የኬንያ የፀጥታ ጥበቃ ዘመቻ | አፍሪቃ | DW | 03.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የኬንያ የፀጥታ ጥበቃ ዘመቻ

ኬንያ በተጠርጣሪ አሸባሪዎች ላይ ዘመቻ ከፍታለች ። ፖሊስ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ በአሸባሪነት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቤት ለቤት አሰሳ እያደነ በማሰር ላይ ነው። እስከ ትናንት ድረስ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች መታሰራቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል አቡበከር ሻሪፍ የተባለው የእስልምና ሃይማኖት አዋቂ ሞምባሳ አቅራቢያ ከትናንት በስተያ መገደሉ በከተማይቱ ውጥረቱን አባብሶታል።አንዳንድ ሙስሊሞች ለዚህና በተመሳሳይ ሁኔታ ለተፈፀሙ መሰል ግድያዎች ፖሊስን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ፖሊስ በበኩሉ ገዳዮቹ እንደማንኛውም ተጠራጣሪ አሸባሪ ተይዘው ይታሰራሉ ሲል አስታውቋል። የኬንያ ፖሊስ ዘመቻ ያነጣጠረው በተለይ ከዋና ከተማይቱ ከናይሮቢ ወጣ ብሎ በሚገኘው ኢስሊ በተባለው ሶማሌዎች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ ነው። ኢስሊ ባለፈው ሰኞ በደረሱ ሶስት የቦምብ ፍንዳታዎች የስድስት ሰዎች ህይወት የጠፋበትና 31 ሰዎች የቆሰሉበት ስፍራ ነው። ከዚህ አካባቢ ከአንድ ሺህ በላይ ተጠርጣሪ አሸባሪዎችን መያዙን ያስታወቀው ፖሊስ ከትናንት በስተያ ብቻ 400 ተጠርጣሪዎች ማሰሩን ገልጿል። ፖሊስ ዘመቻውን አጠናክሮ በቀጠለበት በዚሁ እለት በወደብ ከተማዋ ሞምባሳ አቅራቢያ አቡበከር ሸሪፍ ወይም በተለመደው አጠራሩ ማካቡሪ የተባለ ምዕራባውያን በአክራሪነት የፈረጁት የሙስሊም ሃይማኖት አዋቂ በታጣቂዎች መገደሉ በሁለተኛይቱ ትልቅ ከተማ ሞምባሳ ውጥረቱን አባብሶታል። በአብያተ ክርስቲያን ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች የተደጋገሙባት የሞምባሳ ጎዳናዎች ትናንት በታጠቁ ፖሊሶች ሲጠበቁ ነበር። እነዚህና ሌሎችም የፖሊስ እርምጃዎች የኬንያን ፀጥታ አጠያያቂ ቢያደርጉም መንግሥት ግን የሚያሳስብ ነገር የለም ይላል። የፖሊስ ቃል አቀባይ ማሱልድ ሚዊኒ፤

«በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ፀጥታ ጥሩ ትክክለኛ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ከሞምባሳ ወጣ ባለ አካባቢ በደረሰው አደጋ ሰዎች አዝነዋል፤ አንዳንዶችም ተጨንቀዋል። ይህም ፀጥታውን ሊያላላ ክፍተት ሊፈጠር የሚችልበትን ሁኔታ ሊያስከትል ይችላል ብለው የሚያስቡም አሉ። ሆኖም ለህዝቡ በአጠቃላይ ልናሳውቅ የምንፈልገው ድርጊቱ እንደተፈፀመ ፖሊስ ወዲያውኑ በመንቀሳቀስ በወንጀሉ የሚጠረጠሩ ሰዎችን ለመያዝ ምርመራ ጀምሯል።»

ቃል አቀባዩ ይህን ቢሉም ከዚህ ቀደም ቤተሰቦቻቸው በተመሳሳይ ሁኔታ የተገደሉባቸው ሰዎችና ሌሎች ሙስሊሞች በግድያው የፖሊስ እጅ አለበት ባዮች ናቸው። እጎአ ነሐሴ 2004 በተመሳሳይ ሁኔታ የተገደሉት የሙስሊም ሃይማኖት አዋቂ የአቡድ ሮጎ ባለቤት ይህን ከሚሉት አንዷ ናቸው። በርሳቸው አስተያየት ከግድያው በስተጀርባ መንግሥት አለበት የሚሉት በባለቤታቸውና በሌሎች ላይ ለተፈፀሙ ተመሳሳይ ግድያዎች መንግሥት ምንም ዓይነት እርምጃ ባለመውሰዱ ነው። አቡበከር ማክሰኞ ከመገደሉ ጥቂት ጊዜያት በፊት ሞምባሳ ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር። በዚሁ መግለጫው ለምስጢራዊ ግድያዎች ተጠያቂው ፖሊስ መሆኑን ርሱም ሊገደል እንደሚችል ጠቁሞ ነበር።

«ለህይወቴ ስለምሰጋ አይደለም። ህይወቴ አደጋ ላይ ነው። ሆኖም ህይወቴ በፈጣሪ እጅ ነው። እናም ፈጣሪ ካልፈቀደ በስተቀር ምንም አልሆንም። ከዛ በፊትም ሆነ በኋላ ሊሆን አይችልም። የሚሆነው ፈጣሪ ሲል ብቻ ነው። ይህን ግድያ የሚፈፅሙት የኬንያ ፖሊሶች ናቸው። ይህ የታወቀ ነው። አሳዛኙ ነገር የፖሊስ ኮሚሽነሩ ሞምባሳ ነበሩ። እርሳቸውም ሞምባሳ ውስጥ ለምንገኝ ሙስሊሞች የጦር መሳሪያ ይዞ የተገኘ ማንኛውም ሰው ፍርድ ቤት ሳይወሰድ ይገደላል ሲሉ ፖሊስ እንደሚገድል በግልፅ አረጋግጠውልናል። ትዕዛዙ ፖሊስ እነዚህን ግድያዎች እየፈፀመ መሆኑን ያረጋግጥልናል።»

2004 አክራሪ የሚባሉት አቡድ ሮጎ ሌላው በተመሳሳይ የተፈረጁት ሼክ ኢብራሂም ኢስማይል ደግሞ በጥቅምት 2006 ዓም ከተገደሉ ወዲህ ወጣት ሙስሊሞችና ፖሊሶች እየተጋጩ ነው። በሞምባሳ በኬንያ የሚደርሱት ግድያዎች ህዝቡን ስጋት ውስጥ ከተውታል። ከጥቃቶቹ አብዛኛዎቹም በሶማሌዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ኬንያ በገቡ ስደተኞች ተላከዋል። መንግሥት በዚህ ሰበብ ስደተኞች በሙሉ በሁለት የስደተኞች መጠለያዎች እንዲገቡ አዟል። መንግሥት እንደሚለው ይህን የሚያደርገው ለኬንያውያንም ለሰደተኞቹም ደህንነት ሲል ነው። ቃል አቀባይ ማሱልድ ሚዊኒ

«አላቀዱት ቦታ ገብተው የተገኙ ሕገ ወጥ የውጭ ዜጎችንና ስደተኞችን ወደ አንድ አካባቢ ማሰባሰብን ጨምሮ የተለያዩ የፀጥታ ዘመቻዎችን እያካሄድን ነው። በዚህ ተግባርም የዜጎችን ብቻ ሳይሆን የሕገ ወጥ ስደተኞችን ደህንነትም እናረጋግጣለን። በመጨረሻም ኬንያ ውስጥ የሚገኝ የማንኛውንም ሰው ፀጥታ ማስጠበቅ የሀገራችንና የፀጥታ አስከባሪው መሥሪያ ቤት ፍላጎት ነው።»

ኬንያ ስደተኞች እጅግ ወደ ተጨናነቁት የዳዳብና የካኩማ መጠለያዎች እንዲገቡ ማዘዟን የመብት ተሟጋቾች ተቃውመዋል።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic