የኮሪያ ባሕረ-ሰላጤ ፍጥጫ | ዓለም | DW | 18.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኮሪያ ባሕረ-ሰላጤ ፍጥጫ

ትራምፕ የባሕር ኃይል አጥቂ ቡድን ወደ ኮሪያ ባሕረ-ሰላጤ አዝምተዋል። ልጅ እግሩ ኪም ጁንግ ኡን በበኩላቸው በአያታቸው የልደት ቀን ''አኅጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሳይሆኑ አይቀሩም' የተባሉ ሚሳይሎች የታጠቀ ጦራቸውን በፒዮንግያንግ አደባባይ አሰልፈዋል። ተንታኞች የጠባይ መመሳሰል ይታይባቸዋል የሚሏቸው ሁለት መሪዎች በኮሪያ ባሕረ-ሰላጤ ተፋጠዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:03

የኮሪያ ባሕረ-ሰላጤ ፍጥጫ

በዕለተ-ቅዳሜ ማለዳ የሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ የኪም ኢል ሱንግ አደባባይ በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች ተሞልቷል። ልጅ እግሩ ኪም ጆንግ ኡን ከወታደራዊ ሹማምንቶቻቸው ጋር በአደባባዩ ተሰይመዋል። የወታደራዊ ማርሽ ባንድ ሙዚቃ ይሰማል። በሙዚቃው መካከል ሰሜን ኮሪያውያን ለመሪያቸው ኪም ጆንግ ኡን እና ለሃገራቸው ያላቸውን ታማኝነት የሚያረጋግጥ መፈክር በተደጋጋሚ ይደመጣል። 
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በአስደናቂ ሥነ-ሥርዓት በአደባባዩ ሰላምታ እየሰጡ አለፉ። በርካታ ቀይ ባንዲራዎች ያነገቡ ወታደሮች፤ የሰሜን ኮሪያ የቀድሞ መሪዎች ፎቶግራፎች የተሸከሙ ወታደሮችም በአደባባዩ ነበሩ። ጥቁር መለዮ የለበሱ እንስት ወታደሮች በወገባቸው ቦምብ ታጥቀው ተሰልፈዋል። ወንዶቹ ነፍጣቸውን አንግተዋል። ከሰማይ ተዋጊ የጦር አውሮፕላኖች ያንዣብባሉ። ከምድር የጦር ታንኮች፤የአየር መቃወሚያዎች በሰልፍ ይርመሰመሳሉ። ይኸ ሁሉ የሆነው የሰሜን ኮሪያ መስራች የኪም ኢል ሱንግ 105ኛ የልደት በዓል አከባበር ላይ ነው።
ቀኑ ዝም ብሎ ልደት ብቻ አይደለም። ሰሜን ኮሪያ ጡንቻዋን ለዓለም በተለይም ለአሜሪካ የምታሳይበት መድረክ እንጂ! በወታደራዊ ሰልፉ መካከል ብቅ ካሉት መካከል ሁለቱ አዳዲስ አኅጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳይሎች ሳይሆኑ እንደማይቀር ባለሙያዎች ጠርጥረዋል። የተሻሻሉ የሰርጓጅ መርከብ ላይ የሚጠመዱ ሚሳይሎችም በኪም ኢል ሱንግ አደባባይ ታይተዋል። ከወታደራዊ ሰልፉ በኋላ ፒዮንግያንግ ሌላ የተወንጫፊ ሚሳይል ሙከራ አድርጋለች። የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ የጦር ባለሥልጣናት ተወንጫፊ ሚሳይሉ በተተኮሰ ጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ፈንድቷል ብለዋል። የእስያ አገራት ጉብኝታቸውን በደቡብ ኮሪያ የጀመሩት ማይክ ፔንስ ሙከራውን «ጠብ ጫሪነት» ብለውታል። 

ሰሜን ኮሪያ ሁሌም ለጦርነት የምትዘጋጅ አገር ነች።የአገሪቱ መንግሥት የውጭ ኃይል ጥቃት በተለይ ከዩናይትድ ስቴትስ የሚሰነዘር እንዳንዣበበባቸው ሁሌም በመንገር ዜጎቹ ነቅተው እንዲጠባበቁ ይጎተጉታል። ያሰልፋል። ይኸ በሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ዘወትር የሚቀነቀን ሥጋት በዚህ ወር እውን ለመሆን የተቃረበ መስሏል። 
ይሕ ወቅት በዩ.ኤስ.ኤስ ካርል ቪንሰን የተዋጊ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ የሚመራው የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል አጥቂ ቡድን ከሲንጋፖር ወደ አውስትራሊያ የሚቀዝፍበት ነበር። አጥቂው የባሕር ኃይል አቅጣጫውን እና የመጀመሪያ እቅዱን ወደ ጎን አድርጎ ወደ ኮሪያ ባሕረ-ሰላጤ አቅንቷል።
ምዕራባውያኑ ተንታኞች እና የስለላ ተቋማት የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ያደረጋቸውን የሚሳይል ሙከራዎች እና የሳይበር ጥቃቶች እያጣቀሱ «በጥባጭ እና ጠብ ያለሽ በዳቦ» ባይ ነው እያሉ ይወቅሱታል። እንደ አምባገነን በራሱ ዜጎች ላይ ከሚያደርሰው 'አፈና እና ጭቆና' ባሻገር ድርጊቱ ለመላው የኮሪያ ልሳነ-ምድር ሥጋት ተብሎ ተፈርጇል። 
ሥልጣንን ከአባታቸው የወረሱት ልጅ እግሩ የኪም ጆንግ ኡንም የሚሳይል ሙከራዎቻቸውን ደብቀው አያውቁም። የኪም ጆንግ ኡን መንግሥት ከመስከረም እስከ ጥር ባሉት ወራት ብቻ አራተኛ እና አምስተኛ የኑክሌር አረር ተሸካሚ ሚሳይል ሙከራ ማድረጉን እና የመጀመሪያውን የሐይድሮጅን ቦንብ ማፈንዳቱንም ገልጧል። ምዕራባውያኑ ታድያ ሙከራዎቹን እየሰለሉ የጦር መሳሪያ ሙከራዎቹ የፈጠሩትን የመሬት መንቀጥቀጥ እየለኩ ማጣጣላቸው አልቀረም። በዕለተ-ቅዳሜ በፒዮንግያንግ አደባባይ የታዩት አኅጉር ተሻጋሪ ሚሳይሎች የኪም መንግሥት አሜሪካን በዒላማው ሥር ለማስገባት የሚያደርገው ጥረት ነው የሚሉት ባለሙያዎች አለመሞከራቸውን አንስተው ሲያጣጥሉ ይታያል። የሰሜን ኮሪያ ሚሳይሎች ደቡብ ኮሪያን፣ ጃፓንን ምን አልባትም በፊሊፒንስ ባሕር መካከል የምትገኘውን ጉዋም፤የተወሰነ የቻይና እና ሩሲያ ክፍሎችን የመምታት አቅም ሊኖራቸው እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሚሳይሎቹ የዩናይትድ ስቴትስን የባሕር ዳርቻዎች የመምታት አቅም ሊኖራቸው ይችላል የሚል ጥርጣሬ ቢኖርም በካቶ የጥናትና ምርምር ተቋም የፖሊሲ ተንታኙ ኤሪክ ጎሜዝ ግን አይስማሙም። የሰሜን ኮሪያ ሚሳይሎች ምን አልባት ብዙ ሕዝብ የማይኖርበት አላስካ ሊደርሱ ይችሉ ይሆናል የሚሉት ጎሜዝ ከዛ ያለፈ አቅም ይኑራቸው አይኑራቸው መረጃ የለም ሲሉ ይሞግታሉ። የዛሬ አመት በወርኃ የካቲት ፒዮንግያንግ የከተመው ሶሻሊስት መንግሥት አኅጉር አቋራጭ ሚሳይል ለመሥራት የሚያስችለውን ሙከራ አድርጓል። ሰሜን ኮሪያ ይኸን ሁሉ ስታደርግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀቦችን፤የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ማስጠንቀቂያዎችን የጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የቅጣት እርምጃዎችን ሁሉ ከቁብ ሳትጥፍ ነበር። የአለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ኃላፊ ዩኪያ አማኖ እንደሚሉት ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ በርትታ እየሰራች ነው።

«የዩራኒየም ማብላያ ነው ብለን የምንጠረጥረው አካባቢ ተጨማሪ ሕንፃ ሲሰራበት እና ሲስፋፋ በሳተላይት ለመመልከት ችለናል። ሰሜን ኮሪያውያን እናደርገዋለን ያሉትን እየተገበሩት ነው።»
የሰሜን ኮሪያ ተከታታይ የጦር መሳሪያ ሙከራዎች ይበልጥ የሚያሰጋቸው ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ሁልጊዜም ጎረቤት አገራቸውን በአይነ-ቁራኛ እንደጠበቁ ነው። አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በጥምረት የመሰረቱት የሰሜን ኮሪያ መከታተያ ድረ-ገፅ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው ዜና ደግሞ አገራቱን እንቅልፍ የሚነሳ ይመስላል። ድረ-ገፁ ባለፈው አርብ እንዳስነበበው ሰሜን ኮሪያ ስድስተኛ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ ለማድረግ ዝግጁ ነች። በሌላ መጠሪያው 38 ሰሜን ተብሎ የሚጠራው የዚህ ተልዕኮ ተንታኝ ጆሴፍ ቤርሙዴዝ እንዳሉት ሰሜን ኮሪያ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ያደረገችው እንቅስቃሴ ለሙከራው ዝግጁ መሆኗን ይጠቁማል። ይኸ ዜና የተሰማው የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሺንዞ አቤ ሰሜን ኮሪያ ሳሪን የተሰኘው ገዳይ ኬሚካል የተጠመደባቸው ሚሳይሎች ለመተኮስ የሚያስችል አቅም ሳይኖራት አይቀርም ካሉ በኋላ ነበር።
«ሰሜን ኮሪያ ሳሪን የተሰኘው ገዳይ መርዝ የተጫነ ሚሳይል ለመተኮስ የሚያስችል አቅም ሊኖራት ይችላል። አንዳንዶች የመከላከል አቅሙ ሊኖረን ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ። በተለይ በቅርቡ በሶርያ ሕፃናትን ጨምሮ ከ100 በላይ ሰላማዊ ሰዎች በመሰል ጥቃት ከተገደሉ በኋላ።» 

የኮሪያ እና አሜሪካ ውረድ እንውረድ 

በቀኝ ዘመሙ የፎክስ ቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው ስላዘመቱት ጦር የተጠየቁት የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰጡት ምላሽ ድፍን ያለ ግራ አጋቢም ነበር። በትዊተር ማኅበራዊ ድረ-ገፃቸው ባለፈው ማክሰኞ «ሰሜን ኮሪያ ነገር እየፈለገች ነው።» ያሉት ትራምፕ ቻይና የኮሪያ ልሳነ-ምድርን ቀውስ ለመፍታት እጇን ከዘረጋች በጸጋ እንደሚቀበሉ ገልጠዋል። ካልሆነ ግን ያለ ቻይና እገዛ «ችግሩን ራሳችን እንፈታዋለን» ብለው ነበር። ፕሬዝዳንቱ ወደ ኮሪያ ባኅረ-ሰላጤ ያዘመቱት አጥቂ ቡድን ስለሚወስደው እርምጃ ሲጠየቁ ግን ለመናገር ፈቃደኛ አልነበሩም። «ማንም ምንም አያውቅም» ነበር ያሉት። ስለ ዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይል ብቃት መመጻደቃቸውን ግን አልዘነጉትም። 

«ምን አይነት እርምጃ እንደሚወሰድ አታውቁም። አንድ እጅግ ኃይለኛ የጦር መርከብ ጓድ ልከናል። እጅግ ኃይለኛ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች አሉን። ከተዋጊ የጦር አውሮፕላኖች ተሸካሚ መርከብ የበለጠ ኃይለኛ። በምድር ላይ አሉ የሚባሉ ምርጥ ወታደራዊ መኮንኖች አሉን። ኪም ጆንግ ኡን የተሳሳተ ነገር እያደረገ ነው።» 
ለዘብተኛ አሊያም ግራ ዘመም የዓለም ፖለቲካን ተንታኞች፣ የትራምፕ እና ኪም ጆንግ ኡን አኳኋን አይጥማቸውም። በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ይኸ ነው የሚባል ልምድ እና እውቀት የላቸውም።ሁለቱም ለሥልጣን አዲስ ናቸው። ለደጋፊዎቻቸው የአመራር ክኅሎታቸውን ለማሳየት መንበራቸውንም ለመጠበቅ ይኳትናሉ።  የሰሜን ኮሪያ ሶሻሊስት መንግሥት መሪ ደግሞ ምላሻቸው «እንዋጋለን» ብለዋል።  ትራምፕ ወደ ኮሪያ ስለተጠጉት የባኅር ኃይላቸው ኃያልነት እንደሰበኩ ሁሉ የኮሪያ ማዕከላዊ ቴሌቭዥን ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስን እርምጃ «የሞኝ ዘመቻ» ሲል ወርፎታል። 
« ለሰላም ምንም ነገር አንለምንም። ነገር ግን በጠብ ጫሪዎች ላይ መልሰን እርምጃ እንወስዳለን።ራሳችንን እና የመረጥንውን መንገድ በኃይለኛ የጦር መሳሪያ ከጥቃት እንከላከላለን። ዩናይትድ ስቴትስ በወሰደችው ያልተገባ ተግባር ለሚፈጠረው አሰቃቂ ጥፋት ተጠያቂ እናደርጋታለን።» በርካታ ተንታኞች የኪም እና ትራምፕ ጠባይ መመሳሰል እንደሚታይበት ይስማማሉ። ምስስሎሹ ካስገረማቸው አንዱ በኤክስተር ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ኮሪያ ጉዳዮች ተመራማሪው አይዳን ፎስተር ካርተር ናቸው። 
«ሰሜን ኮሪያ ሁልጊዜም ትዕቢተኛ እና ጠበኛ ነች። አዲሱ ተጨማሪ ነገር ግን ዛቻ እና ማስፈራሪያ የሚወዱ ፕሬዝዳንት በዩናይትድ ስቴትስ መኖራቸው ነው። ትራምፕ በሰሜን ኮሪያ ላይ የሰነዘሩት ዛቻ ደግሞ በግልፅ ትርጉሙ የማይታወቅ ግን ደግሞ አሳሳቢ ነው። ለነገሩ ቀላል እምቢተኝነት ሊሆን ይችላል። ሲመዘን ባዶ ሆኖ የሚገኝ እንዲህ አይነት ቋንቋ እና ማስፈራሪያ በኮሪያ ሰላም ለማስፈን ይረዳል ብዬ አላምንም።»
ተመራማሪው ዶናልድ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያን ትጥቅ ለማስፈታት የአመራር ክኅሎቱም ሆነ አማራጩ እንደሌላቸው ያምናሉ። በእርሳቸው አባባል አሁን ትራምፕ የተከተሉት መንገድ ለቀጣናውም ሆነ ለአሜሪካ አጋሮች ፈፅሞ አያዋጣም።  «ትራምፕ ብዙ አማራጮች የሏቸውም። ከእርሳቸው የተሻለ የአመራር ክኅሎት ያላቸው የቀደሙት የአሜሪካ፤ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን እንዲሁም የቻይና መሪዎች ለ20 ወይም ለ30 አመታት ከሰሜን ኮሪያ እንቆቅልሽ ጋር ሲታገሉ ቆይተዋል። ጉዳዩ እጅግ አስቸጋሪ እና ውስብስብ ነው። ስህተቶች ቢሰሩም እንቆቅልሹ ከቁጥጥር ውጪ የሆነበት ምክንያት መፍትሔ ካለመፈለግ አይደለም። ጥሩ አማራጭ ስላልነበረ እንጂ። አሁን በፕሬዝዳንት ትራምፕ ታሳቢ የተደረገው ወታደራዊ መፍትሔ ደግሞ አሰቃቂ መከራ የሚያስከትል ነው። በተለይ ደግሞ በቀጣናው ለሚገኙት የአሜሪካ አጋሮች ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ከፍተኛ ቀውስ ይፈጥራል።» ትራምፕ በሶርያ የተዋጊ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የሚሳይል ድብደባ መፈጸማቸው ከሩሲያ ጋር አቃቅሯቸዋል። አወዛጋቢው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ሰሜን ኮሪያን ነካክተው ከቻይና ጋር ሌላ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት አያዋጣቸውም ይላሉ-ተንታኞች። በጀርመኑ ሜርካተር የቻይና ጥናት ማዕከል ተንታኙ ሐስን ማውል ትራምፕ «ኤኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ሊጠቀሙ ይችላሉ» ባይ ናቸው። 
«የትራምፕ አስተዳደር ከምር ወታደራዊ አማራጭ ለመጠቀም ዝግጁ ነው የሚለውን ነገር እጠራጠራለሁ። ፕሬዝዳንቱ በትዊተር መልዕክታቸው ዩናይትድ ስቴትስ ኤኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ለማጠናከር መፈለጓን ይጠቁማሉ። እነዚህ ማዕቀቦች ደግሞ ሰሜን ኮሪያን ብቻ ሳይሆን አብረዋት የሚሰሩ የቻይና ኩባንያዎችንም ይጎዳል። ወታደራዊ መፍትሔ በዩናይትድ ስቴትስ ከዚህ ቀደም እንደ አማራጭ ታይቶ ይታወቃል። ነገር ግን አብዛኛው የደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴዑል ክፍል በሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ሊመታ በሚችልበት ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ በጣም አደገኛ ነው። ሰሜን ኮሪያን ለማጥቃት ቢሞከር እጅግ ብዙ ሕዝብ ያልቃል።»

ቻይና ወታደራዊ ኃይል መጠቀም ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሜን ኮሪያ ጋር የገባችበትን እሰጥ አገባ ሊፈታ እንደማይችል በተደጋጋሚ አስታውቃለች። የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሉ ካንግ ወታደራዊ ኃይል ብቻ ሳይሆን የኤኮኖሚ ማዕቀብ እንኳ ቢሆን አገራቸው እንደምትቃወም ገልጠዋል።
«እንደሚመስለኝ አንድ ነገር ግልፅ መሆን አለበት። ቻይና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች አንድ አገር ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሚደረገውን ጥረት ሁልጊዜም ትቃወማለች። በተለይ በአንድ አገር ላይ የሚጣለው ማዕቀብ የቻይናን ጥቅም የሚጎዳ ሲሆን።» በኤክስተር ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ኮሪያ ጉዳዮች ተመራማሪው አይዳን ፎስተር ካርተር እንደሚሉት ግን የሰሜን ኮሪያ እምቢ ባይነት ለቻይና ሌላ ወታደራዊ ጥቅም ጭምር አለው።
«ከፈለገች በሰሜን ኮሪያ ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ ማሳደር የምትችለው ብቸኛ አገር ቻይና መሆኗ እሙን ነው። ቻይና፦ሰሜን ኮሪያ በንግዱ ከተቀረው ዓለም የምትገናኝባት መተላለፊያም ጭምር ናት። ነገር ግን ቻይና የአሜሪካ ወደ 28 ሺህ የሚጠጋ ጦር የምታስተናግደው ደቡብ ኮሪያን እንድትቀናቀን የኮሪያ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ተብላ የምትጠራው አገር እንድትኖር ትሻለች። ይኸ ደግሞ ከአሜሪካም ይሁን ከደቡብ ኮሪያ አቋም ፈፅሞ የተፃረረ ነው። ደቡብ ኮሪያ በአንድ ወር ውስጥ ምርጫ ታካሒዳለች። እስካሁን በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት ከሰሜን ኮሪያ ጋር ሰላም መፍጠር የሚፈልግ መሪ ይመረጣል የሚል ጥቆማ ሰጥቷል። ይኸ ደግሞ በአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ትብብር ላይ ሌላ ውጥረት ይፈጥራል።
የትራምፕ አስተዳደር እንደ ፎከረው በሰሜን ኮሪያ ላይ አንዳች ወታደራዊ እርምጃ ቢወስድ ቀጣናው የደኅንነት እና ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ መግባቱ አይቀርም።አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት የኪም ጆንግ ኡን መንግሥት ቢንኮታኮት የሚኖረውን ዳፋ አስቀድማ የተረዳችው ቻይና የኮሪያ ልሳነ-ምድርን ቀውስ ለመፍታት አጣብቂኝ ውስጥ የገባች ይመስላል። ኩነቱን ጊዜውን እየጠበቀ የሚያብጥ የፖለቲካ ትኩሳት አድርገው የቆጠሩትም አልጠፉም።


እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic