የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት እና የመከላከል ጥረት | ጤና እና አካባቢ | DW | 18.02.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት እና የመከላከል ጥረት

ኮቪድ-19 የሚል ስያሜ የተሰጠው ቻይና ውስጥ የተቀነቀሰው ተላላፊ ተሐዋሲ ያጠቃቸው ሰዎች ቁጥር ከ70 ሺህ በልጧል። የሞቱት ደግሞ ሁለት ሺህ ተጠግተዋል። ተሐዋሲው በሩቅ ምሥራቅ ይቀስቀስ እንጂ ባለው የመጓጓዣና የእንቅስቃሴዎች ፍጥነት ምክንያት ሃገራት ስጋት ገብቷቸዋል። ወደእስያ የተጓዙ ዜጎችም በየሀገሩ ለጥንቃቄ ክትትል እየተደረገባቸው ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:22

«ኮቪድ-19»

ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2019 መጨረሻ ላይ ለመጀመሪ ቻይና ውስጥ በወረርሽኝ መልክ መተስቀሱ የተነገረው ኮሮና ተሐዋሲ አነሳሱ ግልፅ ባይወጣም ከእንስሳት ወደ እንስሳት በመተላለፍ የሚታወቅ መሆኑን አንዳንድ የምርመራ ዘገባዎች ያሳያሉ። ሌላው መታወቅ ያለበት ኮሮና ተሐዋሲ የተለያየ አይነት እንዳለው ነው።  ቀደም ሲል በጎርጎሪዮሳዊው 2002 ሳርስ፤ በ2012 ደግሞ መርስ የተሰኙ የዚሁ ተሐዋሲ አይነት ወረርሽኞች ተከስተው እንደነበር። ሳርስ፤ መርስም ሆነ  ኮሮና  የመተንፈሻ አካላትን የሚያውኩ ተሐዋሲዎች ናቸው። ተሐዋሲው እንግዳ ባይሆንም አይነቱ በመለወጡ እስካሁን መድኃኒት አልተገኘም። 

 ኮሮና ተሐዋሲ የተለመደው የጉንፋን በሽታን፤ እንዲሁም የመተንፈሻ አካል ችግርን የሚያመጡ ተሐዋሲዎች ቤተሰብ ሲሆን አንድ ሰው በዚህ በሽታ መያዙ እስኪታወቅ በአማካይ ከ12 እስከ 14 ቀናት ሊወስድ እንደሚችል የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። የሚያደርሰው ጉዳትም ከኃይለኛ ሕመም አንስቶ እስከ ሞት ይደርሳል። እስካሁንም ትኩሳት፤ ሳል እና የትንፋሽ ማጠር ወይም የመተንፈስ ችግር እንደሚያስከትል የተገለፀው በሳይንሳዊ ስሙ ኮቪድ 19 የተሰኘው ኮሮና ተሐዋሲ ለ1ሺህ 775 ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ ተሰምቷል። እስካሁንም  ቻይናን ጨምሮ በ26 ሃገራት በኮሮና ተሐዋሲ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ተመዝግቧል። በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 71 ሺህ 432 ደርሷል።

በተለያዩ ጊዜያት የመተንፈሻ አካላት ችግር ለምሳሌም እንደኢንፉሉውንዛ ያሉ ህመሞች ያጋጠማቸው ሰዎችን ተሐዋሲው የመጉዳት አቅም እንዳለው  መረጃዎች ያሳያሉ። ተሐዋሲው የተቀሰቀሰባት እና እጅግ የተስፋፋባት ቻይና ሰዎች ራሳቸውን ከበሽታው ለመከላከል ሊያደርጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄ ከመምከር ባሻገር በተሐዋሲው ለተያዙት ዜጎቿ መድኃኒት ለማግኘት ጥረቷን ቀጥላለች። የዓለም የጤና ድርጅት እና የህክምና ዘርፍ ተመራማሪዎችም መድኃኒቱን ለማግኘት የበሽታው ምንነት እና የትመጣው እንዲጣራ ምርምር ያደረጉ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት ከፍተኛ ሳይንቲስት የሆኑት ዶክተር ሶሙያ አዋሚናታን የምርምሩ ትኩረት ምን ላይ መሆን እንዳለበት መለየቱን አመልክተዋል።

«ምርምር ከሚደረግባቸው ዘርፎች መካከል የመተላለፉ ሁኔታ እና የትመጣው ቅድሚያ ማግኘት እንዳለበት ለይተናል። ምክንያቱም የተሐዋሲውን ምንነትና ከየት እንደመጣ እንዲሁም እንዴት ወደሰው እንደተዛመተ መረዳት ይኖርብናል። በዚህም ላይ የመተላለፍ ይዞታው፤ የሚያጠቃው የተለየ የዕድሜ ክልል፣ እንዲሁም ከሌሎች በተለየ እንዴት ያሉ ሰዎች ላይ በሽታው እንደሚፀና እና ትኩረት የሚያሻቸው የትኛዎቹ ሁኔታዎች ወይም የተፈጥሮ አካባቢዎች ናቸው የሚለውም በቶሎ ሊታወቅ የሚተባው ጉዳይ ነው።»

ባለፈው ሳምንት ጄኔቫ ላይ በተካሄደው ውይይት ከ300 የሚበልጡ ተመራማሪዎች እና ሳይንቲስቶች በአካል እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ተሳትፎ አድርገዋል። የሳይንቲስቶች እና የገንዘብ ለጋሾች የጋራ ውይይቱም ተሐዋሲውን በተመለከተ አስቸኳይ ምርምር እንደሚያስፈልግ ከመግባባት እንዲደርሱ ማገዙ ተነግሯል። የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ተመራማሪዎች በሚያከናውኑት ሥራ ታማሚዎችን እንዴት መርዳት እንደሚቻል በቂ መረጃ ይገኛል የሚል ተስፋቸውን ገልጸዋል።

«ዓለም አቀፍ የተመራማሪ ማኅበረሰብ ፈተናውን ለመቋቋም ያሳየውን ኃይል እና ፍጥነት በጣም አበረታቶኛል።  እኛ እዚህ ስንነጋገር የምርምር ቡድኖችን በገንዘብ የሚደግፉ አካላት እጅግ አሳሳቢ ለሆነው ችግር መፍትሄ ለማግኘት ቀዳሚ ምርምሮች እንዲካሄዱ ለማድረግ እየተወያዩ ነው። ቅድሚያ ከተሰጣቸው መካከል ቀላል ምርመራ ማካሄድ፤ ተጋቦቱን ለመከላከል የሚረዳ የተሻለ መከላከልን እንዲሁም ታማሚዎችን ሊያክሙ የሚያስችሉ ዘዴዎችን፣ ክትባት ማግኘት የሚገባቸውን የመለየት እንዲሁም ይህን  እንዴት ማፋጠን እንደሚቻል በተጨማሪም ለችግሩ መፍትሄ  እንዴት ማግኘት ይቻላል የሚሉት ይገኙበታል።»

ለኮሮና ተሐዋሲ ወይም ለኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት በ18 ቀራት ውስጥ ሊገኝ እንደሚቻል ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ ተሐዋሲው ተስፋፍቶ የባሰ ጉዳት እንዳያደርስ ባለው አቅም መረባረብ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

«አሁንም በእጃችን የሚገኙ ተሐዋሲው እንዳይተላለፍ የሚረዱ በርካታ መሠረታዊ ዘዴዎች አሉ። ለምሳሌ ለዚህ ችግር የመጀመሪያው ክትባት ሊዘጋጅ የሚችለው ከ18 ወራት በኋላ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ማድረግ የምንችለው ተሐዋሲውን ለመዋጋት የሚረዱ በእጃችን የሚገኙ መሣሪያዎችን ዛሬ  መጠቀም ነው።»

አልጃዚራ እንደዘገበው የቻይና መንግሥት ራሱ ነው ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ማለቂያ ላይ ለዓለም የጤና ድርጅት 11 ሚሊየን ዜጎች በሚገኙበት በሀገሪቱ የወደብ ከተማ ሁዋን ያልተለመደ እና የሳንባ ምች መሰል ከባድ ህመም መከሰቱን ያመለከተው። በወቅቱ ከታመሙት አብዛኞቹ በከተማዋ ከባሕር የሚገኙ ምግቦች መሸጫ ስፍራ የሚሠሩ ወገኖች ነበሩ። ወዲያውም ገበያው ተዘጋ። የህክምና ባለሙያዎች የበሽታውን ምንነት የማጣራት ሂደት ላይ ሳሉ በታማሚዎች ቁጥር ከ40 በለጠ። ወዲያውም የቻይና ባለሥልጣናት በሽታው በጎርጎሪዮሳዊው 2002 ተከስቶ ከ700 ሰዎች በላይ ሕይወት የቀጠፈው ሳርስ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሱ። ብዙም ሳይቆይ የዓለም የጤና ድርጅት እንደጠቆመው ባለሥልጣናቱ አዲስ ተሐዋሲ ማግኘታቸውን ይፋ አደረጉ። ኮቪድ 19 የሚል ስያሜ የተሰጠው ፈጥኖ የሚተላለፈው ኮሮና ተሐዋሲ የተገኘው እዚህ ጋር ነው በሚል ቦታዎችን ለይቶ መግለፁ መገለልን ሊፈጥር እንደሚችል ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም አሳስበዋል። ኮቪድ 19፤ CO፤ ኮሮና፣ VI፣ ቫይረስ፣ D ደግሞ ዲዝዝ፤ የሚል ትንታኔ የያዘ ነው።

« በሽታው ቦታዎችንም ሆነ፤ እንስሳት፣ ግለሰቦችም ሆነ በቡድን ያሉ ሰዎችን በሚገልፅ መልኩ የሚገናኝ ስያሜ እንዳይኖረው የተለየ ስም መፈለግ አለብን። ስም አሰጣጡ ያልተገባ ወይም የሚያገልል ስያሙ እንዳይኖር ይከላከላል። በዚያም ላይ ወደፊት ለሚከሰቱ የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኞች ደረጃውን የጠበቀ አካሄድ እንዲኖረን ያደርጋል።»

ምንም እንኳን ኮቪድ 19 ተሐዋሲ በ26 ሃገራት ውስጥ መገኘቱ ቢረጋገጥም፤ ቻይና ውስጥ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ከሌሎቹ ጋር የሚወዳደር እንዳልሆነ ነው የተገለፀው።

በሻንጋይ የህክምና ዶክተሮች በበኩላቸው የታማሚዎችን ሕይወት ከማትረፍ ጎን ለጎን ምርምር እያካሄዱ ነው። ቀደም ሲል በሀገሪቱ የተከሰተው የሳርስ ተሐዋሲ ተጠቂዎች የታከሙበት የሻንጋይ የህክምና እና  የምርምር ማዕከል በዚሁ ተግባር ተጠምዷል። እስካሁን በተሐዋሲው በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በሞቱባት ቻይና በአንድ ጊዜ በርካታ ተመሳሳይ የጤና ችግር ያጋጠማቸው ታማሚዎችን በአንድ ሀኪም ቤት ማስተናገድ አቅምን የሚፈታተን መሆኑን የማዕከሉ ተባባሪ ዳይሬክተር ሉ ሁንግዙ ተናግረዋል። እስካሁን የህክምና እና ምርምር ማዕከሉ 320 የኮሮና ተሐዋሲ ታማሚዎችን ተቀብሎ ያስታመመ ሲሆን፤ 135ቱ ተገቢውን ህክምና አግኝተው ተሽሏቸው ከሀኪም ቤት መውጣታቸውንም አመልክተዋል። አሁንም ዶክተሮe ቀሪ 184 ታማሚዎች ፤ ከእነሱ መካከል ደግሞ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ 14 ዜጎችን እያከሙ ነው። ለህክምናውም በሽታ የመከላከል አቅም የሚያጠናክሩ ፀረ ተሐዋሲ መድኃኒቶችን፤ እንዲሁም ከተሐዋሲው መዳን የቻሉ ታማሚዎች ደም ውስጥ ቀለም አልባውን ፈሳሽ ወይም ፕላዝማ በመጠቀም እየረዱ መሆኑን ዶክተሩ ተናግረዋል። ከዚህም ሌላ የቻይናን ባህላዊ መድኃኒት በኮሮና ተሐዋሲ ለተጠቁ ወገኖች በመስጠትም በርካቶችን በመርዳት ላይ መሆናቸውን ዛሬ አመልክተዋል።

«የቻይናን ባህላዊ መድኃኒት በመጠቀም ረገድ በአሁኑ ሰዓት ሀኪም ቤት ከገቡት አጠቃላይ ሰዎች 90 በመቶው ባህላዊ የቻይና መድኃኒትን ተጠቅመዋል። በሀኪም ቤታችን ካሉት ከ184 ታማሚዎች ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁሉም የቻይናን ባህላዊ መድኃኒት ተጠቅሟል። ከዚህ ተነስተንም የቻይናን ባህላዊ መድኃኒት እና የምዕራባውያንን መድኃኒት አጣምሮ መጠቀሙ ወረርሽኙን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ጠቃሚ ሚና ተጫውቷል ብሎ መደምደም ይቻላል።»

ኮሮና ተሐዋሲ አፍሪቃ ውስጥ እስካሁን ወደግብፅ በአንድ ሰው አማካኝነት መግባቱ ተሰምቷል።  ኢትዮጵያ በበኩሏ ከጥር 15 ቀን 2012 ጀምሮ አደረኩ ያለችውን ጥንቃቄ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ በፌስቡክ አሰራጭቷል። እስካሁን ለኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል 60 ጥቆማዎች እንደደረሱት፤ ከእነዚህ ጥቆማቾ 17ቱ የቻይና የጉዞ ታሪክ ስላላቸው እና የበሽታው ምልክት ስለታየባቸው ለይቶ በማቆያ ማዕከል ማሰንበቱን፤ የላቦራቶር ምርመራ ተደርጎም ከተሐዋሲው ነፃ መሆናቸው ሲረጋገጥ ወደኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉንም ገልጿል። ኅብረተሰቡም በማሳል ወይም በማስነጠስ ጊዜ አፍና አፍንጫን በመሸፈን ጥንቃቄ እንዲያደርግ፤ የተጠቀሙበትን የአፍንጫ አፍ ማበሻም በየሜዳው እንዳይጥል የሚመክሩ መረጃዎችንም እያሰራጨ ነው። እጅን በውኃ እና ሳሙና መታጠቡ ሳይዘነጋ። ትኩሳት፣ ሳልና የመተንፈስ ችግር ሲያጋጥምም ላስቸኳይ የህክምና እርዳታ ነጻ በሆነው 83 35 በመደወል ርዳታ ማግኘት እንደሚቻልም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባሰራጨው መረጃ ጠቁሟል።

በነገራችን ላይ የተለያዩ አየር መንገዶች ተሐዋሲው ቻይና ውስጥ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለረዥም እና ቀጭር ጊዜያት በረራቸውን አቋርጠዋል። የአሜሪካ፣ የካናዳ፣ የአውሮጳ እንዲሁም የእስያ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት ታዋቂ  የአየር መንገዶች ይገኙበታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን ጉዞ አለመግታቱ ለብዙዎች የስጋት ምንጭ መስሏል። ለትምህርት ቻይና የሚገኙ ልጆቻቸው እንዲመለሱላቸው የጠየቁ ወላጆችም አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በየጊዜው የዓለምን ትኩረት የሳቡ የተሐዋሲ ወረርሽኞች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተደጋገሙ ተከስተዋል። አፍሪቃ ውስጥ ኤቦላ፤ እሲያ ደግሞ ሳርስ እና መርስ፤ አሁን ደግሞ ኮሮና ተሐዋሲ የበርካቶችን ሕይወት ስጋት ላይ ጥሏል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው መከላከያ ክትባት ለማግኘት ቢያንስ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ መጠበቅ ግድ ይሆናል። በዚህ መካከል ግን ሰዎች ራሳቸውን የሚከላከሉባቸው መሠረታዊ ጥንቃቄዎች ላይ ትኩረት ማድረጉ አማራጭ የለውም እና የጤና ጥበቃን መመሪያ ማስተዋሉ ይመከራል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic