የኮንጎው ጦርነትና የዓለም ኅብረተሰብ ቸልታ | የጋዜጦች አምድ | DW | 21.12.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የኮንጎው ጦርነትና የዓለም ኅብረተሰብ ቸልታ

በዴሞክራታዊት ሬፑብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ከፊል በመንግሥት ወታደሮችና በአማጽያኑ መካከል እንደገና ውጊያው ገንፍሏል። በሺህ የሚቆጠሩ የክፍለ-ሀገር ሰሜን-ኪቩ ነዋሪዎች አሁን በሽሽት ላይ ነው የሚገኙት።

በፕሬዚደንት ዦሴፍ ካቢላ የሚመራው የኮንጎው መንግሥት፥ ጎረቤት-ሀገር ሩዋንዳ በምሥራቅ-ኮንጎ ፍልሚያ ጀመረች በማለት ስሞታ አቅርቧል። ሩዋንዳ በስምንት ዓመታት ውስጥ ለሦሥተኛ ጊዜ ኮንጎን መውረሩዋ ነው። ብዙ ደም የሚያንጣልለው ጦርነት እየተባባሰ በሄደበት ባሁኑ ወቅት የውጭው ርዳታ የተጓደደ ሆኖ ነው የሚታየው።

“በታላላቆቹ ሐይቆች አካባቢ ሰላምን የሚፈልግ፥ ጦርነት ማካሄድ አለበት” ብለው ነበር የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ከአንድ ወር በፊት ለተባ መ ዲፕሎማቶች ባሰሙት ንግግር። በዚህ አኳኋን፣ ጦረኛው ካጋሜ አሁን ቃላትን በተግባር ለውጠው እንደገና ጦርነቱን መቀስቀሳቸው ነው። እኒሁ የቁንጽል ሀገር ሩዋንዳ መሪ በስምንት ዓመታት ውስጥ ለ፫ኛ ጊዜ ወታደሮቻቸውን ወደ ኮንጎ ለማዝመት እንደተዘጋጁ የዓለም ኅብረተሰብ አስቀድሞም መገመትና ማወቅ ነበረበት።

ሩዋንዳ ከስድስት ዓመታት በፊት በምሥራቅ ኮንጎ ሁለተኛውን ወረራ የከፈተችበት ድርጊት በጠቅላላው ስድስት ሀገሮች በጦርነቱ እንዲሳተፉ አደረገ፥ ከ፫ እስከ ፬ ሚሊዮን የሚገመቱ ኮንጎሌዎችን አረገፈ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲህ የአፍሪቃውን አህጉር ያህል ሕዝብ የተጨፈጨፈበት ቦታ የለም። እርስበርሱ ጦርነት በይፋ ቆሞም ሳለ ሴቶችና ሕጻናት በግዳጅ የተደፈሩበት የግፍ ማዕበል፣ በየቀኑ ፩ሺ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያጡበት፣ ሌላ ቦታ አይደለም--ያው ያፍሪቃው አህጉር ነው። አሁን ታዲያ ካጋሜ ኮንጎ ውስጥ እንደገና ያቀጣጠሉት የባሩድ ጋን ቀጥሎ ሊፈነዳ ይችላል። ውጊያው አሁን በሁቱ እና በቱትሲ፣ ወይም በሄማ እና በሌንዱ መካከል ብቻ አይደለም የሚካሄደው--ከቁጥጥር ውጭ፣ መረንለቀቅ የሚሆንበት ዝንባሌ ነው የሚታየው።

የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ኮንጎ ውስጥ ምን እንደሚፈልጉ አስቀድሞም መታወቅ ነበረበት። ካጋሜ ሩዋንዳ ውስጥ ከ፰፻ሺ የሚበልጡ ቱትሲዎች ለተጨፈጨፉበት ድርጊት ተጠያቂ የሚሆኑትን ሁቱ-ታጣቂዎች ለመውጋት መነሳሳታቸው የታወቀ ነገር ነው፣ ግን ይኸው ምክንያት ለይምሰል ያህል ነው የሚቀርበው፥፥ዋናው ምክንያት ሌላ ነው። የሩዋንዳው መሪ አሁን በተለይም በምሥራቅ ኮንጎ ተጽእኖአቸውን ለመጫን እና ለማስፋፋት ነው የሚሹት። የኮንጎ ድልብ ሐብት ያጓጓል፣ ይጋብዛል፥ የቆላ እንጨት፣ ወርቅ፣ አልማዝና ሌሎችም ክቡር ድንጋዮች ሞልተዋል። ካጋሜ የኮንጎን መመሰቃቀል ነው ቀዳሚ ግብ ያደረጉት።

እንግዲህ ይህ ሁሉ ሲሆን የዓለም ኅብረተሰብእ ምን አድርጓል? ምን ያደርጋል? የዓለሙ ድርጅት ሁሉ ነገር ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸውን ፲ሺ ወታደሮች ኮንጎ ውስጥ አሰማርቷል፥ ግን ራሱን ጨርሶ መሳቂያ ነው ያደረገው። እነዚያው የዓለሙ ድርጅት ወታደሮች ደንዳና ሥልጣን አላቸው ቢባልም፣ ትጥቃቸውን ባገዘፉት ጀሌዎች ፊት እንደ ቱሪስቶች እየታዩ መሳለቂያ ነው የሆኑት። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ፥ እነዚያው የተባ መ ወታደሮች ራሳቸው ስደተኞቹን ሕፃናት ለግዳጅ ወሲብ እንደሚዳርጉ የሚሰማው ወሬ ነው። ሦሥተኛው የኮንጎ ጦርነት ውስብስብ እየሆነ በሚታይበት ባሁኑ ወቅት የዓለም ኅብረተሰብእ ገለልተኛ ተመልካች መምሰሉም ነው የሚያሳዝነው። ግን ያው ጦርነት ይብሱን ውስብስብ እየሆነ በተገኘ ቁጥር ተጨማሪ ወታደሮችን እንዲልክ የሚገደድ መሆኑን ሊገነዘበው በተገባውም ነበር የዓለሙ ድርጅት።

የአውሮጳው ኅብረት ከአንድ ዓመት በፊት በተሳካ ሁኔታ በቡኒያ ጣልቃ የገባበት ዓይነቱ ወታደራዊ ርምጃ አሁን የተጓደደ ሆኖ፥ የዓለሙ ፀጥታ ጥበቃ ምክርቤት ለሩዋንዳ ፋይዳ የሌለው አቤቱታ ያቀርባል፣ አንዳች ውጤት የማይኖረውንም የማዕቀብ ዛቻ ይሰነዝራል። ርግጥ፥ ፖል ካጋሜ በዚያው አካባቢ ብቸኛው ጦረኛ አይደሉም፣ ግን ሩዋንዳን አድነው ኮንጎን እሳት ውስጥ ዶለዋታል። ምፀቱ ታዲያ፥ ይህ እየሆነ ሳለ ሚሊዮኑ የጀርመንና የአውሮጳ ልማት-ርዳታ ወደ ሩዋንዳ ሲንቆረቆር መቆየቱና ለጦርሰራዊቱ ማግዘፊያ መዋሉ ነው። ለመሆኑ ግድያውን፣ ጭፍጨፋውን ለመግታት ማስቻል የነበረበት የፖለቲካው በጎፈቃድ ወዴት ኮበለለ? በያለበት፥ በዓለም ኅብረተሰብም ዘንድ የይስሙላው ቃል ብቻ ነው የሚሰማው። ዓለም በሩዋንዳ ከተፈፀው ከአሰቃቂው የሕዝብ ጭፍጨፋ ያገኘው ትምህርት የለም። ግና ማወቅ በተቻለም፥ በተገባም ነበር።