የኮሮና ተሕዋሲ ስጋት ለስደተኞች | ዓለም | DW | 27.04.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኮሮና ተሕዋሲ ስጋት ለስደተኞች

ኢትዮጵያ ዉስጥ  760 ሺሕ ስደተኞች በየመጠለያ ጣቢያዉ ሰፍረዋል።የሐገር ዉስጥ ተፈናቃዩን ቁጥር አናዉቅም።አብዛኞቹ ስደተኞች የደቡብ ሱዳን፤ የሶማሊያና የኤርትራ ዜጎች ናቸዉ።ስደተኞቹ የሚኖሩት ተፋፍገዉ ነዉ።ኮሮናን የመሰለዉን አደገኛ ተሕዋሲ የሚከላከሉበት የንፅሕና መገልገያ፣ ጭምብልም ሆነ ጓንት አያገኙም። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:03

የኮሮና ተሕዋሲ ስጋት በስደተኞች ጣቢያ


የ47 ዓመትዋ ኢራቃዊት ስደተኛ ወበቅ-መለስ፣እያለ ለሳምት ያሰቃያት ትኩሳት ሲጠናባት፣ ከሰፈረችበት (ከቪያል-ግሪክ ደሴት) መጠለያ ጣቢያ ባካባቢዉ ወደለዉ ሐኪም ቤት ተወሰደች። ተመረመረች። ከኮሮና ተሕዋሲ ነፃ ሆነች። ሐኪሞችዋ ወይም አሳካሚዎችዋ ሴትዮዋን ለማዳን አልተጨነቁም። መልሰዉ መጠለያ ጣቢያዋ ወረወሯት።ሞተች።በሽታዉ እስኪጠናባት አካሚ ማጣትዋ፣ ሆስፒታል ደርሳም ከኮሮና ተሕዋሲ ምርመራ በስተቅር ሌላ በቂ ሕክምና አለማግኘትዋ፣ ስደተኛ የመሆኗ «እርግማን» እንጂ በርግጥ ሌላ ሊባል አይችልም።ሴትዮዋ ትኖርበት የነበረዉ ስደተኞ ግን በጋራ ለምን ከማለት ጥያቄ ይልቅ፣ የሴትዮዋ የሞተቸዉ «በኮቪድ 19 ነዉ-አይደለም» ጠብ ገጥመዉ መጠለያ ጣቢያዉን አጋዩት።ሕክምና የማያገኘዉ ወይም እንደ ሟቿ የተነፈገዉ ስደተኛ ተሕዋሲዉ በርግጥ ቢሰራጭ ምን ይዉጠዉ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
                                  
ኢትዮጵያዊዉ ሐኪም ደብሩ ጉባ በሙያቸዉ የማሕፀን ስፔሻሊስትና ቀድዶ አካሚ ናቸዉ።ጀርመን ላይብሲሽ ከተማ አጠገብ በሚገኝ ሆስፒታል 26 ዓመት አገልግለዋል።እንደ ጎሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2009 እንደሳቸዉ ሁሉ የማሕፀን ልዩ ሐኪም ከሆኑ ባለቤታቸዉ ጋር ኢትዮጵያዉያን ወጣት ሐኪሞችን ማስተማር ወይም

ማሰልጠን ጀመሩ።ትምሕርቱ እየተጠናከረ፣ ሌሎች የጀርመን ሐኪሞችንም እየጨመረ በተለያዩ ሆስፒታሎችና ዩኒቨርስቲዎች ለሚያገለግሉ 110 ኢትዮጵያዉያን ሐኪሞች ተዳረሰ።
የኮሮና ተሕዋሲ የድፍን ዓለምን ሥራ፣አሰራር፣ ዕቅድ፣ ዓላማ፣ያኗኗር ዘዬንም  ሲዘበራርቀዉ ወይም ሲለዋዉጠዉ፣ የነዶክተር ደብሩ የርዳታ መልክና ባሕሪም ከዘመነ-ኮሮና ጋር መጣጣም ግድ ሆነበት።
ሐኪሞችና የሕክምና ተቋማት የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመከላከል፣ ሕሙማንን ለማዳን እና ለመርዳት ልዩ ትኩረት ሰጥተዉ መልፋት-መድክመቸዉ ተገቢ፣ አስመስጋኝ ሊደገፍም የሚገባዉ እርምጃ ነዉ።የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት የዓለም ቁጥር አንድ ሥጋት ነዉ ብሎ ሁሉን ነገር ለፀረ-ኮሮና እና ለመከላከሉ ማድረግ ግን ሌሎች የጤና እክሎችን አስዘንግቶ  አስከሬን እንዳያስመርት ያሰጋል።እንደገና ዶክተር ደብሩ።
ኢራቃዊቷን ስደተኛ የመረመሩት የግሪክ ሐኪሞች አንድም በኮቪድ 19ኝ ወረርሽኝ የተደናገጡ፣ ሁለትም ከኮቪድ 19ኝ ሌላ፣ ሌላ በሽታ አይገድልም ብለዉ የሚያስቡ፣ ሶስትም ደሐ በጣሙን ስደተኛን ለማከም ጊዜ ማጥፋት የለበንም ብለዉ የወሰኑ ከንቱዎች ባይሆኑ ኖሮ ያደረጉትን ባላደረጉ ነበር።
 ዓለም ኢራቃዊቷን ሟች የመሰሉ 70 ሚሊዮን ነዋሪዋ ስደተኛ ወይም ተፈናቃይ የሚል መለያ ተሰጥቶታል።ሶማሊያዊቱ መርየም አብዲ እና ምያንማሪቱ ሳኪና ኩታን ብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት፣

ሐገርና  ቋንቋ የሚለያያቸዉ ግን ስደተኞነትና ችግር ያመሳሰላቸዉ፣ የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት እኩል ያሰጋቸዉ አንድ ናቸዉ።
የመጀመሪያዋ የአሸባብን ጥቃት፣ ሁለተኛዋ የምያንማር መንግሥት ጦርን አረመናዊ ግድያ ሸሽተዉ ቀዳሚዋ ደዳዓብ-ኬንያ፤ ሁለተኛዋ ኮክስ ባዛር-ባንግላዴሽ ሰፍረዋል።«አሜሪካ ዉስጥ በየቀኑ ያን ሕል ሕዝብ ከገደለ----» አለች መርየም በቀደም ለአሶስየትድ ፕሬስ ዘጋቢ « እኛ ጋ ከመጣ ድምጥማጣችንን ነዉ የሚያጠፋዉ።»
የነመርየም መጠለያ ሰፈር 217 ሺሕ የሶማሊያ ስደተኛ ይርመሰመስበታል። ከሌላ ጥቃት በደል ሊያድናቸዉ የሚገባዉ የመንግስታቸዉ ጦር መንደራቸዉን እያጋየ፤ ወንዱን እየገደለ፣ ሴቶችን እየደፈረ ያባረራቸዉ ሮሒንጂያዎች የሰፈሩበት መንደር  ብዙ ስደተኞችን  የማስተናገድ ክብረ ወሰኑን ከደዳዓብ ከተረከበ ሁለት ዓመት አለፈዉ።ከአንድ ሚሊዮን በላይ።
ሳኪና ኩታን አንዷ ናት።እንደነገሩ በተወሻሻለ የቀርከሐ ጎጆ ዉስጥ ከሰባት ልጆችዋና ከሞት ካመለጠ ባለቤቷ ጋር ትኖራለች።«ተሕዋሲዉ----እዚሕ ከገባ የሚያድነን ሐኪም አይኖርም።» ትላለች ኩታን።
የጂማ ዩኒቨርስቲ ልዩ ሆስፒታል የበላይ ኃላፊ ዶክተር አሕመድ መሐመድ ኮሮና ተሕዋሲ ስደተኛ ጣቢያ ከደረሰ መዘዙን «አያድርስ» ዓይነት ይላሉ።«እንዳይደርስ የሚመለከተዉ አካል አስቀድሞ ይጠንቀቅ።»
ኢትዮጵያ ዉስጥ  760 ሺሕ ስደተኞች በየመጠለያ ጣቢያዉ ሰፍረዋል።የሐገር ዉስጥ ተፈናቃዩን ቁጥር አናዉቅም።አብዛኞቹ ስደተኞች የደቡብ ሱዳን፤ የሶማሊያና የኤርትራ ዜጎች ናቸዉ።ስደተኞቹ የሚኖሩት ተፋፍገዉ ነዉ።ኮሮናን የመሰለዉን አደገኛ ተሕዋሲ የሚከላከሉበት የንፅሕና መገልገያ፣ ጭምብልም ሆነ ጓንት አያገኙም። 
ስደተኛዉ በተሕዋሲዉ መለከፍ አለመለከፉ የሚመረመርበት መሳሪያም የለም።የቡርኪናፋሶዉ ደግሞ ከኢትዮጵያም የከፋ ነዉ።ዋጋዱጉ አጠገብ የሰፈረችዉ አጉሪታ ማይጋ «እጅሽን ቶሎ ቶሎ ታጣቢ» የሚለዉ ምክር  ሳይቸካት አልቀረም።«ሳሙና ለኔ በጣም ዉድ ነዉ» አለች።አንዱ ሳሙና 40 ሳምንቲም ነዉ።«40 ሳምንቲም ገዝቼ የልጆቼን ልብስ ነዉ ወይስ እጃቸዉን የማጥብበት?» 
ዶክተር ደብሩ እንደሚሉት የትሕዋሲዉን ስርጭት ለመከላከል ስደተኛዉን ይሕን-አድርግ አታድርግ ማለቱ ብዙም አይጠቅመምም።ስደተኛ በመሆኑ ማድረግ የሚገባዉን ማድረግ  አይችልምና። የሚጠቅመዉ ይቅጥላሉ ዶክተር ደብሩ።
ቡርኪናፋሶ ከ800 ሺሕ የሚበልጥ ዜጎችዋ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል። አብዛኞቹ ተፈናቃዮች የሰፈሩባቸዉ ጣቢያዎች በእያንዳዱ ክፍላቸዉ ከ30-እስከ 40 የሚደርስ ተፈናቃይ ያስተናግዳሉ።ቡርኪናፋሶ 20 ሚሊዮን ሕዝብ አላት።ፅኑ ሕመምተኞች የሚተኙባቸዉ አልጋዎች ግን 60 ብቻ ናቸዉ።የኮቪድ 19 ዓይነት ሕሙማን የሚተነፍሱባቸዉ ቬንትለተሮች ቁጥር ሐምሳ መድረሱ ያጠራጥራል።
 23 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሶሪያ ሕዝብ ከግማሽ የሚበልጠዉ  አንድም ተፈናቃይ አለያም ስደተኛ ነዉ።ዘጠኝ ዓመት ባስቆጠረዉ ጦርነት ከ900 በላይ የጤና ባለሙያዎች ተገድለዋል።350 የጤና ተቋማት ወድመዋል።ሶሪያዊዉ ሐኪም ዛሐር ሳሕሉል ቺካጎ-ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ አድቮኬት ክርስቲ የሚባለዉ ሆስፒታል ባልደረባ ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ሌሎች የሶሪያ ተወላጆችን አስተባብረዉ ያሰባሰቡትን የኮቪድ 19ኝ መመርመሪያ መሳሪዎች ኢድሊብ በሚባለዉ የሶሪያ ግዛት ለተፈናቀሉ

ወገኖቻቸዉ በቅርቡ ልከዋል። «የምሰራበት ሆስፒታል 230 ቬልትሌተር አለዉ» አሉ ዶክተር ሳሕሉል፤ « 4 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርበት ኢድሊብ ያለዉ ቬትሌተር ግን 98 ብቻ ነዉ።» አከሉ።
የተባበሩት መንግስታት የጤና ድርጅት (WHO) ችግሩ ለጠናባቸዉ ስደተኞች የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያና መመርመሪያ መሳሪያዎችን ለመስጠት እየጣረ ነዉ።ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ ለድርጅቱ የምትሰጠዉን 400 ሚሊዮን ዶላር መዋጮና ድጎማ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በማቋረጣቸዉ ወትሮም እጅግ አናሳዉ የዓለም ጤና ድርጅት ርዳታ በእጅጉ ይቀንሰዋል።
በ30 ሐገራት የሚኖሩ ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን የሚረዳዉ የኖርዌ የስደተኞች መርጃ ምክር ቤት ኃላፊ የን ኤግላንድ እንደሚሉት የኮሮና ተሕዋሲ ስደተኞችና ስደተኞች በሰፈሩባቸዉ ሐገራት እንዳይሰራጭ ሐብታሞቹ ሐገራት ቢረዱ ርዳታዉ የሚጠቅመዉ ለራሳቸዉም ጭምር ነዉ።«ምክንያቱም ወረርሺኙ ከዩናይትድ ስቴትስ ጠፍቶ ቬኑዙዌላ ወይም ሑንዱራስ ዉስጥ ቢሰራጭ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መግባቱ አይቀርም።» ባይናቸዉ።«ተሕዋሲዉ አሁን ከአዉሮጳ በቱርክ አድርጎ ኢድሊብ ከገባ» ቀጠሉ የኖርዌዉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የበላይ «ከኢድሊብ በቱርክ አድርጎ ወደ አዉሮጳ እንዳይመለስ ማድረግ አይቻልም።» እያሉ
ዶክተር ደብሩ  በበኩላቸዉ ኮቪድ 19  የስደተኛ መጠለያ ጣቢዎችን ከወረረ  ለስደተኛዉ ተጨማሪ ፈተና፣ ስደተኛዉን ለሚያስተናግደዉ ማሕበረሰብም የጥላቻ መቀስቀሻም የበሽታ ዑደት መሠረትም  ነዉ የሚሆነዉ።«ስደተኛ ጣቢያዎች መፍረስ አለባቸዉ።ስደተኛዉ ከሕዝቡ መቀየጥ አለበት።» ይሉ ዶክተር ደብሩ።

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ


 


 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች