የኬንያ የፀረ ሽብር ትግል | አፍሪቃ | DW | 17.05.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኬንያ የፀረ ሽብር ትግል

የኬንያ ፖሊስ አንድ የጀርመን ዜጋ ሶማሊያ ዉስጥ ከሚንቀሳቀሰዉ ታጣቂ ቡድን አሸባብ ጋ ግንኙነት አለዉ ሲል ግለሰቡን ማደን ቀጥሏል። ኬንያ ከአዉሮጳዉያኑ 1998ዓ,ም ነሐሴ ወር አንስቶ ለሽብር ጥቃት ብትጋለጥም፤ ካለፈዉ ዓመት ወዲህ ግን

ተደጋጋሚ ጥቃቶች ደርሰዉባታል። ባለፈዉ ዓመት የኬንያ መንግስት አሸባብን ለመዋጋት ወታደሮች ወደሶማሊያ አዝምቷል።

«አሸባብ የሽብር ተግባሩን አቁሞ የሰላም ሂደቱ አካል የሚሆንበት ጊዜዉ አሁን ነዉ።» የኬንያ ወታደራዊ ኃይል ቃል አቀባይ ሜጀር ኢማኑዌል ችርችር በትዊተር መረጃ ለሚለዋወጧቸዉ ወገኖች ባለፈዉ ሚያዚያ ወር ያሰፈሩት መልዕክት ነዉ። የአሸባብ ምላሽ ብዙም አልቆየ፤ «አሸባብ የኬንያ ሙስሊሞች ያለባቸዉን ጭቆናና የፍትህ መጓደል ለማስወገድ መንግስትን እንዲጋፈጡ ለጂሃድ  በቆራጥነት እንዲነሱ ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል።» ሲል በተመሳሳይ ስልት አሰፈረ። ምንም እንኳን አሸባብ የተጠቀመበት የትዊተር አድራሻ በትክክል የቡድኑ መሆኑ ባይረጋገጥም፤ ሁኔታዉ ግን ኬንያና አሸባብ በኢንተርኔት ብቻ ሳይሆን በአካባቢዉ መሬት ላይም ጦርነት ዉስጥ መሆናቸዉን ያመለክታል። የኬንያ መንግስት ለረዥም ዓመታት ሶማሊያ ዉስጥ የሚደረግ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ሲሸሽ ቆይቷል።

አሸባብ ደግሞ በተለይ ከአዉሮጳዉያኑ 2006ዓ,ም ወዲህ ሶማሊያ ዉስጥ እየተጠናከረ ብቅ ብሏል። የሽብር ጥቃትና ረሃብ በሺዎች የሚገመቱ ሶማሊያዉያንን ወደኬንያ አሰድዷል። ዛሬም ኬንያ ዉስጥ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ የሶማሊያ ስደተኞች ይገኛሉ። አሸባብ በኬንያ ምድር የዉጭ ዜጎችን ማገቱ ግን የናይሮቢዉን መንግስት ከታጣቂዉ ቡድን ጋ ጦርነት ዉስጥ ከተተዉ። ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባና የፖለቲካ ተንታኝ ኢማኑዌል ኪሳንጋኒ፤

«ክርክሩ የኬንያ ወታደሮችን ወደዚያ በመላክ የፀጥታ ስጋት ሆኖ የሚታየዉን አሸባብን ከኬንያ ድንበር አካባቢ ጠራርገን ማባረር እንችላለን፤ ከተቻለም እናጠፋለን የሚል ነዉ። በእርግጥ አሁን ትላልቅ የሽብር ጥቃቶች ለመከላከል ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል ነገር ግን አገሪቱ ዉስጥ የሚፈፀሙ የሽብር እንቅስቃሴዎችን ሙሉ ለሙሉ ማስቆም አልቻሉም።»

Anschlag auf US-Botschaft in Nairobi

ኬንያ ከዚህ ቀደም ሁለት ከባድ የአሸባሪዎች ጥቃት ደርሰዉባታል። በአዉሮጳዉያኑ 1998ዓ,ም ናይሮቢ የአሜሪካን ኤምባሲ ላይ ያነጣጠረዉና ለሁለት መቶ ሰዎች ህልፈተ ህይወት ምክንያት የሆነዉ፤ በመቀጠልም የአስር ሰዎችን ህይወት በ2002ዓ,ም ሞምባሳ ዉስጥ በሚገኝ ሆቴል ያሳጣዉ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት። በወቅቱ ጥቃቱ ያነጣጠረዉ የምዕራብ አገራት ዜጎች ላይ ነዉ። ባለፉት ወራት ኬንያ ዉስጥ የሚደርሱ ጥቃቶች መንስኤ ደግሞ አገሪቱ ከአሸባብ ጋ የገጠመችዉ ፍጥጫ ዉጤት መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ።

ናይሮቢም ሆነ ሞምባሳ ህዝብ በሚያዘወትራቸዉ ስፍራዎች ጓዳ ሠራሽ ፈንጂዎች ይጣላሉ። በቅርቡ ከደረሱት ጥቃቶች የመጨረሻዉ የሁለት ሰዎችን ህይወት የቀጠፈዉና 15 የተጎዱበት ባለፈዉ ሚያዝያ ወር ማለቂያ ናይሮቢ በአንድ ቤተክርስቲያን የደረሰዉ ፍንዳታ ነዉ። ከዚህ የሽብር ጥቃት ጋ በተገናኘም የተጠረጠረ አንድ ጀርመናዊ እንደሚፈለግ ፖሊስ ይፋ አድርጓል። የኬንያ ፖሊስ በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ የሚያድነዉ ጀርመናዊ አህመድ ኻሊድ ሙለር እንደሚባልም ገልጿል። የኬንያ ፖሊስ ቃል አቀባይ ቻርለስ ኦዊኖ፤

«ሶማሊያ ዉስጥ በሚገኘዉ አሸባብ ጋ ግንኙነት እንዳለዉ ባገኘነዉ መረጃ ምክንያት  ነዉ መጥቶ እሱ ላይ የቀረቡ ክሶችን በሚመለከት ጉዳዩን ግልፅ እንዲያደርግ የጠራነዉ። የተወሰኑ አጋጣሚዎችን አንጠቅስም፤ የምንለዉ ከእነሱ ጋ ተባብሯል ነዉ ከእነሱ ጋ ይሰራል ነዉ፤ እኛ ማወቅ የምንፈልገዉ ከእነሱ ጋ ምን ይሰራ እንደነበር ነዉ።»

ግለሰቡ ከሶስት ዓመታት በፊት ፓኪስታን ዉስጥ ታስሮ እንደነበር እና አሁን በህገወጥ መንገድ ወደኬንያ ሳይገባ እንዳልቀረ ፖሊስ አመልክቷል። ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች የተለያየ አገር ዜጎች ሶማሊያ ዉስጥ ከአሸባብ ጎን ሳይሰለፉ እንዳልቀሩ ያመለክታሉ። ኬንያ ዉስጥ በሚደርሱ ጥቃቶች መሳተፍ አለመሳተፋቸዉ ግን ግልፅ አይደለም

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic