የኮንጎ ዴሞክራቲክ ጠቅላላ ምርጫ | የጋዜጦች አምድ | DW | 28.01.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ጠቅላላ ምርጫ

ጠቅላላው ምርጫ እና ማከራከር የያዘው የምዝገባ ጥያቄ

በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ በቅርቡ እንዲካሄድ ለታቀደው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮችና ተመራጮች ምዝገባ እንደገና እንዲከፈት ዋነኛው የተቃቃሚ ቡድን፡ የዴሞክራሲና ማኅበራዊ መሻሻል ኅብረት ፓርቲ - ዩ ዲ ፒ ኤስ ያቀረበውን ጥያቄ ነፃው አስመራጭ ኮሚስዮን ውድቅ አድርጎታል። የሽግግሩ መንግሥት ሥልጣን ዘመን እስከሚያበቃበት እአአ እስከ ሰኔ ሠላሣ ድረስ ምክር ቤታዊውና ፕሬዚደንታዊው ምርጫ እንዲጠናቀቅ በተወሰነው መሠረት ምርጫው የፊታችን መጋቢት፡ ሚያዝያ እና በግንቦት ወር ውስጥ ይካሄዳል። ግዙፉን የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ለመቆጣጠር ሲባል በመንግሥቱ ጦር ኃይላትና በተለያዩ ያማፅያን ቡድኖች መካከል አምስት ዓመት ሙሉ የተካሄደውን የርስበርስ ጦርነት ባበቃውና ታህሳስ 2002 ዓም በተፈረመው የሰላም ስምምነት ነበር የሽግግሩ መንግሥት የተቋቋመው።
ዩ ዲ ፒ ኤስ እአአ በ 2006 ዓም በሚካሄደው ምርጫ ላይ እና ብዙ ያልተስተካከለ አሠራር ታይቶበታል ባለው ባለፈው ዓመት በተካሄደው የመራጮች ምዝገባ ላይ ሕዝቡ፡ ብሎም ደጋፊዎቹ እንዳይሳተፍ ጥሪ ማስተላለፉ አይዘነጋም። ይሁን እንጂ፡ የፓርቲው መሪ ኤትየን ቺሴኬዲ ከጥቂት ጊዜ በፊት እንዳስታወቁት፡ አዲሱ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ባለፈው ታህሳስ ወር በሬፈረንደም የፀደቀበትን ድርጊት በመደገፍ፡ ፓርቲያቸው በጠቅላላው ምርጫ ለመወዳደር ወስኖዋል። ዩ ዲ ፒ ኤስ በምርጫው ላይ ለሚሳተፍበት ድርጊት ሕገ መንግሥቱ ለሬፈርደም የሚቀርብበትንና የሚፀድቅበትን ሁኔታ እንደ ቅድመ ግዴታ አቅርቦ ነበር። ይኸው የፓርቲው የውሳኔ ለውጥ ነበር የዩ ዲ ፒ ኤስ ባለሥልጣናትን የፓርቲው ደጋፊዎች ይመዘገቡ ዘንድ የምዝገባ ማዕከላት እንደገና በመላይቱ ሀገር የሚከፈቱበትን ጥያቄ ያስነሳው። አስመራጩ ኮሚስዮን ግን ምዝገባው በጊዜ እጥረት የተነሳ እንደገና ሊጀመር እንደማይችል በማስታወቅ፡ የጠቅላላ የምዕራብ አውሮጳን ያህል የቆዳ ስፋት ያላት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ መሠረተ ልማት ያን ያህል ያልተሻሻለ በመሆኑ ባለፈው ዓመት ሀያ አራት ሚልዮን መራጭ ሕዝብ የተመዘገበበት ሂደት ምን ያህል ችግር እንዳጋጠመው ለማስረዳት ሞክሮዋል። ይሁን እንጂ፡ በተወዳዳሪነት መቅረብ የሚሹ የሀገሪቱን ዜጎች መብት ላለመንፈግ ሲባል እስካሁን ስማቸውን ያልሰጡ የዩ ዲ ፒ ኤስ ዕጩዎች ሊመገቡ እንደሚችሉ አስመራጩ ኮሚስዮን አስታውቋል። የመራጮች ዳግም ምዝገባ እንዲካሄድ ፓርቲየው ያቀረበውን ጥያቄ ኮሚስዮኑ ውድቅ በማድረጉ ቅር የተሰኙት ቺሴኬዲ፡ አስመራጩ ኮሚስዮን የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት ዦሴፍ ካቢላ የሚመሩትን የመልሶ ግንባታና የዴሞክራሲ ሕዝባዊ ፓርቲን ለመደገፍ ሲል በውሳኔው ዩ ዲ ፒ ኤስን ከምርጫው