የኬንያ ፕ/ምርጫ እና የኬምብሪጅ አናሊቲካ ተቋም ሚና  | አፍሪቃ | DW | 21.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የኬንያ ፕ/ምርጫ እና የኬምብሪጅ አናሊቲካ ተቋም ሚና 

ኬምብሪጅ አናሊቲካ የተባለው መረጃዎችን የሚገመግመው የብሪታንያውያን አማካሪ ተቋም በሚልዮን የሚቆጠሩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃዎች ካለፈቃዳቸው በመውሰዱ በወቅቱ ትልቅ ወቀሳ ተፈራርቆበታል። እንደ ብሪታንያ ቴሌቪዥን ቻነል 4 ዘገባ፣ ተቋሙ የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በ2017 ዓም ድጋሚ በተመረጡበትም ምርጫ ላይ እጁ አለበት ነው የተባለው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:04

የኬንያታ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ስራቸው ግልጽ ካልሆነ አማካሪ ተቋማት ጋር በተገናኘ ስሙ አዘውትሮ ይነሳል።

የብሪታንያ ቴሌቪዥን  ቻነል 4 በኅቡዕ የቀረጸው ቪድዮ የኬምብሪጅ አናሊቲካ ኩባንያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተቋሙ በኬንያ የ2017 ዓም አከራካሪ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ ስለተጫወተው ሚና ሲናገሩ ያሳያል። የኬምብሪጅ አናሊቲካ ኩባንያ እና ስትራተጂክ ኮምዩኒኬሽን ላብራቶሪስ ግሩፕ የተባለው እህት ተቋም አስተዳደር ዋና ኃላፊ ማርክ ተንበል ፣ « የፓርቲውን አሰራር በጠቅላላ ሁለቱ ጊዜ ቀያይረናል። ማኒፌስቶውንም ጽፈናል፣ የምርምር ጥናት፣ ግምገማ አካሂደናል፣ መልዕክቶችን አሰራጭተናል። ዲስኩሮችን ሁሉ የጻፍን እና ይህን እጩ የሚመለከተውን ነጥብ በጠቅላላ በዲስኩሮቹ ያጎላን ይመስለኛል።» በማለት ነበር ኅቡዕ ዘገባ ላዘጋጀው የቻነል 4 ጋዜጠኞች ቡድን የተናገሩት። ተንበል ያሏቸው እጩ ዋነኛ ተፎካካሪያቸውን ራይላ ኦዲንጋ ከጠንካራ የምርጫ ዘመቻ በኋላ ባለፈው ነሀሴ ወር ማሸነፍ የተሳካላቸው የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ናቸው።

ይህንኑ ድላቸውን የሀገሪቱ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ምርጫው ያልተስተካከለ አሰራር ታይቶበታል በሚል ውድቅ ቢያደርግም፣ ኬንያታ በጥቅምቱ ድጋሚ ምርጫ አሸንፈዋል። ከምርጫው በኋላ በተፈጠረ ግጭት ብዙዎች መገደላቸው እና የመብት ተሟጋች ቡድኖች ፖሊስ በተቃዋሚ ደጋፊዎች ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅሟል ሲሉ መውቀሳቸው ይታወሳል። 
የቻነል 4 ቪድዮ ኬምብሪጅ አናሊቲካ ለኬንያታ የምርጫ ዘመቻ ሰጥቶ ሊሆን ይችላል የሚባለውን አገልግሎት አልገለጸም። ይሁን እንጂ፣ ኬምብሪጅ አናሊቲካ የዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዘመቻን ለመርዳት ሲል የ50 ሚልዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ ለራሱ ጥቅም አውሏል በሚል በብሪታንያ እና በዩኤስ አሜሪካ ወቀሳ ከተፈራረቀበት ወዲህ ኬንያውያን ኩባንያውን በጥርጣሬ መመልከት ጀምረዋል። በቻነል 4 ቪድዮ እንደታየው፣ የተቋሙ ባለስልጣናት ፖለቲከኞችን ችግር ላይ ሊጥሏቸው የሚችሉ ፣ ጉቦ ሲቀበሉ ወይም ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ሲገናኙ የሚያሳዩ ወጥመዶችን የመፍጠር፣ እንዲሁም፣ ስለነሱ በኢንተርኔት ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ የማስፋፋት አቅም እንዳላቸው እና በተለያዩ  ሀገራት ምርጫዎችም ላይ በእነዚህ ዘዴዎች መጠቀማቸውን እንደ ጉራ ተናግረዋል። ይህ የተቋሙ አሰራር በኬንያውያን ዘንድ ትልቅ ቅሬታ እንደፈጠረ አርቲክል 19 በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የምሥራቅ አፍሪቃ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን ዋና ኃላፊ ሄንሪ ማይና ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። የኬንያ ድረ ገጽ ጸሀፍት ማህበር ባልደረባ ሺቴሚ ኻማዲም ለኪስዋሂሊ ክፍል እንዳለው፣ በአምናው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ወቅት በርግጥ ሀሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በብዛት ተነበዋል።

« ብዙው መልዕክት በኬንያ ካሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ጥላቻን በሚያስተጋቡ ኃይለ ቃላት የተሞላ ነበር።  »
እርግጥ፣ በውጭ ጣልቃ ገብነት የተደረገ ለመሆኑ ማረጋገጫ እንደሌለ ቢናገርም፣ የውጭ እጅ ሳይኖርበት እንዳልቀረ ነው የሚገምተው። « በፌስቡክ፣ ጉግል እና በትዊተር የተነበቡት መልዕክቶች በጣም ቁጣን የቀሰቀሱ እና ራይላ ኦዲንጋን ዒላማ ያደረጉ ነበሩ፤ ምክንያቱም ተጨማሪ የጁብሊ ደጋፊዎች በብዛት በመውጣት ድምፃቸውን ለእጩዎቻቸው እንዲሰጡ ለመቀስቀስ የታሰበ ነበር።  » 
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ከ48 ሚልዮኑ የኬንያ ሕዝብ መካከል 30 ሚልዮኑ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው። የጁብሊ ፓርቲም ስለቻነል 4 ዘገባ የሰጠው አስተያየት የለም። ስለሚሰማው ወቀሳ አስተያየት መስጠቱ፣ እንደ ሄንሪ ሜይና አመለካከት፣ ቀላል አይሆንም። የኬንያታ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ስራቸው ግልጽ ካልሆኑ አማካሪ ተቋማት ጋር በተገናኘ ስሙ ሲነሳ ያሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
« የሕዝቡ ቅሬታ በጣም ከፍ ያለ ነው። ለዚህ መልስ የመስጠቱ ጉዳይ ለፓርቲው እንደማይከብደው አስባለሁ፣ ጁብሊ ራሱን ሕግን እንዲሁም የዜጎችን አስተያየት እንደሚያከብር ፓርቲ አድርጎ ስለሚመለከት።  ይሁንና፣ ይህ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖበታል። »
ተቋሙ  ወቀሳውን በጠቅላላ  አስተባብሏል። ባለስልጣናቱም ሲቀልዱ የተናገሩት እንደነበር ነው ያስታወቁት። እንደ ሄንሪ ሜይና  ግምት፣ በኬምብሪጅ አናሊቲካ ላይ የተሰነዘረው ወቀሳ እውነት ከሆነ፣ ይህ ብዙ አፍሪቃውያን በአህጉሩ የፖለቲካ ስርዓት ላይ ያላቸውን እምነት ይበልጡን ይቀንሳል።
« አፍሪቃ ውስጥ ዴሞክራሲ እየቀጨጨ በመሄድ ላይ መሆኑን እናውቃለን። ይህም ትልቅ ችግር ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ዜጎች መንግሥታቸው ወደ ስልጣን የመጣው የነሱን ድምፅ አግኝቶ ሳይሆን፣ ባንዳንድ፣ በተለይም መንበራቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ፣ አስተሳሰብን የመዘወር እና ትክክለኛ ያልሆነ መረጃን የማስፋፋት አቅም ባላቸው ኩባንያዎች ስራ ሰበብ ነው ብለው ማሰባቸውን ይቀጥላሉና። » 

አርያም ተክሌ/ጄን አዬኮ ኩሜት/ዩስራ አብደላ ቡዋይሂድ

ሂሩት መለሰ 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች