የኮንጎዉ ሐኪም መሸለም | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 22.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የኮንጎዉ ሐኪም መሸለም

መኪናቸዉን እያሽከረከሩ ከቤታቸዉ ቅጥረ-ግቢ ሲገቢ የታጠቁ ሰዎች ተከትለዋቸዉ--- «ዘዉ።» ዘበኛዉ ጮኸ---«ሊገድልዎት ነዉ---»እያለ።ለሐኪሙ የተዘጋጁት ጥይቶች የዘበኛዉን አካል በረቃቀሱት---ሞተ።

ኮንጎዊዉ የማሕፀን ሐኪም ዴኒስ ሙክዌጌ የአዉሮጳ ሕብረት የሚሰጠዉን የዘንድሮዉን የሳኻሮቭ ሽልማት አሸነፉ።ሙክዌጌ ለሽልማት የበቁት በትዉልድ ሐገራቸዉ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፕብሊክ የተደፈሩ ሴቶችን በመርዳታቸዉና በሴቶች ላይ የሚፈጸምን ወሲባዊ ጥቃት ለማስቆም በመታገላቸዉ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት በቀድሞዉ የሶቬት ሕብረት ሳይቲስት ስም የሰየመዉን ሽልማት 1980 ጀምሮ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈንና በደልን ለማስወገድ ለታገሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች በየዓመቱ ይሸልማል።ሽልማቱ 50 ሺሕ ዩሮ ያስገኛል።

ሐገር በርግጥ ሰላም ሆኖ አያዉቅም።ሐኪሙ ግን ክፉ ይገጥመኛል ብለዉ አላሰቡም።ተሳስተዋል።ሐሙስ ነዉ።ጥቅምት 25 2012-(ዘመኑ በሙሉ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።) መኪናቸዉን እያሽከረከሩ ከቤታቸዉ ቅጥረ-ግቢ ሲገቢ የታጠቁ ሰዎች ተከትለዋቸዉ--- «ዘዉ።» ዘበኛዉ ጮኸ---«ሊገድልዎት ነዉ---»እያለ።ለሐኪሙ የተዘጋጁት ጥይቶች የዘበኛዉን አካል በረቃቀሱት---ሞተ።

እስካሁን ገዳዮችን የያዘ-ግድያዉን ያጣራ የለም። የሕይወት ዑደት ግን ዘበኛዉ-ሲቀር ቀጠለ።ዘበኛቸዉ «ጭዳ» የሆኖላቸዉ ሐኪም ዴኒስ ሙክዌጌ ይባላሉ።ምሥራቃዊ ኮንጎ ቡካቩ የሚገኘዉ የፓንሲ ሆስፒታል አስተዳዳሪ ናቸዉ።የማሕፀን ሐኪም።ጦርነት ባልተለያት- ሐገር ተገደዉ የሚደፈሩ ሴቶችንና ልጃገረዶችን በየቀኑ ያክማሉ።ይረዳሉም።

«ሰዎችን እንደረዳ ያስተማረኝ አባቴ ነዉ»-አሉ ሰዉዬዉ 2009---ኦላፍ ፓልም የተሰኘዉን ሽልማት ሲያገኙ።አባት ቄስ ነበሩ።

«ለኔ (ያደረግሁት) ትንሽ ነገር ነዉ።ይሁንና ሁሌም ለራሴ የምነግረዉ በዚሁ ሥራ መቀጥሉ ጥሩ ነዉ እያልኩ ነዉ።»

ሕክምና ያጠኑት ኮንጎ ጎረቤት ብሩንዲ ነዉ።ትምሕርታቸዉን እንዳጠናቀቁ ደቡባዊ ኪቩ ግዛት ሌሜራ በትባል ከተማ ሥራ-ጀመሩ።በወሊድ ወቅት የሚሞቱት ሴቶች ብዛት-ለወጣቱ ሐኪም-እስደንጋጭ ነበር። » ሴቶችን በማከሙ ሙያ እንድሰለጥን ይበልጥ የገፋፋኝ ይሕ ነዉ።» ይላሉ ዶክተር ሙክዌግ። ፈረንሳይ ዉስጥ በማሕፀንና በማዋለድ ሕክምና ሠለጠኑ።ያኔ ገና ዛኢር ትባል ከነበረችዉ ሐገራቸዉ 1990ዎቹ አጋማሽ ሲመለሱ-ሐገሪቱን ከሚያወድመዉ እዉነታ ጋር መጋፈጥ ግድ ነበረባቸዉ።ጦርነት።ሌሜራ ወድማለች።ነዋሪዎችዋ ይገደሉ፤ የሰደዱ፤ ይደፈራሉ።የተፋላሚ ሐይላት ታጣቂዎች የየተቀናቃኞቻቸዉን ወገኖች ሴቶችን መድፈርን እንደ ዉጊያ ሥልት ተያይዘዉታል።

