የኮሌራ በሽታ ስርጭት በኦሮሚያ | ኢትዮጵያ | DW | 26.09.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኮሌራ በሽታ ስርጭት በኦሮሚያ

ኦሮሚያ መስተዳድር ሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ የነበሩ አንድ ሰዉ ትናንት በብሽታዉ መሞታቸዉ ተዘግቧል።የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ወረርሽኙን ለመግታት እየጣረ መሆኑን አስታዉቋል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:18

የኮሌራ ስጭት በኦሮሚያ

           
ኢትዮጵያ ዉስጥ ርዕሠ-ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአካባቢዎች ከአራት ወራት በፊት የተከሰተዉ የኮሌራ በሽታ አሁንም የጤና ሥጋት እንደሆነ ቀጥሏል።ኦሮሚያ መስተዳድር ሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ የነበሩ አንድ ሰዉ ትናንት በብሽታዉ መሞታቸዉ ተዘግቧል።የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ወረርሽኙን ለመግታት እየጣረ መሆኑን አስታዉቋል።ይሁንና ወቅቱ ለበሽታዉ መዛመት አመቺ በመሆኑ ሕዝቡ እንዲጠነቀቅ ቢሮዉ አሳስቧል።

በኦሮሚያ ክልል የበሽታው  ምልክት ከታየበት ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ የረቡዕ መስከረም 15 ቀን፤ 2012 ዓ.ም  ሳይጨምር የአስር ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ለዶይቸ ቬለ (DW) ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ የታማሚዎች በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋማት አለመምጣት መሆኑን ገልጸዋል።

«እንደሚታወቀው ከአራት ወራት በፊት ነበር ይህ በሽታ በሌሎች ክልሎች የተከሰተው። መጀመሪያ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች ነበር የታየው ።ከዚያም ወደ ክልላችን ተዛምቶ መጀመሪያ ቦረና ነበር የታየው ፤ ከዚያ ወደ ምእራብና ምስራቅ ሃረርጌ ተዛመተ ፤ እንዲህ እያለ ወደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መዛመት ቻለ ። በአጠቃላይ ባለፉት ሶስት ወራት ከ652 በላይ ሰዎች ላይ ይህ በሽታ ተገኝቶባቸዋል።»

«ከእነዚህ ውስጥም ዐሥር ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። አብዛኞቹ ሕይወታቸው ያለፈው እቤታቸው ነው። ወደ ህክምና ተቋም ባለመምጣታቸው ነው። የተወሰኑት ደግሞ ለምሳሌ ትናንት በሻሸመኔ አንድ አዛውንት በበሽታው አርፈዋል ፤  እስከ ሦስት ቀን ውስጥ ወደ ህክምና ባለመምጣታቸው ነው።»

በኦሮሚያ ክልል በተለይ በምእራብ አርሲ ዞን የሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ወረዳዎች የወረርሽኝ ስጋት አይሎ መስተዋሉን የሚናገሩት ዶ/ር ደረጀ ምንም እንኳ በጥቂት ወረዳዎች ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ቢቻልም በተቀሩት ወረዳዎች ያለው ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ ነው ይላሉ።

«በሽታው ምእራብ አርሲ ውስጥ ተገኝቷል።  አራት ወረዳዎች ውስጥ ተከስቷል።  ከአራት ወረዳዎ

ች ውስጥ በሁለቱ መቆጣጠር ችለናል፤ ሁለቱ ላይ ግን  [አኹንም ] በሽታው ይታይባቸዋል።  ሻሸመኔ ከተማና ሻሸመኔ ወረዳ ላይ ይታያል።  አሁን በተያዘው ሥራ ግን በቀላሉ መከላከል እንችላለን ብዬ አስባለሁ፤  ምክንያቱም ብዙ ኮሚቴዎች ተዋቅረው አመራሩ ሙሉ በሙሉ እየሠራ ነው የሚገኘው ፤ በተለይ ከከተማው የሚወጣው ወንዝ ስለተበከለ በሁለቱ ወረዳዎች በሸታው እንዲተላለፍ እያደረገ ነው። ለዚህም ውኃውን የማጥራት ሥራ እየተከናወነ ነው። »

የኮሌራ ወረርሽን ከንጽህና ጉድለት ፣ በተለይ ከውኃ መበከል ጋር ተያይዞ የሚከሰት በመሆኑ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ይላሉ ቢሮ ኃላፊ። ከክልሉ ባሻገር በሌሎች አጎራባች ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ በጋራ የተቀናጀ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል ሲሉ አክለዋል።

«የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሠሩ ነው የሚገኙት፤ ከዚህ ውጪ ውኃ የሚያክሙ ኬሚካሎችን በስፋት እያሰራጨን ነው የምንገኘው፤የጤና ኤክስቴንሽን እና የጤና ባለሞያዎችን በመደብ ህክምና እየተደረገ ነው የሚገኘው። ሐዋሳ ከተማም በሽታው ስለተገኘ የመዛመት ሁኔታዎች ስለሚኖር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።»

በሽታው በኢትዮጵያ እስካሁን በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ከ680 በላይ የህመሙ ምልክት የታየባቸው ሰዎች ሲገኙ፤ ቁጥራቸው ከ20 የሚሻገሩትን ደግሞ ለሞት ዳርጓል።

ታምራት ዲንሳ 

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

Audios and videos on the topic