1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሚሽነሩ ጉብኝትና የጠቅላይ ሚንሥትሩ ሽልማት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 19 2010

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች አያያዝን የተመለከተው ጉብኝትና የቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአዲሱ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አኅመድ መሸለማቸው አነጋግሯል።

https://p.dw.com/p/2wmpX
Symbolbild Twitter
ምስል imago/xim.gs

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርን ዛይድ ራኣድ አል ሁሴን ለአራት ቀናት ጉብኝት ኢትዮጵያ በቆዩበት ወቅት ከሀገሪቱ የተለያዩ አካላት ጋር መነጋገራቸውን በተመለከተ  ዮሴፍ በርሃኔ ትዊተር ላይ ቀጣዩን ጽፏል።  «ታዋቂ የመብት ተሟጋቾች፣ ጦማሪያን፣ ፖለቲከኞች እና የሃይማኖት አባቶች ከተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጋር መነጋገራቸው ጥሩ ነው።» ከዮሴፍ የትዊተር መልእክት ጋር ፎቶግራፍም ተያይዟል። ፎቶግራፉ፦የኃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟጋቾች ይታዩበታል።

ከዞን ዘጠኝ የድረገጽ ጸሐፍት አባላት አንዱ የኾነው ናትናኤል ፈለቀ እዛው ትዊተር ላይ ባሰፈረው መልእክት «ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዶክተር ዛይድ ራኣድ አል ሁሴን ጋር በመገናኘቴ ክብር ይሰማኛል» ብሏል። ናትናኤል ከኮሚሽነሩ ጋር ተጨባብጦ የሚታይበት ፎቶግራፍ ከመልእክቱ ጋር አያይዟል።

ኮሚሽነሩ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ፤ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከተለያዩ የሲቪል ማኅበራት መሪዎች፣ እንዲሁም በቅርቡ ከእስር ከተፈቱ ታዋቂ ግለሰቦች ጋር መገናኘታቸውም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ከፎቶግራፍ ምስሎች ጋር ቀርቧል።  

ኮሚሽነሩ ንግግር በሚያሠሙበት ወቅት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ ይደረግ እንደነበር በመጥቀስ ንግግሩን ፋይዳ የለውም ሲሉ የተቹ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችም ነበሩ። ማር ነች በሚል የፌስቡክ ገጽ የቀረበ አስተያየት «አሁን እንባ አየተንጠባጠበ አይደል ተማሪ ከመበደል ጥያቄ መመለስ» ሲል ይነበባል። ይርጋለም ሐጎስ «ሰብአዊ መብት ካካካካካካካካካ እውነት ነው ግን ሰብአዊ መብት የሚለውን ራሳቸው ያውቁት ይሆን ሲል ቶማስ ወንድሙ በአጭሩ «ወይ ሰብአዊ መብት» ብሏል።

የኮሚሽነሩ ጉብኝትን በተመለከተ በዋትሰአፕ የደረሱን የጽሑፍ መልእክቶች በርካታ ናቸው።

Äthiopien Amtseinführung neues Kabinett durch  Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Reuters/T. Negeri

«በኢትዮጵያ የሰብአዊ  መብት ጥሰት ብዙም አይደለም። ይህንን አጉልተው የሚናገሩት በሀገሪቱ ሰላም እንዳይኖር የሚፈልጉ ናቸው በነገራችን ላይ እኔ የማንኛውም ደጋፊ አደለሁም።»

«ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡን ትኩረት አድርጎ መረጃ መያዝ አለበት ባለሥልጣኑን መሰረት ማድረግ አይገባም»

«የዜጎች ሠብአዊ መብት እንዲከበር አሥተዋፅኦ ይኖራቸዋል።» 

«ከኮሚሽነሩ ምንም አንጠብቅም። ለሰላማችን እና ለመብት ጥሰቱም እንድንቆም መሥራት ያለብን  እኛው እትዮጵያ ነን። ትናንት የት ነበሩ ዛሬ ከብዙ መስዋዕትነት በኋላ ጭላንጭል መታዬት ስጀምር የሚረባረቡት። ሆኖም ግን በአንድ ነጥብ እስማማለሁ፡ እነዚያን ነፍስ በሊታዎችን፤ ወገኖቻችንን በእስር ያሰቃዩትን ለፊትኅ የሚያቀርቧቸው ከሆነ እሰየሁ ያስብላል።»

በእንግሊዝኛ የደረሰን የዋትስአፕ መልእክት ደግሞ እንዲህ ይላል፦ «የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በሕወሓት የወታደራዊ እና የደኅንነት አካላት በኢትዮጵያ ሶማሌ እና ኦሮሞ ህዝቦች መካከል የነበረውን ችግር ጨምሮ ሠላማዊ ሰዎች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ያደረሱትን ወንጀል መመርመር አለባቸው።» 

USA | United Nations High Commissioner for Human Rights Zeid Ra'ad al Hussein
ምስል imago/Xinhua

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራኣድ አል ሁሴን ቀደም ሲል የዛሬ ዓመት ግድም ኢትዮጵያን ጎብኝተው ነበር። በያኔው ጉብኝታቸው ወቅትም ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንሥትር እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ጋር ስለ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ተነጋግረው እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት መግለጫ አትቷል። 

የቀድሞ ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ «ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ» የተባለውን ሽልማት መሸለማቸውን በተመለከተ የትናየት ጥላሁን ፌስቡክ ላይ «በጣም ደስ የሚል» ስትል አድናቆቷን ገልጣለች። «አንዱ አንዱን አክብሮ፣ አመስግኖ መሸኘት ለሌሎችም ትምህርት ስለሚሰጥ ከዚህ ሁሉም አመራር መማር አለባችሁ / አብይን አመሰግናለሁ። እንዲሁም አቶ ኃይለማሪያም ሥልጣን ለመልቀቅ በፈቃደኝነት ላደረጉት አስተዋፅኦ እጅጉን ሊመሰገኑ ይገባል። ቀሪ ዘመነዎትም ጥሩ እንዲሆንለዎት እመኛለሁ» ብላለች።

የአዲስ ነገር ጋዜጣ የቀድሞ አዘጋጅ መሥፍን ነጋሽ በዚሁ ጉዳይ ላይ ባቀረበው ትችት፦ «ሕግ የማያውቀው መንግሥታዊ ሽልማት፣ ብሔራዊ ባንክ የማያውቀው ብር ነው» ሲል የዋዜማ ራዲዮ ድረገጽ ላይ ጽፏል። «/ አብይ አህመድ ለቀድሞው / ኀማደከፍተኛ የክብር ዲፕሎማእና ለወ/ ሮማን ደግሞየእውቅና የምስክር ወረቀትመስጠታቸውን አየን፣ ሰማን። ወደዝርዝሩ ሳንገባ፣ አንድ የአገር መሪ ተሰናባቹን በክብር ሲሸኝ፣ ለክብሩ የራት ግብዣ ሲያደርግ ማየት በጣም መልካም ነገር ነው። ለአገራችንም እጅግ እንግዳ ባህል ነው። የክብር ኒሻን ወይም ሜዳይ መስጠት ግን ፍጹም የተለየ ጉዳይ ነው። ሁለቱን ማምታታ አያስፈልግም» ብሏል መሥፍን። ስለሽልማቱ የእንግሊዝኛ ትርጉም ሰንካላነት፣ መሰል ሽልማት በሕጉ መሠረት ማን መስጠት እንዳለበት እንዲሁም ሽልማቱ በየትኛው ሕግ መሠረት እንደተሰጠም ጠይቋል። «ወግ ያለው፣ በሰጪውም በተቀባዩም፣ እንዲሁም በሕዝቡ የሚከበር ነገር ከፈለጋችሁ በቅድሚያ ሕግ፣ ሥርአት እና ሥነ ሥርአት አቋቁሙ። ከግርግርና ከዘማቻ ባህል ውጡ» ሲልም አክሏል።

ደራሲ እና ገጣሚ ዮሐንስ ሞላ፦ «ይኽ በእንዲህ እንዳለ፥ አምባገነኑ ስርዓት ሰፈር ሄዶ ማድነቅ ግድ ሲል፣ በቀዳማዊት እመቤትነት ዘመናቸው፣ ከእዩልኝ ስሙልኝ ባለፈ በርካታ የማኅበረሰብ ሥራዎችን ላከናወኑት / ሮማን ተስፋዬ ክብርና ምስጋና ይድረስልን» ብሏል የቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር ባለቤትን በማድነቅ። «መቼም ነገራችን ሁሉ ንጽጽር ነውና፥ እንኳን የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት / አዜብ መስፍን ጋር ሄደን፣ ከባለቤታቸውም ጋር ቢነጻጸሩ ሚናቸው ጉልህ ነበር» ሲልም አክሏል ዮሐንስ።

Seyoum Teshome
ምስል Geberu Godane

የአበበ መገርሳ የፌስቡክ መልእክት ድጋፍም ትችትም የተቀየጠበት ነው። ጽሑፉ እንዲህ ይነበባል፦  «/ማርያም ምንም ከወንጀል ነጻ ባይሆኑም በሁለት ነገር ክብር ይገባቸዋል። አንድም ሀገሪቱ ዉስጥ ሌብነት በተንሰራፈ ጊዜ እሳቸው እንደሌሎቹ እጃቸው በሌብነት ያልተጨማለቀ ሲኾን፣ 2 ሥልጣናቸውን በሰላም መልቀቃቸው ያስመሰግናል፡፡ ስለዚህ ክብር መስጠቱ አያስከፋም፡፡ ምናልባት ሥልጣናቸውን በፍቃዳቸው ባይለቁ ኖሮ አሁን ባንጻሩ የምናየዉን ሠላም አናይ ይሆናል» ብሏል፡፡ በዋትስአፕ የደረሰን የድምጽ መልእክት ግን «ጉልቻ ቢቀያየር…..» ይላል።

የዩኒቨርሲቲ መምሕር እና ጦማሪ ሥዩም ተሾመ፦ «ለተተኪው /ሚኒስትር ትልቅ ውለታ መዋልና ለሀገር ውለታ መዋል ለየቅል ናቸው» ሲል ሽልማት አሰጣጡን ተችቷል። ለምሳሌ ሲልም ጽሑፉን ማብራራቱን ይቀጥላል። «ለምሳሌ / ሃይለማሪያም ደሳለኝ እንደ ሀገር መሪ በራሳቸው ምንም መወሰን የተሳናቸው በጣም ደካማ የአመራር ብቃት ያላቸው መሆኑ እርገግጥ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በሥልጣን ዘመናቸው በሀገርና ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ይህን ተከትሎ በተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ ለዶ/ አብይአህመድ ምቹ በሆነ ግዜና ሁኔታ ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል፡፡ ይህ የቀድሞውን /ሚኒስተር ከተጠያቂነት ከማዳን አልፎ ለከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ የሚያበቃቸው ከሆነ ሸላሚዎቹ የሀገር ወይም የክብር ትርጉም ጠፍቶባቸዋል፡፡ ለፍርድ መቅረብ ያለበትን ሰውዬ የክብር ሜዳሊያ መሸለም ትንሽ አይከብድም? / አብይ ማኖ ነክተዋል! "አንድ" በሉልኝማ!!??» ሲል ሥዩም ጽሑፉን አሳርጓል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