የኬንያ እና የዩጋንዳ የስኳር ንግድ ስምምነት | አፍሪቃ | DW | 14.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኬንያ እና የዩጋንዳ የስኳር ንግድ ስምምነት

ኬንያ ከዩጋንዳ ስኳር ለመግዛት የገባችው ስምምነት የሰላ ትችት እየተሰነዘረበት ነው። ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በሶስት ቀናት የዩጋንዳ ጉብኝታቸው የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:14

የኬንያ እና የዩጋንዳ የስኳር ንግድ ስምምነት


የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በሶስት ቀናት የዩጋንዳ ጉብኝታቸው ከዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ከተፈራረሟቸው ስምምነቶች መካከል የስኳር ግዢ ነው። በስምምነቱ በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. ከዩጋንዳ ወደ ኬንያ ይገባ በነበረው የስኳር ግብይት ላይ የጣለችውን እግድ አንስታለች። ስምምነቱ ግን ነቀፋ አላጣውም። የኬንያ ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ የአገር ውስጥ የስኳር አምራቾችን ያዳክማል በማለት ተችተዋል።

«በስኳር ላይ የተፈረመው ስምምነት የከፋ ነው።» በማለት ለኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ የተናገሩት ኦዲንጋ «የኬንያ ትልቁ የስኳር አምራች ሙሚያስ በሁለት እግሩ ለመቆም በሚንገዳገድበት ወቅት የተፈጸመ ነው። በመላ አገሪቱ የሚገኙ የሸንኮራ አገዳ አምራቾችም ክፍያ አጥተው በመቸገር ላይ ናቸው።» ሲሉ የኡሩ ኬንያታ መንግስት የፈጸመውን ስምምነት ወቅሰዋል።
የኬንያ መንግስት የሙሚያስ ስኳር ፋብሪካን ለማጠናከር ቀደም ብሎ አንድ ቢሊዮን የኬንያ ሺልንግ (8.9 ሚሊዮን ዩሮ) ቢመድብም ኬንያውያን አሁን የተፈረመው ስምምነት ከዩጋንዳ በሚገባ ስኳር ገበያው ይዋጣል ሲሉ ይነቅፋሉ።በኬንያ ፓርላማ አባል የሆኑት የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ፋጢማ ኢብራሂም አሊ ስምምነቱን «አሳዛኝ» ብለውታል።

DW-Interview Raila Odinga

የኬንያ ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ

«ፕሬዝዳንቱ ስኳር ለማስገባት ከዩጋንዳ ጋር የደረሱበት ስምምነት አሳዛኛ ነው። ምክንያቱም ኬንያ ለራሷ የሚያስፈልጋትን ስኳር የማምረት አቅም አላት። እንዲያውም ወደ ዩጋንዳ ሊላክ የሚችል ትርፍ ሁሉ ማምረት ትችላለች።»

በምዕራባዊ ኬንያ ለስኳር የሚሆን የሸንኮራ አገዳ በማምረት የሚተዳደሩት ማርጋሬት ኬሩቦም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከዩጋንዳ አቻቸው ዩዌሪ ሚሴቬኒ ጋር በተፈራረሙት ስምምነት ቅያሜ አድሮባቸዋል። «እዚህ ኬንያ ማምረት ስንችል ለምንድነው ስኳር ከዩጋንዳ የምናስመጣው? ይህ ፍትሃዊ አይደለም።» በማለት ስምምነቱን ይቃወማሉ። የኤኮኖሚ ተንታኝ ጃኔት ኦካች ስምምነቱ ለኬንያ ኤኮኖሚ ጉዳት ያመጣል ባይ ናቸው።

«ይህ ስምምነት ገበሬዎችን በጣም ይጎዳል። ርካሽ ስኳር ወደ ሃገር ውስጥ ስናስገባ የራሳችን ስኳር ለገበያው ውድ ይሆናል። ይኼኔ የስኳር ማምረቻዎቻችን ይዳከማሉ። ማምረቻዎቻችን ሲዳከሙ ደግሙ መጀመሪያ ተጎጂ የሚሆኑት ገበሬዎቹ ናቸው። በዚህ ስምምነት ከቀጠልን በመጪዎቹ አመታት ይህን እንመለከታለን። ስምምነቱ አሁኑ መቋረጥ ይኖርበታል።»
የ38 አመቱ መምህር ጆናታን ሙቴንጊ ግን አሁን በኬንያና ዩጋንዳ መካከል የተፈረመው ስምምነት የሁለቱን አገሮች የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ይጠቅማል የሚል አዎንታዊ አስተያየት አላቸው።

Besuch von Uhuru Kenyatta in Uganda

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በዩጋንዳ ፓርላማ

«ይህ በጣም ጥሩ ስምምነት ነው። ምክንያቱም ዩጋንዳውያን ወንድሞቻችን ናቸው። የንግድ ልውውጣችን ሚዛኑን የጠበቀ ነው። በሰሜናዊ ኬንያ ሰፊ መሬት አለን። በዚያ የቀንድ ከብት ዋጋ በጣም ርካሽ ነው። ወንድሞቻችን ስጋ ከፈለጉ ለእነሱ ልንሸጥላቸው ይገባል። በመካከላችን ክፍት የነጻ ገበያ ሊኖር ይገባል።»

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ከዩጋንዳ መንግስት ጋር የተፈራረሙትን የስጋና የወተት ምርቶች ግብይት ስምምነቶችንም ነቅፈዋል። በእሳቸው አባባል ኬንያ እንኳን ለውጭ ገበያ ቀርቶ ለአገር ውስጥ ፍላጎት የሚበቃ የስጋና የወተት ምርቶችን ማቅረብ አልቻለችም። ራይላ ኦዲንጋ እና ሌላዋ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ፋጢማ ኢብራሂም አሊ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በሶስት ቀናት ጉብኝታቸው ከዩጋንዳ መንግስት ጋር የተፈራረሙዋቸውን ስምምነቶች ሁሉ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic