የኬንያ ፓርላማ በICC ስምምነት ላይ ተከራከረ | አፍሪቃ | DW | 04.09.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኬንያ ፓርላማ በICC ስምምነት ላይ ተከራከረ

የኬንያ ባለስልጣናት በዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት (ICC) ክሳቸው ሊታይ ጥቂት ሳምንታት ሲቀረው፤ የሀገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኬንያ የICC መቋቋሚያ ዉል ፈራሚነቷን ታነሳ ዘንድ ትናንት ሲከራከር ውሏል።

በመጪዎቹ ሳምንታት የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የክስ ሂደት ደን ሀግ ላይ በዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት (ICC) ይታያል። ባለስልጣኑ እኢአ በ2007 ዓ ም ከተካሄደው ምርጫ በኋላ ደም የተፋሰሰበት አመፅ እንዲካሄድ አነሳስተዋል በሚል 3 ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸዋል። በተጨማሪም ፕሬዝዳት ኡሑሩ ኬንያታ ላይ የቀረበዉ ክስ ቀነ ቀጠሮዉ ደርሷል። ህዳር 3 2006 ዓ,ም። የተከሰሱት አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ፣ በግድያ እና ህዝብን ከኖረበት ቀየ በማፈናቀል ነው። ምንም እንኳን ሀገሪቱን ከICC ዉል ፈራሚነት ለማዉጣት ትናንት ፓርላማው ሲከራከር ቢውልም፤ በፍርድ ቤቱ የተጀመረዉ የክስ ሂደት ላይ ለዉጥ አይኖርም። ይህን ሀሳብ በናይሮቢ የሲቪል እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ጋሺሂ ጋቼኬ ይጋራሉ፤

Kenya's newly elected President Uhuru Kenyatta attends the Easter Mass at the Saint Austin's Catholic church in the capital Nairobi, March 31, 2013. Kenya's Supreme Court upheld Uhuru Kenyatta's presidential election victory on Saturday and his defeated rival accepted the ruling, helping douse tensions after tribal violence blighted the election five years ago. REUTERS/Thomas Mukoya (KENYA - Tags: POLITICS ELECTIONS)

ፕሬዝዳት ኡሑሩ ኬንያታ

«ፊርማቸዉን ለማንሳት ማመልከቻ ቢያስገቡም ኬንያን ከICC ስምምነት ለማዉጣት ቢያንስ አንድ ዓመት ሊወስድ ይችላል። በዚያ ላይ የስምምነቱ ዉል እስኪያበቃ ድረስም ሌላ ጉዳይ ካልመጣ በቀር ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ጉዳይ አያስቆምም።»

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ጋቼኬ በኬንያ ምርጫ በተካሄደ ቁጥር ግጭት ሲነሳ እንደቆየ ያስታውሳሉ። የተባበሩት መንግስታት እና ICC ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጋ በመተባበር ጥፋተኞች ለፍርድ መቅረብ ጀመሩ እንጂ ይህ መንግስት በዚህ ረገድ ምንም አስተዋፅዎ አላደረገም ባይ ናቸው።

NAIROBI, Kenya - Photo shows Kenyan Deputy President William Ruto in Nairobi in March 2013. Ruto, facing charges of crimes against humanity, will visit Japan to attend an international conference on development in Africa, Japanese government and other sources said May 27. (Kyodo)

የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

«ይህ መንግስት በኃይል ነው ስልጣን የያዘው። የራሳቸውን ጎሳ አባላት ለድጋፍ እንዲነሳሱ ሰፊ ቅስቀሳ አድርገዋል። ጥምረቱ እንዴት እንደተመሠረተም የሚታወቅ ነው። እናም ለማህበራዊ ፍትህ ፍላጎት ያላቸው አይመስለኝም። ምክንያቱም ታሪካቸዉን እንኳ ብንመለከት የኡሑሩ ኬንያታም ይሁን የዊሊያም ሩቶን ታሪክ ስንመለከት በ1992 እና በ1997 የት ነበሩ? ካኖ አካባቢ ነበሩ። ነገር ግን ግድያ ሲፈፀም አንዴ እንኳን ለምን ብለዉ ጥያቄ አላቀረቡም። ስለዚህ ለኬኒያውያን ፍትህ በግንባር ቀደምትነት ቆማዋል ለማለት ያስቸግራል።»

በአንጻሩ ኬንያ ዉስጥ እንደ እሳቸዉ ሁሉ ለሲቪል እና ለሰብዓዊ መብቶች የሚሟገቱ አካላት በምርጫ ጊዜ ሀገሪቱ ዉስጥ የታየው አይነት በደል በሰዎች ላይ እንዳይከሰት ስላደረጉት ጥረት ሲገልጹ፤

« ባለፈው አርብ ደብዛቸው የጠፋበት ሰዎች በአለም አቀፍ ደረጃ በሚታሰቡበት ዕለት መግለጫ አዉጥተናል፤ በዚህም ለተከሰተዉ ታሪካዊ የፍትህ ጉድለትና ለተፈጸመዉ ግድያ ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርበናል። በተጨማሪም ለፍትህ ስንታገል እንደነበረው ዘመቻችንን እንቀጥላለን፣ ኬንያውያንን በማስተባበርም፣ ምክር ቤቱ የሚያካሂደዉ ክርክር ለሀገሪቱ ሳይሆን የግለሰቦችን ፍላጎት ለማሳካት ብቻ እንደሆነ እናስረዳለን።»

የኬንያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ የICCን ውል ማፍረስ ከሆነ ኬንያ የመጀመሪያዋ የዚህ ውል አፍራሽ ሀገር ትሆናለች። የኬንያ ፓርላማ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆይስ ላቦሶ ትናንት እንዳሳወቁት የምክር ቤት አባላቱ በጉዳዮ ላይ መክረው ውሳኔያቸውን ነገ እንዲያሳውቁ ቀጠሮ ተይዟል። እስካሁን ምክር ቤቱ የደረሰበት ዉሳኔ ይፋ ባይደረግም፤ ጉዳዩ ግን ከፍተኛ ክርክር እንደሚያስነሳ ተገምቷል።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic