የኮንጎው አንጋፋ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቺሴኬዲ | አፍሪቃ | DW | 02.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የኮንጎው አንጋፋ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቺሴኬዲ

የተቃዋሚው «አንድነት ለዴሞክራሲ እና ማህበራዊ እድገት የተሰኘው ፓርቲ መሪ ቺሴኬዲ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ተሀድሶ እንዲሰፍን ለብዙ አሥርት ዓመታት ሲታገሉ ነበር ። የኮንጎው ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ከሥልጣን እንዲወርዱ በቅርቡ በተደረሰበት ስምምነት ውስጥም የላቀ ተሳትፎ በማድረግ  ይታወሳሉ ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:12

ኢትየን ቺሴኬዲ

የኮንጎ ተቃዋሚዎች አብነት ኤትየን ቺሴኬዲ ትናንት አርፈዋል ። በ84 ዓመታቸው ያረፉትን የኮንጎውን አንጋፋ ተቃዋሚ ኤትየን ቺሴኬዲን የዶቼቬለው ፊሊፕ ዛንድነርን ፕሬዝዳንት መሆን ሳይሳካላቸው ያረፉ ተቃዋሚ ሲል ነበር የገለፃቸው ። ቺሴኬዲ በቀድሞው የሀገሪቱ አምባገነን መሪ ሞቡቱ ሴሴሴኮ የሥልጣን ዘመን  በተለያዩ ሃላፊነቶች አገልግለዋል ። አገሪቱ ዛየር ተብላ በምትጠራበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ ። የፍትህ ሚኒስትርም ሆነው አገልግለዋል ። ምንም እንኳን በፕሬዝዳንት ሞቡቱ ሴሴሴኮ ዘመን ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩ ቢሆንም በሞቡቱ ላይ ዘመቻ ያካሄዱ እና አምባገነኑን ሞቡቱን ከተፈታተኑ ጥቂት የኮንጎ ፖለቲከኞች አንዱ ነበሩ ።ተንታኝ እና ጋዜጠኛ ጀነራሊ ኡሊም ዌንጉ  ቺሲኬዲ እድሜያቸው ቢገፋም በህዝቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እና የሚሰጣቸውም ክብር ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳሉ ። 
«በዛየር እና በኮንጎ ታሪካዊ የተቃዋሚዎች መሪ ናቸው ። በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ፣ብዙ ህዝብ ያከብራቸዋል ። ሰዉ በፖለቲካ መሪዎች ውስጥ የሚፈልገው ግርማ ሞገስ አላቸው ።ይህ ደግሞ እድሜ ሲገፋ የሚጠፋ አይደለም ። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ሲያረጁ ይበልጥ መሲህ  ይሆናሉ  ።» 

ቺሴኬዲ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የመጀመሪያውን ተቃዋሚ ፓርቲ በጎርጎሮሳዊው 1982 የመሠረቱ ፤እስከ እለተ ሞታቸው ለቆሙለት ዓላማ ሲታገሉ የቆዩ እና ወድቀው የማይቀሩ መሪ ነበሩ ።በተደጋጋሚ ጊዜያት የፖለቲካ ጎዞአቸው አበቃለት ሲባል ሁሌም ተመልሰው በማንሰራራት ይታወቃሉ ። በጎርጎሮሳዊው ህዳር 2011 የተካሄደው ምርጫ አሸናፊ ነኝ ብለው በፕሬዝዳንትነት ቃለ መሀላ ፈጽመው ነበር ። ሆኖም ያኔ ከተቃዋሚዎች በስተቀር ለቺሴኬዲ  እውቅና የሰጣቸው አልነበረም ። በዚህ ምርጫ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ  ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጬያለሁ ብለው ሥልጣኑን ዳግም ያዙ ።ቺሴኬዲ ግን ተሸንፈው አልቀሩም ። ከ5 ዓመት በፊት ሥልጣን መያዙ ባይሳካላቸውም ትግላቸውን አላቆሙም ። ለሁለት ዓመታት በህክምና ከቆዩበት ከቤልጂግ ባለፈው ሐምሌ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ያደረጉላቸው የእንኳን ደህና መጡ አቀባበል እንደ ድል የሚቆጠር ነበር ። ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላም ካቢላ በስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ በጎርጎሮሳዊው 2016 መጨረሻ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ሲጥሩ ነበር ። ይሁን እና የኮንጎ ፍርድ ቤት  ቀጣዩ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ማለት እስከ 2017 መጨረሻ ካቢላ ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚል አከራካሪ ውሳኔ አሳለፈ። ቺሴኬዲ መፈንቅለ መንግሥት ያሉትን ይህን እርምጃ ዝህቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲቃወም ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር ። ታህሳስ አጋማሽ መንግሥት እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ ዓመት ውስጥ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ፣ካቢላም ከአሁን በኋላ እንዳይወዳደሩ እና ህገ መንግሥቱንም እንዳይቀይሩ   ስምምነት ላይ ደርሰዋል ። ቺሴኬዲ ግን ካቢላ ቃላቸውን ጠብቀው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ሳያዩ አልፈዋል ። ኮንጎአዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዦን ክሎድ ካቴንዴ ቺሴኬዲ በኮንጎ ዴሞክራሲ እንዲነቃቃ በሩን የከፈቱ ፖለቲከኛ ናቸው ይላሉ ።

Bildkombo Etienne Tshisekedi Joseph Kabila Demokratische Republik Kongo

«በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ዴሞክራሲያዊ  ሂደት ቅድሚያ እንዲያገኝ በማነሳሳት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ።ፓርቲያቸው« አንድነት ለዴሞክራሲ እና ማህበራዊ እድገት በምህጻሩ UDPS ለአሁኖቹ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በርካታ ፖለቲከኞች የዴሞክራሲ ትምህርት ቤት ነበረ ።»
የቺሴኬዲ ጥንካሬ ምንልባትም በአንድ ወቅት ለሥልጣን ከነበራቸው ቅርበት የተገኘ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ኮንጎ ከቅኝ ገዥዋ ከቤልጂግ በ1960 ነጻ በወጣችበት ወቅት የሀገራቸውን መጻኤ እድል ለማቃናት ከሚፈልጉ ምሁራን አንዱ ነበሩ ። የህግ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ነበር ለብሔራዊ የህግ እና አስተዳደር ኮሌጅ ሃላፊነት የተሾሙት ። በ1968 ደግሞ ሞቡቱ በፍትህ ሚኒስትር ሚኒስትርነት ሰየሙዋቸው ።ከዚያም በልዩ ልዩ የሚኒስትርነት ሃላፊነቶች በአምባሳደርነት እንዲሁም በመንግሥት ድርጅቶች መሪነት ያገለገሉት ቺሴኬዲ የሞቡቱ ታማኝ ሆነው ለ20 ዓመታት ከሰሩ በኋላ ፕሬዝዳንቱን በመቃወም ትችት መሰንዘር ጀመሩ ። ለፕሬዝዳንቱ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ተሃድሶ እንዲካሄድ ጠየቁ ። «አንድነት ለዴሞክራሲ እና ማህበራዊ እድገት» የተባለውን በኮንጎ የመጀመሪያውን ተቃዋሚ ፓርቲ መሠረቱ ።ፓርቲው ወዲያውኑ ታገደ ።በ1992 በዓለም ዓቀፍ ግፊት ከተካሄደ ብሔራዊ ጉባኤ በኋላ ቺሴኬዲ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ ።ያኔ የለውጥ ተስፋ ቢሰነቅም ሞቡቱ ከዓመታት በኋላ ደም ባፋሰሰ አመጽ ከሥልጣናቸው ተባረሩ ።ሞቡቱ ሲነሱ የቀድሞዋ ዛየር የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ሆነች ። ቺሴኬዲም የተቃዋሚ ፖለቲከኞች አርአያ ሆነው ቀጠሉ ።ሞት ቀደማቸው እንጂ ቺሴኬዲ ቀጣዩ ምርጫ እስኪካሄድ ያለውን የሽግግር መንግሥት ተቆጣጣሪ ቦርድ እንዲመሩ ተመርጠው ነበር ። 

ፊሊፕ ዛንድነር /ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic