የኬንያ ድጋሚ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እና ተፅዕኖው | አፍሪቃ | DW | 13.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኬንያ ድጋሚ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እና ተፅዕኖው

በኬንያ የፕሬዚደንታዊው ምርጫ ውጤት መሰረዝ ሀገሪቱን አስተማማኝ ያልሆነ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ስጋት ውስጥ እንደጣላት ተነገረ። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ብይን በተቀዛቀዘው የኬንያ ኤኮኖሚ የወደፊት እድገት ላይ ጥላ አጥሎበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:21
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:21 ደቂቃ

ኬንያ

በኬንያ የተካሄደው የአንድ ዓመቱ የምርጫ ዘመቻ እና ከሁለት ሳምንት በፊት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውድቅ ያደረገው የጎርጎሪዮሳዊው ነሀሴ ስምንት፣ 2017 ዓም ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በሀገሪቱ  ኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ ተነገረ። ለሀገሪቱ በጀትም ትልቅ ጫና እንደሚፈጥር በወደብ ከተማይቱ ሞምባሳ የሚገኘው የኬንያ ብሔራዊ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ሊቀ መንበር ጄምስ መሮይ አስረድተዋል።
« የምርጫው ውጤት መሰረዝ  በሀገሪቱ ፋይናንስ ላይ ግዙፍ ተፅዕኖ ይኖረዋል።  አዲስ ምርጫ ማዘጋጀት ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል፣ እና ፍርድ ቤቱ ብይኑን ከማሳለፉ በፊት ፣ በሰበቡ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ሁሉ መመልከት ነበረበት። ብይኑን የምርጫውን ውጤት በተመለከተ የተሰጠ ሀቀኛ ብይን ሳይሆን ፖለቲካዊ ብይን አድርጌ ነው የተመለከትኩት። »
በኤኮኖሚው ላይ ባረፈው አሉታዊ ተፅዕኖ አዲሱ ሁኔታ አብዝቶ የተጎዳው የናይሮቢው የአክስዮን ገበያ ሲሆን፣ እንደ መሮይ አስተያየት፣ ጥቅምት 17፣ 2017 ዓም ድጋሚው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እስኪሚደረግ እና በምርጫው ሰበብ ለተፈጠረው ልዩነት  መፍትሔ እስከ  ድረስ የዋጋው ግሽበት ከፍ እንዳለ እና ምንዛሪው ሽሊንግም እንደተዳከመ መቀጠሉ አይቀርም።
«  የአክስዮን ገበያውን ብንመለከት በየቀኑ 92 ቢልዮን ሽሊንግ እያጣን ነው፣ ይህ ሁኔታም እየከፋ መሄዱ አይቀርም። እና ፣ በኔ አስተያየት፣ ለዚሁ ሁኔታ ፣ ፊት ለፊት ከምናየው በስተጀርባ ሌላ መንስዔ ይኑረው አይኑረው ጠንቀቅ ብለን መመልከት ይኖርብናል። ለምሳሌ፣ ብዙ ቢልዮኔር ቻይናውያን ሀገራችንን ጎብኝተዋል፣ እነዚህ ቢልዮኔሮች የአክስዮን ገበያችንን ለመጣል እና በኋላም አክስዮኖቹን በዝቅተኛ ዋጋ ለመግዛት የሚፈልጉ ናቸው። »


ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ድጋሚ ይደረግ የተባለበት ውሳኔ እና በፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ በንግዳቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳረፈባቸው ለዶይቸ ቬለ የገለጹት የሞምባሳው ነጋዴ ፒተር ኩቲ መዘዙን በተወሰነ ደረጃ ለመወጣት ጫናውን በደንበኞቻቸው ላይ መጫን እንደተገደዱ አስረድተዋል።
« የዕቃዎች ዋጋ ጨምሯል። ቀደም ሲል አንድ ጂንስ ሱሪ 400 ሽሊንግ እንሸጥ ነበር፣ አሁን ግን በ700 እና 800 ሽሊንግ መካከል ነው የምንሸጠው።  18,000 ሽሊንግ ይሸጡ የነበሩ የተለበሱ  የልጆች ልብሶች አሁን ዋጋቸው 19,500 ሽሊንግ ደርሷል። »


በኬንያ ፕሬዚደንታዊው ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ እና የሀገሪቱ ኤኮኖሚም ባፋጣኝ እንዲያገግም ለማድረግ ይቻል ዘንድ፣ በመወዛገብ ላይ የሚገኙት ኬንያውያን ፖለቲከኞች የሀገሪቱን አስመራጭ ኮሚሽን በነፃ  እንዲያሰሩ የኬንያ ብሔራዊ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጠይቋል። በወቅቱ የተቃዋሚው ፓርቲዎች ህብረት፣ ናሳ አዲሱን የምርጫ ዕለት ባለመቀበሉ፣ ገዢው የጁብሊ ፓርቲም ምርጫውን እንዲቆጣጠር አስመራጩ ኮሚሽን ያዋቀረውን ቡድን ባለመቀበሉ የተፈጠረው የፖለቲካ ፍጥጫ  አሳሳቢ እንደሆነ ቀጥሏል።

አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች