የኮንጎ ጉዞ ወዴት ይሆን? | የጋዜጦች አምድ | DW | 30.12.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የኮንጎ ጉዞ ወዴት ይሆን?

የያዝነዉ አመት ላለፉት አምስት አመታት ከተካሄደባት የእርስ በርስ ጦርነት ወጥታ በዲሞክራቲክ ኮንጎ አንፃራዊ ሰላም የሚሰፍንበትን ስምምነት ያስገኘ የተሻለ አመት ተብሎ ሳያልቅ ሁኔታዎች እየተለወጡ ነዉ።

የፈረንጆቹ 2004 አ.ም. ከማለቁ በፊት የሰላም ዉሉን በአደገኛ መንገድ የሚያፈርስ ሁኔታ ተከስቷል።
ባለፉት ሳምንታት በዲሞክራቲክ ኮንጎና በጎረቤቷ ሩዋንዳ መካከል የነገሰዉ ዉጥረት የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ በኮንጎ ሸምቀዋል ያሏቸዉን የሁቱ ጎሳ ሚሊሺያዎች ትጥቅ አስፈታለሁ በሚል ሰበብ ጦራቸዉን ወደጎረቤቲቱ አገር በማስገባታቸዉ እየከረረ ሄዷል።
ካጋሜ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ሲሉ እንደነበረዉ የሽምቅ ተዋጊዎቹ በአገራቸዉ ላለዉ ደህንነት አደጋ መሆናቸዉን በድጋሚ በመግለፅ ነዉ ጦራቸዉን ወደኮንጎ የላኩት።
ከሁለት አመት በፊት ሩዋንዳ የተባበሩት መንግስታትና የኮንጎ መንግስት ኃይሎች የሁቱ ሚሊሻዎችን ትጥቅ እንዲያስፈቱላት በመጠየቅ ኮንጎ ዉስጥ ያላትን ጦር ለማስወጣት ተስማምታ ነበር።
ተንታኞች እንደሚሉት በኮንጎ የመሸገዉ የሩዋንዳ ዲሞክራሲያዊ ነፃ አዉጪ ጦር በመባል የሚታወቀዉ ዋነኛዉ የሁቱ ሽምቅ ተዋጊ ቡድን ለሩዋንዳ ያንያህል የሚያሰጋ ወታደራዊ ሃይል አይደለም።
በቅርቡ የሩዋንዳ መንግስት ተሞከረብኝ ያለዉ የጥቃት እርምጃ ምናልባትም ስጋቱን የሚያባብሰዉ ሊሆን ይችላል።ሆኖም ከተባበሩት መንግስታት የወጡ መረጃዎች እንደጠቆሙት የተባለዉን ጥቃት የሚደግፍ ተጨባጭ ማስረጃ አልተገኘም።
ሩዋንዳ በምስራቅ ኮንጎ በኩል ተቃጣብኝ የምትለዉ የሁቱ ሚሊሻዎች ጥቃት ምናልባትም በስፍራዉ በብዛት የሚገኘዉን የአገሪቱን የማእድን ሃብት ለመቀራመት የታለመ ነዉ በማለት የሚከሷትም በርካቶች ናቸዉ።
ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ የተባበሩት መንግስታት ተቆጣጣሪ ቡድን ሩዋንዳና ኡጋንዳን የኮንጎን አማፅያን በመደገፍና በህገወጥ መንገድ ከኮንጎ የማእድናት ዘረፋ እንደሚያካሂዱ አጋልጧቸዉ ነበር።
ባለፈዉ ሰሞን የሩዋንዳ ወታደሮች ኮንጎ መግባታቸዉ በተነገረ ወቅት ካጋሜ እዉነታዉን በማድበስበስ የሁቱ ሚሊሻዎችን ትጥቅ የማስፈታቱትን ተግባር ለተባበሩት መንግስታት የተዉ መሆናቸዉን ቢገልፁም ወታደሮቻቸዉ ድንበር አልፈዉ መግባታቸዉን ዘገባዎች ይፋ አድርገዋል።
በተጨማሪም ኮንጎ ሩዋንዳ ለኮንጎ ተቃዋሚ ወታደሮች መሳሪያ በማስታጠቅ በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ከመንግስት ጋር ግጭት እንዲፈጥሩ አድርጋለች በማለት ተጨማሪ ክስ አቅርባለች።
እነዚህ ተቃዋሚ ወታደሮች መቀመጫዉን ጎማ በተባለችዉ ከተማ ባደረገዉና በሩዋንዳ እየተደገፈ ግጭት በሚፈጥረዉ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ አማፂ ቡድን ዉስጥ የነበሩ መሆናቸዉን ነዉ ኮንጎ የምትገልፀዉ።
ከሁለት አመት በፊት በተደረሰዉ ስምምነት መሰረትም አብዛኛዎቹ የዚህ ቡድን አባላት በኮንጎ ብሄራዊ ጦር ኃይል ዉስጥ ገብተዋል። ሆኖም በኮንጎ እዉነተኛ ህብረትን የመፍጠሩ ነገር ህልም ሆኖ ቀርቷል።
ባለፈዉ ሰኔ የአማፅያን ቡድኑ ኮማንደር ሎረንት ናኩንዳ ምስራቃዊዋን ከተማ ቡካቩን የኮንጎ ቱትሲዎችን ከግድያ ለመከላከል ነዉ በሚል ሰበብ በቁጥጥራቸዉ ስር አድርገዋል።
የተባበሩት መንግስታት ዘግየት ብሎ እንደገለፀዉ ግን ናኩንዳ ያሉትን እልቂት የሚደግፍ መረጃ አላገኘም።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልም እንደገለፀዉ በሰሜን ኪቩ ሁኔታዎች የተባባሱ ሲሆን ጎማ የሚገኘዉና በሩዋንዳ የሚደገፈዉ ይህ ቡድን ክፍለ ሃገሩን እንደከለላ እየተጠቀመበት ነዉ።
በአካባቢዉ ያለዉ የፓለቲካና ወታደራዊ እንቅስቃሴ የአገሪቱን የሽግግር መንግስት እንደልቡ ስልጣኑን በዚህኛዉ የአገሪቱ ክፍል እንዳይጠቀም እንዳገደዉም ነዉ አምነስቲ የገለፀዉ።
በመሆኑም አማፂዉ ቡድን በሰፈረባቸዉ በነዚህ አካባቢዎች የሰብአዊ መብት ረገጣ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈፀመ ነዉ።
የተባበሩት መንግስታት በቅርቡ በወሰደዉ እርምጃ በምስራቃዊ ኪቩ አካባቢ መንግስትንና የቀድሞ የአማፂ ብድኑን ወታደሮች በመለየት በመካከል 10 ኪሎ ሜትር የሚሆን ነፃ ቀጣና ፈጥሯል።
ይህ በተባበሩት መንግስታት የተፈጠረዉ ነፃ ወረዳ ጦርነቱን በማስቆም በአካባቢዉ ለተፈናቀሉት ሰላማዊ ዜጎች እርዳታ ለማድረስ ያስችላል ተብሎ ተሰፋ ተጥሎበታል።
እስከዛሬ በኮንጎ በተፈጠረዉ ችግር ሳቢያ ከደረሰዉ ከፍተኛ መፈናቀል በተጨማሪ በቅርቡ በተቀሰቀሰዉ ዉጊያም በሺ የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ለስደት ተዳርገዋል።
ይህ አይነቱ ቀዉስ በመጪዉ ሰኔ ወር በኮንጎ ይካሄዳል ተብሎ የታሰበዉን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የማይታለም አድርጎታል።
ምርጫዉ የሽግግር መንግስቱን በመተካት ከተቃዋሚዎች፤ ከአማፅያን እንዲሁም አሁን ካለዉ የመንግስት አካል በተዉጣጡ ተመራጮች የተዋቀረ በአገሪቱ ቋሚ መንግስትን የመተካት ሂደት ይሆናል ተብሎ ታስቦ ነበር።
አሁን ከተፈጠረዉ የሰላም መደፍረስ ተነስቶ ግን ኮንጎ ወዴት እየሄደች እንደሆነ ለጊዜዉ መተንበይ አስቸጋሪ ይሆናል።