ለማግለል ሞክሮዋል በማለት ወቀሳ አሰምተዋል። የአስመራጩን ኮሚስዮን ውሳኔን ብዙዎች ቢደግፉትም፡ የተቃወሙትም ጥቂቶች እንዳልሆኑ የሕዝብ አስተያየት መዘርዝሮች አሳይተዋል። ዩ ዲ ፒ ኤስ ደጋፊዎች ቢያንስ ባንዳንድ ከተሞች የምዝገባ ዕድል እንዲሰጣቸው ነውየኮሚስዮኑን ውሳኔ የተቃወሙት ወገኖች የሚጠይቁት። ዩ ዲ ፒ ኤስ የተከተለው ፖሊሲ ኃላፊነት የጎደለው መሆኑን የገለፁ ሌሎች የሀገሪቱ ዜጎች ደግሞ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ውስጥ ሰላም ለማረጋገጥና የሽግግሩን መንግሥት የሥልጣን ዘመን በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ከተፈለገ ሁሉም የሀገሪቱ መራጭ ሕዝብ በመፃዒው ጠቅላላ ምርጫ መሳተፍ እንዳለበት አሳስበዋል።
የፊታችን መጋቢትና ሚያዝያ በሀገሪቱ የከተሞች አስተዳደርና ያካባቢ ምክር ቤታዊ ምርጫዎች፡ በሚያዝያና በግንቦት ወር ደግሞ የፕሬዚደንታዊው ምርጫ እንዲካሄድና አዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ሆኖ የሚመረጠው ግለሰብ የፊታችን ሰኔ አጋማሽ ሥልጣኑን እንዲረከብ ተወስኖዋል።
የሰባ ሦስት ዓመቱ የዩ ዲ ፒ ኤስ መሪ ኤትየን ቺሴኬዲ እአአ በ 1997 ዓም ከሥልጣን በተወገዱት የቀድሞው ፕሬዚደንት ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ አመራር ወቅት በጠቅላይ ሚንስትርነት ቢያገለግሉም፡ ወደመጨረሻው የሥልጣናቸው ዘመን በሞቡቱ ሴሴ ሴኮ አንፃር ግልፁን ሒስ በመሰንዘራቸው ከሥልጣናቸው ተባረዋል። ቺሴኬዲ ሞቡቱን አስወግደው ሥልጣኑን በያዙት እና እአአ በ 2001 ዓም በተገደሉት ሎውሮ ካቢላ መንግሥት፡ እንዲሁም በተኩዋቸው ልጃቸው ዦሴፍ ካቢላ መንግሥትም አንፃር ቢሆን ሒስ ከመሰንዘር ወደ ኋላ ብለው እንደማያውቁ ነው የሚነገረው።
ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ውስጥ በይፋ ሰላም መውረዱ ቢገለፅም፡ ምሥራቃዊው የሀገሪቱ ከፊል ጊዚያዊ ሁኔታ አሁንም አስተማማኝ አይደለም። በዚችው ሀገር ውስጥ ያሉትን ዓማፅያን የጦር መሣሪያ ትጥቅ ማስፈታት እንዲረዳ የተሠማራውና ትልቁ መሆኑ የሚነገርለት የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ እንኳን አሁንም ተልዕኮውን በመወጣቱ ረገድ ግዙፍ ችግር እንዳለበት ተገልፆዋል። ባለፈው ሰኞ እንኳን ስምንት አባላቱ በምሥራቃዊው ኮንጎ ከሚንቀሳቃሱ ዓማፅያን ጋር በተፈጠረ ግጭት ሲገደሉበት አምስት ቆስለውበታል፤ ወደ አሥር ሺህ የሚሆን ያካባቢው ሕዝብም ቤት ንብረቱን ለቆ መሰደድ ተገዶዋል። በመሆኑም የአውሮጳ ኅብረት ለተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ የጦር ድጋፍ እንዲልክ የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ባቀረበው ጥሪ የተነሳ የአውሮጳ ኅብረት ርዳታውን የሚልክበትን ጉዳይ የሚያጣራ አንድ ቡድን ወደ ኮንጎ ለመላክ ወስኖዋል። የአውሮጳ ኅብረት በኮንጎ ለተሠማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ እአአ በ 2003 ዓም አርቴሚስ በሚል መጠሪያ የተጠራ በፈረንሣይ የተመራ አንድ የጦር ቡድን በርዳታ መላኩ የሚታወስ ነው።