የኬንያ ፕሬዚደንት የአንድ ዓመቱ የሥልጣን ዘመን | አፍሪቃ | DW | 14.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የኬንያ ፕሬዚደንት የአንድ ዓመቱ የሥልጣን ዘመን

የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ሥልጣን ከያዙ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ለሀገራቸው ሕዝብ ለማሟላት የገቡትን ቃል መጠበቅ ተስኗቸዋል። በሀገሪቱም የፀጥታው ስጋት እየጨመረ ሄዷል።

የኬንያ መሥራች አባት የሆኑት የመጀመሪያው የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ጆሞ ኬንያታ ልጅ፣ ኡሁሩ ኬንያታ የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን ከያዙ ከሁለት ቀናት በፊት ልክ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከኬንያታ ብሔራዊ ህብረት ፓርቲ፣ ከዊልያም ሩቶ የተባበረው ሬፓብሊካውያን ፓርቲ ፣ ከቻሪቲ ንጊሉ የናርክ ፓርቲ እና ከናዢብ ባላላ የሬፓብሊካውያን ኮንግረስ የተጠቃለሉበት የጁብሊ ጥምረት የሚመራው የፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ መንግሥት የሚጠበቅበትን እንደሚፈለገው አላከናወነም በሚል ከፖለቲካ ተቃዋሚዎቹ እና ከብዙ የህብረተሰብ አባላት ብርቱ ወቀሳ ተፈራርቆበታል።እአአ ሚያዝያ ዘጠኝ፣ 2013 ዓም ቃለ መሀላ በፈፀሙበት ጊዜ በሀገራቸው የኤኮኖሚ ዕድገት ለማስገኘት፣ ብሔራዊውን አንድነት ለማጠናከር፣ የጤና ጥበቃውን አገልግሎት ለሁሉም በናፃ ለማዳረስ፣ የምግቡን ዋስትና ለማረጋገጥ፣ ለወጣቱ ትውልድ የስራ ቦታ ለመፍጠር እና ለያንዳንዱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ላፕቶፕ ለማቅረብ ቃል ገብተው ነበር።

ከዚሁ መካከል እስካሁን ተግባራዊ ማድረግ የተሳካላቸው ጥቂቱን ብቻ ነው። የምግብ ዋጋ በጣም ተወዶዋል። የወጣት ስራ አጦችም ቁጥር አሁንም እንደበፊቱ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ለያንዳንዱ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ላፕቶፕ ለማደል የተወጠነውም ዕቅድ በሙስና ቅሌት ወደኋላ ተገፍቷል። የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚንስትር እና የ ራይላ ኦዲንጋ የፕሬዚደንት ኬንያታ መንግሥት እስካሁን ያሳየው አመራር አጥጋቢ አለመሆኑን ለአንድ የዩኤስ አሜሪካ ራድዮ አስታውቀዋል። ሲቭሉን ህብረተሰብ በመወከል በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢንችኪርዋ ንዴዤሌይ ተከታዩን አስተያየት ነበር የሰጠችው።

«የጁብሊ መንግሥት በቂ አልሰራም። እና ፕሬዚደንቱም የገቡትን ቃል ጠብቀዋል ብየ አላስብም፤ ምክንያቱም ፣ ብዙ ለመስራት ነበር ቃል የገቡት። ግን፣ እስካሁን የሰሩትን ስንመለከት፣ በጣም ንዑስ ሆኖ ነው ያገኘንነው ። »

ይሁን እንጂ፣ የፕሬዚደንት ኬንያታ ደጋፊዎች የመንግሥቱን ስራ ለመገምገም አንድ ዓመት አጭር ነው በሚል ይከራከራሉ። ኬንያታ ሥልጣን እንደያዙ ወዲያው ያሟሉት አንድ ነገር እንዳለ በማስታወቅ፣ ነፍሰ ጡሮች ነፃ ቅድመ ወሊድ ምርመራ እና በሚወልዱበትም ጊዜ ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደረጉበትን ርምጃቸውን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል።

ፕሬዚደንቱ ሥልጣን የያዙበት አንደኛ ዓመት ሊታሰብ ጥቂት ቀናት እንደቀረው ለሀገሪቱ ባሰሙት ንግግር የምጣኔ ሀብቱን ለማነቃቃት እና ሙስናን ለመታገል ያደረጉትን ጥረታቸውን ቢያሞግሱም፣ በተጨባጭ የጠቀሱት አልነበረም። በኬንያ የሚገኘው የጀርመናውያኑ የህይንሪኽ በል ተቋም ባለደረባ ካትሪን ዛይድል እንዳመለከቱት፣ እርግጥ፣ በተለይ በፖሊስ መስሪያ ቤት ውስጥ በተስፋፋው ሙስና አኳያ ምርመራ ቢካሄድም እስካሁን በተጠያቂዎቹ ላይ ርምጃ አልተወሰደም።

« የሙስናውን ወቀሳ እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚስዮን በተወቃሾቹ ላይ የቀረበውን ወቀሳ መርምሮ፣ አንዳንዶቹን ጥፋተኛ ቢልም፣ እነዚህ ሰዎች አሁንም ከስራቸው አልተወገዱም። በፀጥታው ድርጅት ወይም በፖሊስ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ እንደያዙ ይገኛሉ። »

ኬንያውያን ግን በሙስና የተነሳ ብቻ አይደለም በፀጥታ ኃይላቱ ላይ እምነት ያሳጣው። ባለፈው መስከረም 21፣ 2006 ዓም የሶማልያ የዓማፂ ቡድን አሸባብ ሚሊሺያ በናይሮቢ የዌስትጌት የገበያ ማዕከል ላይ ጥቃት ጥለው ወደ 70 የሚጠጉ ሰዎች በገደሉበት ጊዜ፣ መንግሥት ጥቃቱን ለማስቆም እና የሕዝቡን ሕይወት ለማትረፍ አለመቻሉ ሕዝቡ በመንግሥቱ እና በፀጥታ ኃይላቱ ላይ የነበረውን እምነት እንደሸረሸረው ነው ዛይድል የገለጹት።

« ባጠቃላይ ኬንያውያን ከመንግሥታቸው በቂ እንክብካቤ እንዳልተደረገላቸው እና አስፈላጊው ዋስትና እንዳልተሰጣቸው ነው የሚሰማቸው። »

የዌስትጌቱ ጥቃት ምርመራ ውጤት እስካሁን በውል አለመታወቁ በብዙዎቹ ዘንድ ስጋት መፍጠሩን ዛይድል አመልክተዋል።

« ከዌስትጌት ጥቃት በኋላ የተካሄደውን ምርመራ በተመለከተ ከመንግሥት በኩል በይፋ በቂ መረጃ ባለመውጣቱ፣ ብዙ ኬንያውያን መንግሥታቸው በሚከተለው የፀጥታ አጠባበቅ ላይ ከፍተኛ ስጋት አድሮባቸዋል። »

ኬንያ በአሁኑ ጊዜ ከጎረቤት ሀገራት የሄዱ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ስደተኞችን ማስተናገድ የያዘችበት ሁኔታ በሀገሪቱ የፀጥታ ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ስጋትደቅኖዋል።

ኬንያ በሶማልያ መንግሥት አንፃር የሚንቀሳቀሰውን አሸባብ ሚሊሺያዎችን ለመዋጋት እአአ በ2011 ዓም ጦሯን ወደ ሶማልያ ከላከች ወዲህ አክራሪው ቡድን በኬንያ በርካታ ጥቃቶችን ጥሎዋል። ከጥቂት ቀናት በፊት በመዲናይቱ ናይሮቢ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ሦስት ቦምቦች በፈነዱበት ጥቃት ስድስት ሰዎች ነበሩ የተገደሉት። ከጥቃቱ በኋላ ፕሬዚደንት ኬንያታ ባሰሙት ንግግር ለሕዝባቸው ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል እንደሚያሠማሩ በድጋሚ ቃል ሲገቡ ተሰምቶዋል።

« የሕዝባችንን ደህንነት ማረጋገጥ እና ሉዓላዊነቱን ማስከበር ካሉብኝ መሰረታዊ ኃላፊነቶች መካከል ይቆጠራሉ። አንፈራም፣ በሉዓላዊነታችን ላይ የሚሰነዘር ማናቸውንም አደጋ በመላ ኃይላችን እንመታዋልን። »

Wahlen Kenia 2007 Auschreitungen Unruhen

ድህረ ምርጫ ሁከት

በአንድ ዓመቱ የሥልጣን ዘመናቸው ያን ያህል የሚያስመሠግናቸው ነገር አልሰሩም የሚባሉት የኬንያ ፕሬዚደንት በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነታቸውን ለማሳደግ እና ይህንንም ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኛ ፍርድ ቤት የመሠረተባቸውን ክስ ለማጣጣያ ብሔረተኝነትን እንደ መሣሪያ እየተጠቀሙበት መሆናቸውን ታዛቢዎች ይናገራሉ። እንደሚታወቀው፣ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት ኬንያታን እና ምክትላቸውን ዊልያም ሩቶ እአአ በ2007 ዓም በኬንያ ከተካሄደው ምርጫ በኋላ የተፈጠረውን የጎሣ ጭት አቀነባብረዋል በሚል ነው ክስ የመሠtr,ተባቸው። በዚያን ጊዜው ግጭት ከ1,200 የሚበልጥ ሰው ሲገደል ወደ 500,000 የሚጠጋም ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎዋል። ሁለቱ ተከሳሾች ክሱን ምዕራባውያን መንግሥታት ኬንያን ጥገኛ ለማድረግ የጠነሰሱት ነው በሚል ክሱን አጣጥለውታል።

ይሁን እንጂ፣ ይህ ዓይነቱ አነጋገር ብቻ ኬንያውያኑ ፕሬዚደንታቸውን እንዲደግፉ ማድረጉ አጠራጣሪ ነው። ከጥቂት ጊዜ በፊት በሀገሪቱ የወጣ አንድ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ መዘርዝር እንዳሳየው ከ50% የሚበልጠው የኬንያ ሕዝብ በፕሬዚደንቱ አመራር ደስተኛ አይደለም።

ፕሬዚደንቱ ሀገሪቱ በወቅቱ ለምትገኝበት ግዙፉ ፈታኝ ሁኔታ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በምጣኔ ሀብቱ፣ በፀጥታው እና በማህበራዊው ዘርፎች አኳያ አስፈላጊውን ርምጃ ማንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው ነው ብዙ ኬንያውያን እያሳሰቡ ያሉት።

በአሁኑ ጊዜ የብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ሰራተኞች የተደረገላቸውን የደሞዝ ጭማሪ ስላለተከፈላቸው የስራ ማቆም አድማ ላይ ይገኛሉ። እአአ በ2010 ዓመ የፀደቀው የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ክፍላተ ሀገርን ያጠናክራል ተብሎ ነበር የታሰበው፦ ግን፣ ክፍለ ሀገራቱ በበጀታቸው ላይ ፣ በተለይ፣ በጤና ጥበቃው ዘርፍ የተደረገው ቅነሳ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩትን ተግባራት እንዳያሟሉ እንቅፋት ሆኖዋል። በሰራተኛው ደሞዝ ላይ ጭማሪ ባልታየበት በአሁኑ ጊዜ የምግብ እና እህል ዋጋ ካለማቋረጥ እየተወደደ ሄዶዋል። መንግሥት ትምህርት ቤቶችን በኃይሉ ምንጭ መረብ ውስጥ ለማስገባት ዕቅድ ቢያወጣም፣ ካለ ኮሬንቲ ኬንያታ በቀሪው የሥልጣን ዘመናቸውም ቢሆን ተማሪዎችን ላፕቶፕ ባለቤታ ለማድረግ የወጠኑት ሀሳባቸው ተግባራዊ ሊያደርጉ አይችሉም።

 

ሂልከ ፊሸር/አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች