የክርስቲያኖች በጎ ተግባር በረመዳን | አፍሪቃ | DW | 24.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የክርስቲያኖች በጎ ተግባር በረመዳን

የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ሃላፊ ቄስ ዮሃናና ከ 30 በላይ የሚሆኑ የመሰል አብያተ ክርስቲያን ባልደረቦች የገንዘብ ቅጣቱን እና መከፈል የነበረበትን የዋስ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን እሥረኞቹ ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ወጪም ሸፍነዋል ።

ከናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ በስተሰሜን የምትገኘው ትልቋ ከተማ ካዱና ባለፉት 10 ዓመታት በክርስቲያኖችና ሙስሊሞች መካከል የሚካሄድ ደም አፋሳሽ ግጭት ተምሳሌት ሆና የምትታይ ከተማ ነበረች ። በወቅቱ ሁለቱም ሃይማኖቶች ተፅእኖ ለማድረግና የበላይነትን ለመያዝ ባካሄዱት ትግል በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ። አሁን ግን ሁኔታዎች ተለውጠዋል ። በዘንድሮው ረመዳን እንኳን አንድ የአካባቢው ቄስና በጎ ፈቃደኞች ሙስሊም እስረኞች የረመዳንን ወር በቤታቸው እንዲያሳልፉ ዋስ ሆነው አስለቅቀዋቸዋል ።

ቄስ ዮሃና ቡሮ ና አንድ የበጎ ፈቃደኖች ቡድን ከሰሜን ናይጀሪያዋ ከተማ ካዱና 30 ሙስሊም ወንድ ና ሴት እስረኞችን ነበር የገንዘብ ቅጣታቸውን በመክፈልና ዋስ በመሆን ያስለቀቁት ። ይህን ያደረጉትም እስረኖቹ ረመዳንን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲፆሙ በማሰብ ነው ። በካዱና ፌደራል ክፍለ ሃገር እሥር ቤት ውስጥ የተያዙት እነዚህ እስረኞች የተጣለባቸውን የገንዘብ ቅጣት ወይም በዋስትና ማስያዝ የሚገባቸውን ገንዘብ መክፈል ባለመቻላቸው ነበር የታሰሩት ።

እና አሁን የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ሃላፊ ቄስ ዮሃናና ከ 30 በላይ የሚሆኑ የመሰል አብያተ ክርስቲያን ባልደረቦች የገንዘብ ቅጣቱን እና መከፈል የነበረበትን የዋስ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን እሥረኞቹ ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ወጪም ሸፍነዋል ። በቄስ ዮሃና እምነት ፀሎትና ፆም ለሠላም አስተዋፅኦ አለው ።

« የረመዳን ፆም ከአምስቱ አበይት የእስልምና መሠረቶች አንዱ ነው ። በዚህ የጾም ወቅት እኛ ክርስቲያኖች በችግር ላይ ያሉ ሙስሊሞችን ስንረዳ እንደሰታለን ። ሙስሊም ወንድሞቻችን መፆምና በሃገራቸው ሠላም እንዲሰፍንም መፀለይ እንዲችሉ ይለቀቁ ዘንድ ጥረት አድርጌያለሁ ። በቁርዓንም ይሁን በመፀሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰውን ሃያማኖታዊ ግዴታችንን መወጣት ይገባናል ።»

ቄስ ቡሮና ሌሎችም ክርስቲያኖች ናይጀሪያ ውስጥ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል የተሻለ የሰመረ ግንኙነት እንዲኖር ይፈልጋሉ ። ይሁንና እውነታው የተለየ ነው ። ከአፍሪቃ በህዝብ ብዛት አንደኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው በናይጀሪያ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች እንዲሁም በተለያዩ ጎሳዎች መካከል ግጭቶች ይከሰታሉ ። ከሁለቱም ወገኖች ሰዎች ይሞታሉ ። አብያተ ክርስቲያንም ሆነ መስጊዶች ይቃጠላሉ ። እነዚህን የመሳሰሉ አሳዛኝ ድርጊቶች በሚፈፀሙባት በናይጀሪያ ቄስ ቡሮና ሌሎች ደጋፊዎቻቸው ያከናወኑት በጎ ተግባር ሙስሊም የሃይማኖት አባቶችንና የካዱና ነዋሪዎችንም አስደስቷል አስደምሟልም ። ሼክ ሳሊሁ ማይ ባሮታ የካዱና ነዋሪ ሙስሊም የሃይማኖት አባት ናቸው ። ለተለቀቁት ሙስሊሞች ባሰሙት ንግግር እንዳሉት በጎው ተግባር ለሁሉም አርአያ ሊሆን ይገባዋል ።

«ቄስ ቡሮ ያከናወኑት ተግባር ለሁላችንም በተለይ በሰላም አብሮ ስለመኖር በራድዮ ለሚናገሩ ባለሥልጣናትና የሃይማኖት መሪዎች ምሳሌ መሆን አለበት ። ዛሬ ሙስሊሞች እንዲለቀቁ ያበቃው አንድ ክርስቲያን ቄስ መሆኑ ሁላችሁንም ሳያስገርማችሁ አይቀርም ።»

ማርያም አቡበከር በሙስሊሞችና በክርስቲያኖች መካከል ሰላምና መግባባት እንዲሰፍን የሚጥረው የሴቶች ድርጅት ሃላፊ ናቸው ። የቄስ ቡሮ ተግባር ሌሎችንም እንደሚያነሳሳ ጥርጥር የላቸውም። ከዚህ ውጭ ግን የናይጀሪያ ወህኒ ቤቶች ይዞታ በእጅጉ ያሳስባቸዋል ።

« እስረኞች የተፈረደባቸውን ጊዜ በእሥር ቤቶች ውስጥ የሚያሳልፉበት ሁኔታ በጣም ያሳዝነኛል ። ስለዚህ ሁሉም ክርስቲያኖችም ሙስሊሞችም በተቻላቸው መጠን እስረኞችን እንዲረዱ ጥሬ አቀርባለሁ ።»

ነፃ የወጡት እስረኞችም የእስር ቤቱ ይዞታ አስከፊ መሆኑን ነው የተናገሩት ።

« ፍየል ገጭቼ የተፈረደብኝን 1000 ናይራ ወደ 50 ዩሮ በአንድ ወር ውስጥ መክፈል ባለመቻሌ ነው የታሰርኩት ። 240 ቀናት መቆየት አለብኝ ። እዚህ አያያዛቸው ሰብዓዊነት ይጎድለዋል ።»

« ማንም ፣ ጠላቴም ቢሆን እዚህ እንዲመጣ አልመኝም ፤ በእውነት እዚህ ቤት ውስጥ መሆን ጥሩ አይደለም ። »

የካዱና እሥር ቤት ጠባቂዎችም እሥረኞቹ ያሉት እውነት መሆኑን አረጋግጠዋል ። በዚህ አጋጣሚም ባለሃብቶች መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለአሥረኞች ምግብ ልብስና ንፅህን መጠበቂያ በመለገስ እንዲታደጓቸው ጥሬ አስተላልፈዋል ።

ኢብራሂማ ያኩባ

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic