የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ወቅታዊ ይዞታ | ጤና እና አካባቢ | DW | 18.05.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ወቅታዊ ይዞታ

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በተከታታይ ቀናት በየዕለቱ ይመዘገብ የነበረው በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን የዓለም የጤና ድርጅት ትናንት ይፋ አድርጓል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር እንደተናገሩት ምንም እንኳን በአንዳንድ ሃገራት በርካታ ሰዎች ክትባቱን ማግኘታቸው እውነት ቢሆንም አሁንም ወረርሽኙ አብቅቷል ማለት ግን አይቻልም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:28

«የክትባቱ ለሁሉም ካልተዳረሰ ችግር ነው»

የኮቪድ 19 ክትባትን ለዜጎች በመስጠት የቀደመችው ብሪታንያ ዜጎች አሁን ለወራት የተገደበ እንቅስቃሴያቸው ዘና በማለቱ ሰው ከሰው መገናኘት መጀመሩ እፎይታ እንደፈጠረላቸው እየገለጹ ነው። የመተላለፊያው መንገድ በግልጽ ባለመታወቁ የሰዎች ለሰዎች መቀራረብ ገደብ ተጥሎበት፤ የሕብረት መዝናኛ ቦታዎች ተዘግተው፤ ሰዎች በየግላቸው ለጭንቀት እስኪዳረጉ ድረስ መነጣጠላቸው ለብዙዎች ሰቀቀን ሆኖ በመክረሙ እንደዋዛ ይታይ የነበረው አብሮነት አሁን ብርቅ ሆኗል። የ18 ዓመቲ ሊዮን ቫጌላ እንደተማሪነቱ አዘውትሮ ይሄድበት የነበረው ሲኒማ ቤት ለረዥም ወራት ተዘግቶ ትናንት መከፈቱ የፈጠረበትን ልዩ ስሜት መሸሸግ አልቻለም።

«ወደ ፊልም ቤት መሄድ እጅግ ከተለመዱ ተግባራቶቼ አንዱ ነበር፤ ዛሬም ወደዚህ መምጣት በመቻሌ በጣም ተደስቻለሁ። ለዚህም ነው የእንቅስቃሴ ገደቡ ዛሬ ሲነሳ እዚህ የመጣሁት፤ ለዚህም ነው ቀድሜ እዚህ የደረስኩት። መቆየት አልቻልኩም።»

እንግሊዝ ውስጥ አሁን እስከ 30 ሰዎች ከቤት ውጭ መሰባሰብ ይችላሉ። ስድስት ሰዎች ወይም የሁለት ቤተሰብ አባላት ደግሞ በቤት ውስጥ ተሰባስበው መጨዋወት ተፈቅዶላቸዋል። እስከ 30 የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ ሠርግ ላይ ለመታደም፤ ወይም የተለያዩ ግብዣዎችም ሆኑ ዝግጅቶች ላይ መገኘት ይችላሉ። ለቀብር የሚገኙ ሰዎች ለጊዜው አሁን ቁጥራቸው አልተገደበም፤ የሚሰባሰቡበት ስፍራ ግን ብዛታቸውን ይወስናል። የእንቅስቃሴ ገደቡ መነሳቱን ተከትሎ አሁን በእንግሊዝ ማኅበራዊ ርቀትን በተመለከተ ያለው ጥንቃቄ ተለውጧል። የቅርብ ቤተሰብ እና ጓደኛሞች በራሳቸው ውሳኔ መሠረት ሊያደርጉት የሚገባውን ጥንቃቄ እንዲወስዱ ኃላፊነቱ ተሰጥቷቸዋል። ውሳኔው የራሳቸው በመሆኑም የቅርብ ንክኪም ሆነ መተቃቀፉ የሚያስከትለውን መመዘን ይኖርባቸዋል ማለት ነው።  

Weltspiegel | Schweiz Corona-Situation Lockerungen in Lausanne

ስዊዘርላንድ ከኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ወደ ዳግም ሕይወት

አሁን ቡና ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶችም ሆኑ ምግብ ቤቶች በራቸውን ከፍተው ደንበኞቻቸውን በውስጥ ማስተናገድ ይችላሉ። የቤት ውስጥ መዝናኛዎች እንደ ቤተ መዘክር፣ ሲኒማ እንዲሁም የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ ቲያትር ቤቶች፣ የኮንሰርት አዳራሾች፣ ስታዲየሞች እና የመሰብሰቢያ ማዕከላት ተከፍተዋል። ሌሎችም ተመሳሳይና ተያያዥ መዝናኛ ቦታዎች ይከፈታሉ። ይኽንኑ የዘረዘሩት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሪስ ጆንሰን ኅብረተሰቡ ተጥሎበት ከቆየው የእንቅስቃሴ ገደብ ሲወጣ የራሱን ጥንቃቄ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።

«አስደናቂ ስኬት ላስከተለው የክትባት መርሃግብር እና ሕጎቹን በመከተል በኩል ጽናት ላሳዩ ሁሉ ምስጋና ይድረስና፤ አሁን ወደ ሦስተኛው ደረጃ መሻገር እንችላለን። ይኽም ጥንቃቄ እና ወደማይቀለበሰው ነጻነት መራመድ ይሆናል። ይኽም ማለት ከግንቦት 17 ቀን ጀምሮ እንግሊዝ ውስጥ ከቤት ውጭ እስከ 30 ሰዎች ሆናችሁ መገናኘት ትችላላችሁ፣ በቤት ውስጥ ከሆነ ደግሞ ስድስት ሰዎች ወይም ሁለት ቤተሰብ መሰባሰብ ትችላላችሁ። ቡና ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶችና ምግብ ቤቶች ተከፍተው ያስተናግዳሉ፤ ሲኒማ ቤቶች፣ የቦውሊንግ መጫወቻ ስፍራዎች፣ እንዲሁም ሙዚየሞችም መከፈት ይችላሉ። የእረፍት ጊዜ መዝናኛዎች ሁሉ ሆቴሎች፣ ሆስቴሎች እንዲሁም አልጋና ቁርስ የሚያቀርቡ የእረፍት ቦታዎች ሁሉ ሥራቸውን ይጀምራሉ።»

ሌላዋ የእንቅስቃሴ ገደብን ያነሳችው ሀገር ግሪክ ስትሆን፤ በሀገር ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ዘጎቿ ብቻ ሳይሆን የአየር፣ የባሕርና የየብስ ድንበሮቿንም ለሀገር ጎብኚዎች ከፍታለች። ግሪክ ውስጥ ዛሬም በየዕለቱ በአማካኝ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደማ በኮቪድ 19 መያዛቸው ቢመዘገብም ክትባቱን በማዳረስ ላይ መሆኗን አሳውቃለች። በመላው አውሮጳ ከሀገር ወደ ሀገር በመጓዝና በመንሸራሸር የሚታወቁት ጀርመናውያን ሀገር ጎብኚዎች ወደ ግሪክ መጓዝ መጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተመሳሳይ የእንቅስቃሴ ገደብን ማንሳቷን ይፋ ያደረገችው ብሪታንያ ዜጎች ከሀገር ለመዝናኛ ጉብኝት መውጣታቸውን ባታግድም እንደግሪክ ወዳሉት ዛሬም በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር ወደሚመዘገብባቸው ሃገራት ባይሄዱ እንደሚበጅ አሳስባለች። እንግሊዝ ምንም እንኳን በተሳካ መልኩ ክትባት ለዜጎች አዳርሻለሁ ብትልም ሕንድን ያስጨነቀው ልውጥ ተሐዋሲ በሀገሪቱ መገኘቱ ከስጋት ለመላቀቅ አልፈቀደላትም። የጀርመኑ ሮበርት ኮኽ ተቋምም ካሳለፍነው እሁድ ሌሊት ጀምሮ የስጋት አካባቢ ሲል ከፈረጃቸው ሃገራት አንዷ ብሪታንያ መሆኗን በዝርዝሩ አመላክቷል። በተቃራኒው በርካታ ቱሪስቶች የሚጎርፉባት ግሪክ በተሐዋሲው ስርጭት ዝርዝር ቢጫ ቀለም ከተሰጣቸው አንዷ ናት። በተመሳሳይ ፖርቱጋልም ለጎብኚዎች በሮቿን ከፍታለች። ባለፈው ወር የእንቅስቃሴ ገደብን ያነሳችው ፖርቱጋል በአረንጓዴ ቀለም ሥር ካሉት ሃገራት ተርታ ናት።

Weltspiegel 27.04.21 | Italien Coronavirus | Öffnungsschritte nach Lockdown

የእንቅስቃሴ ገደብ የተነሳላት ጣሊያን

ሁለተኛው የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ከፍተኛ ጫና ያሳደረባት ጀርመንም ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ወዲህ በተሐዋሲው አዲስ የሚያዙት ቁጥር ከአንድ መቶ ሺህ መካከል ከመቶ በታች እየሆነ በመምጣቱ ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ቀስ በቀስ ማንሳት ጀምራለች። ጀርመናውን የእረፍት ጊዜያቸውን ወደሚያሳልፉባቸው ስፔን፣ ግሪክ፣ ጣሊያን፤ ኦስትሪያ እና ስዊትዘርላንድ የመሄድ ዕድሉ ተመቻችቶላቸዋል። ከተጠቀሱት ሃገራት ወደ ጀርመን የሚመጣ ማንኛውም ሰው ተመርምሮ ከኮሮና ተሐዋሲ ነጻ መሆኑን የሚያረጋግጥ የህክምና ወረቀት ከያዘ ራሱን አግልሎ መቆየት አይጠበቅበትም። በአውሮፕላን የሚጓዙ ሁሉ አስቀድመም በመመርመር ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ያስፈልጋቸዋል። በተሐዋሲው ተይዘው የዳኑ እንዲሄሁም የተከተቡ ደግሞ የተሻለ የመንቀሳቀስ ነጻነት አላቸው ነው የተባለው። እንዲህ ያሉት ሰዎች ልውጡ ተሐዋሲ ከተስፋፋባቸው ሃገራት ከመጡ ብቻ ነው ራሳቸውን አግልለው እንዲቀመጡ የሚገደዱት። ፈረንሳይም እንዲሁ በወረርሽኙ ምክንያት ጥላው የቆየችውን የእንቅስቃሴ እገዳ በማንሳቷ ምግብ ቤቶች እንግዶችን ለማስተናገድ በሮቻቸውን ከፍተዋል። አላይን ሎይክ የምግብ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

«ዳግም ለመተያየት በመቻላችን በጣም በጣም ደስተኞች ነን። ሥራ አስኪያጆች፤ አስተናጋጆች፤ ምግብ አብሳይ ባለሙያዎች፣ ዕቃ አጣቢዎች ሁላችንም በድጋሚ ለመተያየት በመብቃታችንና ስሜታችንን ለመጋራት በመቻላችን በጣም ደስ ብሎናል።»  

በአውሮጳ ሃገራት ብቻም አይደለም በኮሮና ተሐዋሲ ክፉኛ በተጎዳቸው ዩናይትድ ስቴትስም ሕይወት ቀስ በቀስ ማንሰራራት ጀምራለች። ሃገራት ለበርካታ ወራት ከገጠማቸው የጤና ስጋትና ችግር በመጠኑ የእፎይታ ንፋስ ማግኘት መጀመራቸው በአንድ ወገን ቢነገርም አሁንም በተለይ ሕንድ ውስጥ ከ263 ሺህ በላይ ሰዎች ባለፉት  24 ሰዓታት መያዛቸው እየተነገረ ነው። ከአራት ሺህ የሚበልጡትም በአንድ ቀን አልቀዋል። በአሁኑ ሰዓትም በመላ ሀገሪቱ በኮቪድ 19 የተያዙት ሰዎች ከ25 ሚሊየን በልጠዋል። ይኽም አሁንም የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ገና ከዓለም ላይ ገለል እንዳላለ ማሳያ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም አመልክተዋል።

Polen I Coronavirus I Lockerungen in Krakau

ከቤት ውጭ መዝናናት በፖላንድ

«ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተከታታይ በመላው ዓለም በኮቪድ 19 የሚያዙትም ሆነ በዚህ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ታይቷል። በአንዳንድ ሃገራት የክትባቱ በስፋት መዳረስን ተከትሎ ሰፊ የሆነ ልዩነት በመኖሩ ወረርሽኙ አበቃ የሚል አስተሳሰብ አለ። ሆኖም ሌሎች እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በበሽታው እየተያዘ መሆኑ ይታያል። በበርካታ ሃገራት ያለው ሁኔታ አሳሳቢነቱ እንደቀጠለ ነው። ወረርሽኙ ሊያበቃ ገና ረዥም ጉዞ ይቀራል። ወረርሽኙ በሁሉም ቦታ እስካልጠፋ ድረስ ከየትኛውም አካባቢ ሊወገድ አይችልም።»

Coronavirus | Impstoff

የኮቪድ 19 ክትባት

እሳቸው እንዳሉትም ከዚህ ቀደም በወሰዱት የጥንቃቄ ርምጃ የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር የቻሉ ሃገራት በአሁኑ ጊዜ ኮቪድ 19 በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶባቸው ተቸግረዋል። ምንም እንኳን ጥቂት የማይባሉ ሃገራት ክትባቱን ለበርካታ ዜጎቻቸው ማዳረስ ቢሳካላቸውም ሁሉም ሃገራት በቂ ክትባት ማግኘት እስካልቻሉ ድረስ ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ እንደሚቀጥልም ነው ዋና ጸሐፊው ያሳሰቡት። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እስካሁን በመላው ዓለም ከ1,4 ቢሊየን በላይ የኮቪድ 19 ክትባት በ176 ሃገራት ተዳርሷል። በቀን 24,5 ሚሊየን ክትባት ነው የሚሰጠው። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ 274 ሚሊየን ክትባት ለዜጎች ተሰጥቷል። አሜሪካን ውስጥ በየቀኑ ከ1,8 ሚሊየን በላይ ክትባት እየተሰጠ ሲሆን በዚህ ከቀጠለ በቀጣይ አራት ወራት ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ ማዳረስ እንደሚቻል ይታመናል። የክትባቱ መዳረስ ውጤት እንዳለው ለዓለም በቅድሚ ያሳየችው እስራኤል ናት። ባለፈው የካቲት ነበር 84 በመቶው የሚሆነውን በሀገሯ ከ70 እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ሁለቴ እንዲከተቡ በማድረግም በበሽታው የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ እንደቻለች ተመዝግቦላታል።  

 እንዲያም ሆኖ እስካሁን በመላው ዓለም የተዳረሰው የክትባት መጠን ከዓለም ሕዝብ 9,7 በመቶው እንዲከተብ ማስቻሉ ነው የሚነገረው። በተለይም አፍሪቃ ውስጥ ጥቂት ሃገራት ናቸው መጋቢት ወር ላይ መጠነኛ ክትባቶች የተላኩላቸው። በመላው ዓለም ክትባቱን ለዜጎች በማዳረስ ሲሸልስ ቀዳሚዋ ስትሆን እስካሁን ከዜጎቿ 68,5 የሚሆነው ክትባት አግኝቷል፤ በመቀጠል ማልዲቭስ 60,3 በመቶ፤ እስራኤል 58,2፤ ጀርመን 24,1 በመቶ ለሚሆነው ስታዳርስ ኢትዮጵያ 0,7 በመቶ ላይ ናት። ዓለም ከወረርሽኙ ተላቅቆ ወደቀደመ የኑሮ ስልቱ ለመመለስ በበቂ መልኩ ክትባቱን ማዳረስ እንዳልቻለ ያመለከተው የዓለም የጤና ድርጅት በዚህ ምክንያትም ልዩነት መፈጠሩን አጽንኦት ሰጥቷል።

Madagascar Covax

የኮቪድ 19 ክትባት ለማዳጋስካር

እንዴት በፍጥነት ሊዘጋጅ ቻለ በሚል ብዙዎች በስጋት ሲመለከቱት የቆዩት የኮቪድ 19 ክትባት የተዳረሰባቸው ሃገራት አሁን በሚታየው ደረጃ ለወራት የጣሉትን የእንቅስቃሴ ገደብ ለቀቅ ማድረግ ጀምረዋል። በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የሚታየውን ሞቃት የአየር ሁኔታ ተከትሎ ከሀገር ወደ ሀገር የሚደረገው እንቅስቃሴ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለጊዜው ባይታወቅም ሰዎች ቢከተቡም ባይከተቡም አካላዊ ርቀት መጠበቅን ጨምሮ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም ላይ እንዳይዘናጉ ምክሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

 ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች