረከበው አስፔርብራስ የተባለ የብራዚል ኩባንያ ነው። ኩባንያው በአሜሪካ እና ብሪትሽ ቨርጂን አይላንድ ውስጥ ባሉት እህት ኩባንያዎቹ በኩል ገንዘቡን አውሮፓ ወደሚገኙ ኩባንያዎች ያሻግረዋል ትላለች የምርመራ ጋዜጠኛዋ። 

የእነዚህ ገንዘቦች ባለቤት ተደርጎ የተመዘገበው ጆዜ ቬጋ የተባለ ፖርቱጋላዊ የንግድ ሰው እንደሆነ የምትናገረው አብሪዩ ሆኖም የኮንትራንት ስምምነቶች የሚያመለክቱት የኮንጎው ፕሬዝደንት ልጅ የገንዘቦቹ እውነተኛ ባለቤት መሆኑን ነው ትላለች። ይህንን እንዴት እንደረሰችበት ለዶይቼ ቬለ አብራርታለች። “ያገኘነው በጆዜ ቬጋ እና በዴኒስ ክርስቲል መካከል የተፈረመን ኮንትራት ነው። በኮንጎ ዋና ከተማ ብራዛቪል ባለ የውል ጽህፈት ቤት ማህተም ተደርጎበታል። ጆዜ ቬጋ በኩባንያዎቹ ውስጥ ያለውን ባለቤትነት እና አክሲዮኖች በሙሉ ለዴኒስ ክርስቲል አስተላልፎታል። ስለዚህ እርሱ ድብቁ ባለቤት ነው። በቆጵሮስ ያለውን ምስጢራዊ ኩባንያ ባለቤት ማንነት ለማወቅ የሞከረ ማንኛውም ሰው የሚያገኘው ጆዜ ቬጋን ነው” ትላለች አብሪዩ።  

በዚህም ምክንያት በአውሮፓ ሀገራት የተቀመጡ ገንዘቦችን አመጣጣቸው ከየት እንደው ለማወቅ የሚደረገው ጥረት አዳጋች ይሆናል። የምርመራ ጋዜጠኛዋ ይህንኑ ታጠናክራለች። “አዎ። ትክክል ነው። ምክንያቱም የዴኒስ ክርስቲል ስም ተደብቋል። በአውሮፓ ባለው ህግ መሰረት በተለየ ሀገር የአክሲዮን ዝውውር ከተካሄደ ድርጅቱ ለተመሰረተበት ሀገር የማሳወቅ ግዴታ የለም። በዚህ ጉዳይ ያች ሀገር ቆጵሮስ ናት” ስትል ጋዜጠኛዋ ታብራራለች። 

አብሪዩ በህጉ ላይ ያለው ይህን መሰል ክፍተት በአስቸኳይ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ትላለች። የገንዘብ ዝውውሩን አካሄድ ለመረዳት በአውሮፓ በኩል እንዲህ አይነት ተግዳሮት ቢያጋጥምም በሌላ ወገን ያለው ግን ተጨባጭ መረጃ ተገኝቶበታል። ግሎባል ዊትነስ የተሰኘው ድርጅት ከኮንጎ ግምጃ ቤት አስፔርብራስ ለተባለው የብራዚል ኩባንያ ገንዘብ መዘዋወሩን የሚያሳዩ ሰነዶች ማግኘት ችሏል። የምርመራ ዘገባ በሚሰራበት ወቅት እንዲህ አይነት ጥርት ያለ ማስረጃ ማግኘት እምብዛም ያልተለመደ እንደሆነ አብሪዩ ትናገራለች። “የባንክ ሰነዶችን በእርግጥም የምታይበት እና ገንዘቡን በደንብ የምትከትልበት ይህን የሚያህል ማስረጃ ማግኘት በጣም እንግዳ ነገር ነው” ስትል ግርምታዋን አካፍላለች።  

ግሎባል ዊትነስ በኮንጎ ፕሬዝዳንት ቤተሰብ ላይ እንዲህ አይነት አጋላጭ መረጃዎች ሲያወጣ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ሚያዝያ ወር በፕሬዝዳንቱ ሴት ልጅ ክላዊዲያ ሳሱ ኒጌሶ ላይ ተመሳሳይ የገንዘብ ምዝበራ መረጃዎች ይፋ አድርጓል። የሀገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆነችው ክላዊዲያ 20 ሚሊዮን ዶላር የመንግስት ገንዘብን እንደመዘበረች ድርጅቱ በወቅቱ አጋልጦ ነበር። ከእዚህ ገንዘብ ውስጥ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ያህሉ የወጣው በአሜሪካ ኒውዮርክ ለሚገኘው የትራምፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ቅንጡ መኖሪያ ግዢ እንደሆነም ዘርዝሯል። እንደ ድርጅቱ ገለጻ ከሆነ ክላውዲያ ገንዘቡን ለማዘዋወር ወንድሟ ዴኒስ ክርስቲል የተጠቀመበትን መንገድ ተግባር ላይ አውላለች።

 ኮንጎን ለ35 ዓመታት በፕሬዝዳትንት የመሩት ዴኒስ ሳሶ ኒጌሶ እና ቤተሰባቸው በሌሎች ድርጅቶችም ስማቸው ከሙስና በተያያዘ ሲነሳ ቆይቷል። ትራስፓራንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፉ የሙስና አጥኚ ድርጅት የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ከአስር ዓመት በፊት ባወጣው አንድ ጥናት የየሀገራቸውን ሀብት በመመዝበር በፈረንሳይ ውስጥ በርካታ ቅንጡ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን ከገዙ አምስት የአፍሪካ መሪዎች ውስጥ ዴኒስ ሳሶ ኒጌሶ አንዱ መሆናቸውን አጋልጦ ነበር።

በፕሬዝዳንቱ እና ቤተሰባቸው ላይ የሚቀርቡ ይህን መሰል ውንጀላዎች በኮንጎ ውስጥ በየጊዜው መወያያ እንደሚሆኑ የመልካም አስተዳደር እና ሰብዓዊ መብቶች መድረክ የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሊቀመንበር ሜክሰንት አኒምባ ይናገራሉ። “በፈረንሳይ እንዲህ አይነት ቅሌት ሲጋለጥ መንግስት በበኩሉ ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ የተደረገ ሙከራ መሆኑን ይናገራል” ይላሉ። “የኮንጎን መንግስት ለመተቸት ድፍረቱ ያላቸው እንደ እኛ ያሉ ጥቂት መንግስታዊ ድርጅቶች ብቻ ናቸው” ሲሉ ያክላሉ። 

አኒምባ “በኮንጎ ሙስና አጠቃላይ ክስተት ነው ማለት ነገሩን ማሳነስ ነው። የፍትህ አካሉን፣ የትምህርት ስርዓቱን እና ምርጫን ጨምሮ በሁሉም የህዝቡ የህይወት እንቅስቃሴዎች ተንሰራፍቶ ይገኛል” ሲሉ ችግሩ ምን በሀገሪቱም ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ ያስረዳሉ። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየዓመቱ የሚያወጣው የሀገራትን የሙስና ደረጃ የሚያሳየው ዝርዝርም ይህንኑ ያረጋግጣል። መቶ ሰማንያ ሀገራትን ባካተተው ዝርዝር ኮንጎ በ165ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። 

በኮንጎ የካቶሊክ የፍትህ እና ሰላም ኮሚሽን አባል የሆኑት ብሪስ ማኮሶ ላለፉት 20 ዓመታት ሙስናን ሲዋጉ ቆይተዋል። “ሙስና በተለይ የተንሰራፋው በማዕድን ማውጣት ዘርፉ ነው” የሚሉት ማኮሶ ችግሩ “ከኮንጎም ተሻጋሮ በርካታ ሀገራትን የሚያዳርስ ነው” የሚል እምነት አላቸው። በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ኩባንያዎች እና ሀገራትን በአባልነት ያቀፈው ኤክስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ ትራንስፓረንሲ ኢኒሼቲቭ የተሰኘ ማህበር አባል የሆኑት ማኮሶ ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ችግሩን ለመፍታት እርምጃ እንዲወስድ ያሳስባሉ። “አውሮፓውያን የስደተኞችን ፍልሰት ለመግታት ትልቅ ድርጅት ማቋቋም ችለዋል። የገንዘብ ፍልሰትን ለመግታት ታዲያ እንደ ፍሮንቴክስ አይነት ድርጅት ታዲያ ለምን አናቋቁምም?” ሲሉ ይጠይቃሉ። 

ክላሪሳ ሄርማን

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic