የኮንጎ ግጭት እና የሶማሊያ ወታደሮች | አፍሪቃ | DW | 12.05.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኮንጎ ግጭት እና የሶማሊያ ወታደሮች

በሶማሊያ የተረጋጋ ማዕከለዊ መንግስት ለማቆም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተለያዩ ሙከራዎችን ፈትሿል። ከሁለት አስርት ዓመት በላይ እርስ በእርስ የሚቆራቆዙትን የጎሳ አንጃዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ለማምጣት ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም።

ከባድ ነፍጥ የታጠቀ አማፂ በኮንጎ ኪቩ

ከባድ ነፍጥ የታጠቀ አማፂ በኮንጎ ኪቩ

አሁን አሁን በሶማሊያ ከጎሳዎቹ ግጭትም በላይ ዓለምን በማሳሳብ ላይ ያለው የእስላማዊ ፅንፈኛ ቡድኖች እና የባህር ላይ ሽፍቶች እንቅስቃሴ ሆኗል። ይህን በሶማሊያ የሰፈነ አደጋ ለማስወገድ በአውሮጳውያን ፊታውራሪነት እና የገንዘብ ፈሰስ ኡጋንዳ ውስጥ የሶማሊያ ወታደሮች ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ወታደሮቹ ሐሙስ፣ ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. በይፋ መመረቃቸውን የገለፁት የአውሮጳ ኅብረት የሶማሊያ ስልጠና ተልዕኮ በምህፃሩ EUTM አዛዥ የሆኑት አየርላንዳዊው ኮሎኔል ማይክል ቤሪ ናቸው።

፩ ድምፅ ኮሎኔል ማይክል ቤሪ፥

«ዛሬ በማሰልጠኛ ጣቢያው ውስጥ የሰለጠኑት የሶማሊያ ወታደሮች የምረቃ ቀን ነው። ስድስት መቶ ሶስት ወታደሮች  ናቸው የተመረቁት። ወታደሮቹ የተመረቁት የተሟላ መዋቅር ባለው  አራት ዘርፎች ነው።ይኸውም፥ ሻምበሎች፣ ከሻምበል በታች የሚገኙ ባለማዕረጎች፣ ሌሎች ባለ ማዕረጎች እና የበታች ወታደሮች ያሉበት ነው። በአጠቃላይ በሻምበል የሚመራ መዋቅር ነው። »

ከአሰልጣኞቹ አንዱ ጀርመናዊ ኮሎኔል

ከአሰልጣኞቹ አንዱ ጀርመናዊ ኮሎኔል

ለስድስት ወራት በዘለቀው ስልጠና ከተገኙት 608 ሰልጣኞች መካከል የ 40 ዓመቷ ፋጡማ ኑርን ጨምሮ፤ ለምረቃ የበቁት 603ቶቹ ነበሩ። የምዕራቡ ዓለም ይህን ስልጠና እውን ለማድረግ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን እንዳፈሰሰ ተዘግቧል።  ስልጠናው በዋናነት ያተኮረው በዜግነት ጉዳይ፣ በሴቶች መብት እንዲሁም ፆታን መሰረት አድርጎ የሚነሱ በደሎችን ማቆም በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ መሆኑን አዛዡ ገልፀዋል። አክለውም የመጀመሪያ ርዳታ አሰጣጥ፣ የፈንጂ ማምከን እና በጦርነት ወቅት የግንኙነት መስመር መዘርጋትን የሚመለከቱ ትምህርቶች በስልጠናው እንደተካተቱ ጠቁመዋል።

፪  ድምፅ ኮሎኔል ማይክል ቤሪ፥

«የዛሬ ምሩቃን በርካታ አዳዲስ ክህሎቶችን አዳብረዋል። በእርግጥ ወታደሮች ናቸው፤ ሆኖም እኔ እስከማውቀው ድረስ  በፍልሚያ ወቅት የመጀመሪያ ርዳታ የማድረግ  እውቀትንም ቀስመዋል። በጣም ወሳኝ ሊሆን የሚችለው ነገር ደግሞ፤ በተለይ የሶማሊያ ዜግነትን ጨምሮ፤  በፆታ፣ በስደተኞች እና በመሳሰሉት የሠብዓዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕግ መማራቸው ነው።»

በፈንጂ የነጎደ መኪና ሞቃዲሾ ውስጥ

በፈንጂ የነጎደ መኪና ሞቃዲሾ ውስጥ

ስልጠናውን ኡጋንዳ ውስጥ ራቅ ብሎ በሚገኘው የቢሃንጋ መንደር ውስጥ የሰጡት ከ12 የተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት የተውጣጡ 60 አሰልጣኞች እንደሆኑ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።  ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶ በዚህ ልዩ ስልጠና የዘንድሮዎቹን ምሩቃን ጨምሮ 2403 የሶማሊያ ወታደሮች መመረቃቸው ታውቋል። በእርግጥ የተወሰኑ ሰልጣኞች ከዚህ ቀደም ስልጠናውን ጨርሰው ወደ ሶማሊያ ሲመለሱ አልሸባብን የተቀላቀሉ እንደነበሩም ይታወቃል። አየርላንዳዊው አዛዥ የዘንድሮው ሰልጣኝ ወታደሮች በስልጠናው ሂደት ለውጥ አምጥተዋል ሲሉ ተናግረዋል።

፫ድምፅ ኮሎኔል ማይክል ቤሪ፥

«በሂደት ለውጥ አምጥተዋል። ለዚህ ቀን በመድረሳቸው በጣም ደስ ብሎኛል። እነዚህ ሰልጣኞች በቅርቡ ወደ ሞቃዲሾ ሶማሊያ ይመለሳሉ።»

ኡጋንዳ ውስጥ የሰለጠኑት የሶማሊያ ወታደሮች የስልጠናው ተልዕኮ አነስ ያለ ቢሆንም ዘመናዊ ጦር በሶማሊያ ለመገንባት የሚኖረው ድርሻ ግን ላቅ ያለ እንደሆነ ጠቁመዋል። አያይዘውም ከዓመት በፊት አብዛኛውን የሶማሊያ ግዛት ተቆጣጥሮ የነበረው አል ሸባብ በውጭ ሀይሎች ድጋፍ እየተዳከመ በመምጣቱ ብዙም እንደማያሳስባቸው ጠቅሰዋል። ይሁንና ግና ከትናንት በስተያ ከኢትዮጵያ ድንበር 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የደቡብ ሶማሊያ ግዛት ሁዱር ውስጥ በኢትዮጵያ ወታደሮች እና በአልሸባብ መካከል ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።  የኢትዮጵያ ወታደሮች እና የሶማሊያ መንግስት ጦር 17 የአል ሸባብ ተዋጊዎችን እንደገደሉ ሲገልፁ፤ አልሸባብ በበኩሉ 7 ወታደሮችን ገድያለሁ ብሏል። በሁለቱም ወገኖች የተጠቀሰውን የጉዳት መጠን ያጣራ ገለልተኛ ወገን እንደሌለ ግን የዜና አውታሩ አክሎ ጠቅሷል።  በሶማሊያ የኢትዮጵያን ጦር ጨምሮ የኬንያ፣ የቡሩንዲ እና የዩጋንዳ ሃይላት እንደሚገኙ ይታወቃል። ዩጋንዳ ውስጥ ሰልጥነው የተመረቁት 603ቱ  የሶማሊያ ወታደሮች ደግሞ በቅርቡ ወደ ሶማሊያ ይመለሳሉ።

የሶማሊያው አል ሸባብ

የሶማሊያው አል ሸባብ

አሁን ደግሞ በምስራቅ ኮንጎ በአማፂያን እና በመንግስት ወታደሮች መካከል ስለተቀሰቀሰው ግጭት የዶቼቬለው አድሪያን ኪርሽ ያቀረበውን ዘገባ እንደሚከተለው አቀናብረነዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እና የአማፂያን ግጭት ዲሞክራቲክ ሪፐብሎክ ኮንጎን ካለፈው ወር አንስቶ መፈናፈኛ አሳጥቷት ቆይቷል። ግጭቱ በርካቶችን ወደ ጎረቤት ሩዋንዳ እንዲሰደዱ አስገድዷቸዋል። ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ድንበር ላይ የሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ከአቅሙ በላይ በስደተኞች ተጨናንቋል። ንካሚራ የተሰኘው ይኸው ጣቢያ 2,500 ስደተኞችን የማስተናገድ አቅም ቢኖረው፤ በአሁኑ ወቅት በጣቢያው ከእጥፍ በላይ የሆኑ ስደተኞች እንደሚገኙ ታውቋል። የሸቀጦች አቅርቦት በማነሱም በርካታ ስደተኞች ለችግር መዳረጋቸውን አንዲት ስደተኛ እንዲህ ይገልፃሉ።

ድምፅ ስደተኛ (ሴት)

«፬ ኪሎ ቦሎቄ እና ፲፪ ኪሎ በቆሎ ደርሶኛል። ከዚያ ውስጥ የተወሰነውን በማገዶ እንጨት እቀይረዋልሁ፤ አለበለዚያ የሚበላ ነገር ማብሰል አልችልም። ጨው የሚባል ነገር የለም፤ ያለጨው ነው የምንመገበው። እኛ እዚህ ከደረስንበት ጊዜ አንስቶ የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው እየናረ ነው።»

እንደተባበሩት መንግስታት ገለፃ ከሆነ፤ በሰሜን ኪቩ ከሚገኘው ቀዬያቸው በተለይ ከማሲሲ የተፈናቀሉ ስደተኞች ቁጥር 20,000 ደርሷል። ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ታዲያ ሰበቡ የቀድሞው የጦር ባላባት ቦስኮ ንታጋንዳን ተከትለው ነፍጥ ባነሱ ሚሊሺያዎች እና በመንግስት ወታደሮች እንዲሁም ራሳቸውን ባዲስ መልክ ባደራጁ ሌሎች ሚሊሺያዎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እንደሆነ ተጠቅሷል። ቦስኮ ንታጋንዳ ህፃናት ወታደሮችን በመመልመላቸው በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው ናቸው። ግጭቱ የጠናበት የሰሜን ኪቩ ሀገረ-ገዥ ጁሊያን ፓሉኩ።

የቀድሞው የጦር ባላባት ቦስኮ ንታጋንዳ

የቀድሞው የጦር ባላባት ቦስኮ ንታጋንዳ

ድምፅ ጁሊያ ፓሉካ

«በአሁኑ ወቅት ማሲሲ ዉስጥ ለተከሰተው ነገር ሁሉ ተጠያቂው ቦስኮ ንታጋንዳ ነው ማለት እንችላለን። በመንግስት እጅ ሲገባ ለሰራው ነገር ሁሉ ዋጋውን ተጠያቂ መሆን አለበት።»

ቦስኮ ንታጋንዳ ከተለያዩ አማፂያን ጋር ሆነው ሲዋጉ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ናቸው።የተወለዱት ሩዋንዳ ውስጥ ቢሆንም በሀገራቸው ውስጥ ቱትሲዎች ለፍጅት ሲዳረጉ በወጣትነታቸው ከሩዋንዳ ይሸሻሉ። እናም አሁን የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት በሆኑት በቱትሲው  ፖል ካጋሜ የሚመራው የሩዋንዳ አርበኖች ግንባር ውስጥ አባል ይሆናሉ። ቆየት ብለው ደግሞ በቶማስ ሉባንጋ የሚመራው የኮንጎ አርበኞች ኅብረትን ነፍጣቸውን እንዳነገቡ ይቀላቀላሉ። ይህ ኅብረት በመቶዎች ለሚቆጠሩ የጎሳ ጭፍጨፋዎች፣ ለሠብዓዊ መብት ረገጣ እና ለዜጎች ስቅየት ተጠያቂ እንደሆነ ይነገራል። መሪው ቶማስ ሉባንጋን ጨምሮ ንታጋንዳ ከዓመታት በፊት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸዋል። ንታጋንዳ እሳቸውም ሆኑ ሉባንጋ ከደሙ ንፁህ እንደሆኑ ነበር ባንድ ወቅት ለዶቼ ቬለ የገለፁት።

ህፃናት ወታደሮች በኮንጎ

ህፃናት ወታደሮች በኮንጎ

ድምፅ ቦስኮ ንታጋንዳ

«እኔ በአመራር ደረጃ ከሉባንጋ በአራተኛ ደረጃ ላይ የምገኝ ብሆንም ላደረገው ነገር እሱን በቀጥታ ከመጠየቅ ይልቅ ለምን እኔን እንደሚከታተሉኝ  ነው የማይገባኝ። በእርግጥ መጥፎ ነገር ተከስቷል ብዬ ልናገር አልችልም። ጓደኛዬ ያደረገው  ምንም መጥፎ ነገር የለም፤ ራሱን ነበር የተከላከለዉ። ሆኖም እንደሚመስለኝ አመራር ለነበረበት የጦር ሠራዊት ሃላፊነቱን የሚወስደው እሱ ነው። በስልጣን ላይ ስላሉት ፖለቲከኞችም ሃላፊነት ይኖርበታል።»

ንታጋንዳ ጨካኝ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ላውራንት ንኩንዳን ከሶስት ዓመታት በፊት CNDP ከተሰኘው የብሔራዎ ኮንግሬሱ ጦር ካባረሩ በኋላ CNDP ን  ከኮንጎ ጦር ጋር መቀላቀላቸው ይታወቃል።  እናም ምንም እንኳን በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለእስር ቢፈለጉም በቅይጡ ጦር ውስጥ የጀኔራልነት ማዕረግን ተጎናፅፈው ቆይተዋል። ይህ የመዋሀድ ሂደት በራሱ አነጋጋሪ ነበር ሲሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግጭቶችን የሚያጠናው ቡድን ማለትም Interantional crisis Group የመካከለኛው አፍሪቃ ሃላፊ ቲየሪ ቪርኮሎ  ይተቻሉ።

ድምፅ ቲየሪ ቪርኮሎን

«የመዋሃዱ ሂደት ተጨናግፏል።  ሂደቱ የተስተጓጎለው ደግሞ ከCNDP ጋር ብቻ ሳይሆን ከበርካታ ነፍጥ ያነገቡ ቡድናትም ጭምር ነው ። ሚሊሺያዎቹን የጠቀለለው የኮንጎ ጦር ሳይሆን በተቃራኒው ሚሊሺያዎቹ ናቸው ጦሩን የተቆጣጠሩት።»

የኮንጎ የጦር ወንጀለኞች በጀርመን ፍርድ ቤት

የኮንጎ የጦር ወንጀለኞች በጀርመን ፍርድ ቤት

ንታጋንዳ ጄኔራል ተሰኝተው ከተዋሃዱበት የኮንጎ ጦር ውስጥ የቀድሞ  የ CNDP አማፂያንን ይዘው የሸፈቱት የዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ በመፍራት እንደሆነ ይነገራል። ከትናንት ወዲያ እና ትናንት በዚሁ የሰሜን ኪቩ አውራጃ ውስጥ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወታደሮች እና በአማፂያኑ መካከል ከባድ ውጊያ መካሄዱ ተገልጿል። ከኮንጎ ጦር የሸፈቱት ሌሎች አማጺያን ደግሞ አዲስ ግንባር መመስረታቸውን አውጀዋል። አማፂያኑ የቀድሞ የ CNDP አባላት ስንሆን አሁን የምንመራውም  በኮሎኔል ሱልጣኒ ማኬንጋ ነው ብለዋል። ከዛሬ ሶስት ዓመታት በፊት በቦስኮ ንታጋንዳ ስር ሆነን የኮንጎ ጦርን ስንቀየጥ የተፈረመው የሠላም ውል ሙሉ ለሙሉ ይተግበር ሲሉም ጠይቀዋል። ቦስኮ ንታጋንዳ በኮንጎ መንግስት እና በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚፈለጉ ናቸው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 12.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14u8X
 • ቀን 12.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14u8X