ሐኪሙም በሙያቸዉ ሰለቦችን ለመርዳት አዲስ ሥልት ቀየሱ።ርዳታ አሰባስበዉ ቡካቩ ዉስጥ ፓንሲ የተሰኘዉን ሐኪም ቤት መሠረቱ።እሳቸዉን ባልደረቦቻቸዉ ለተደፈሩ ሴቶች በሰጡት ሕክምና የሐኪም ቤቱ-ሥም ዝና ናኘ።«ሴቶች የማሕበረሰቡ ምሶሶና ማገር ናቸዉ» ይላሉ ሰዉዬዉ።«እንዲያዉ ወጣ ብሎ አዉራጎዳናዉን ያየ» ቀጠሉ ሐኪሙ «ሴቶች ልጆች ለማሳደግ፤ለማስተማር፤ቤተሰባቸዉን ለመቀለብ አብዛኛዉ ሥራ ሲሰሩ ማየት አይሳነዉም።» አከሉ።

ተፋላሚ ሐይላት የየባላንጣቸዉን ወገኖች ሴቶች የየጥቃታቸዉ ኢላማ የሚያደርጉትም፤ ሐኪም ሙክዌጌ እንደሚምኑት ሴቶቹ ከተጠቁ ማሕበረሰቡ ደጋፊ እንደሚያጣ ስለሚያዉቁ ነዉ።ሰዉዬዉ ሴቶችን ማከም ብቻ ሳይሆን የሴቶች መብት ተሟጋች ብጤም ናቸዉ።ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የጦርነቱ መቆም መሠረታዊ ጉዳይ ነዉ።ጦርነቱን ለማቆም ግን---ሙክዌግ 2012 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ምክር ቤት እንደነገሩት አንዱን፤ ሁለቱን ወይም ከዚያ በላይ አማፂን ማጥፋት፤ ወይም መሪዎችን ማሰርና መግደል በቂ አይደለም።

«አንዱን አማፂ ቡድን ማጥፋት የሚተክረዉ የለም።ዛሬ አንዱ ይጠፋል።ነገ ሌላ አዲስ ይወለዳል።»

አብነቱ-ዶክተር ሙክዌግ እንደሚያምኑት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በመንግሥትም፤በአማፂያኑም፤ በዉጪ ደጋፊዎቻቸዉም ላይ ተከታታይ ተፅዕኖ ማድረግ፤ የሐገሪቱ ሐብት ለሁሉም ዜጎች የሚዳረስበትን ሥልት መዘርጋት ነዉ።

ሙክዌግ፤ የዘበኛቸዉን ሕይወት ካጠፋዉ ጥቃት ያመለጡት ለፀጥታዉ ምክር ቤት ይሕን መልዕክት አስተላለፈዉ ወደ ሐገራቸዉ በተመለሱ በወሩ ነበር።በጥቃቱ ማግስት ባለቤታቸዉንና ሁለት ልጆቻቸዉን ይዘዉ ወደ ፈረንሳይ ተሰደዱ።ግን ብዙ አልቆዩም----ወገኖቻቸዉን ለመርዳት እንደገና ወደ ኮንጎ ተመለሱ።

«የማሕፀን ሐኪም ናቸዉ። ፈረንሳይ፤ ሌላ አዉሮጳ ሐገራት ይሁን የትም ሥፍራ ሊያኖራቸዉ የሚችል ልምድ አላቸዉ።ግን ሁሌም ከሐገራቸዉ መራቁን አልፈለጉም።»

ይላሉ ጀርመናዊቷ የሕክምና ርዳታ ድርጅት ሐላፊና የሙክዌንጌ ደጋፊ ጊዚላ ሽናይደር።

ጥረት፤ ድፍረት፤እና ዉጤቱ አምና Right Livelyhood Award የተሰኘዉን አማራጭ ኖቤል---አሸለማቸዉ።ዘንድሮ ደግሞ ሳኻሮቭን።ይገባቸዋል-ይላሉ ወይዘሮ ሽናይደር።

«በጣም ትክክለኛ ዉሳኔ ነዉ ።ምክንያቱም ተሸላሚዉ፤ በምሥራቃዊ ኮንጎ ሰላምና ፍትሕ ለማስፈን ሕይወታቸዉን በሙሉ የታገሉ ናቸዉና።»

ዶክተር ዴንስ ሙክዌንጌ የተሸለሙት አፍቃሬ-ምዕራባዉያኑ የዩክሬን ዩሮ ሜይዳን ከተሰኘዉ ንቅናቄና በቅርቡ ከታሰሩት የአዝርበጃንዋ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሌይላ ዩኒስን ከመሰሉ ተፎካካሪዎቻቸዉ መሐል ተመርጠዉ ነዉ።

ፊሊፕ ዛንድነር

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

Audios and videos on the topic