የኬንያ ረቂቅ ሕገ-መንግሥትና ዉዝግቡ | የጋዜጦች አምድ | DW | 18.08.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የኬንያ ረቂቅ ሕገ-መንግሥትና ዉዝግቡ

ከመንግስት፣ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ከሲቢል ማሕበረሰብ ተቋማት የተወከሉት ስድስት መቶ ሃያ-ዘጠኝ ያርቃቂ ኮሚሽኑ አባላት ሥብጥራቸዉ፣ ክርክራቸዉ፣ ግራ-ቀኙን ለማማከል ያደረጉት ጥረት ሁሉ ምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ሐገር ለብዙዎቹ ብጤዎችዋ የዲሞክራሲ፣የፍትሕ የበላይነት ተምሳሌት ሆነች አሰኝቶ ነበር።

የኬንያ ምክር ቤት በቅርቡ የተቀበለዉ ረቂቅ ሕገ-መንግሥት የሐገሪቱን መንግሥት፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችንና የሲቢል ማሕበረብ መሪዎችን እያወዛገበ ነዉ።ኬንያ ከነፃነት ጀምሮ ሥትመራበት የነበረዉን ሕገ-መንግስት እንዲተካ የተዘጋጀዉ ረቂቅ የሚፀናዉ በመጪዉ ሕዳር በሕዝበ-ዉሳኔ ከፀደቀ ብቻ ነዉ።በረቂቁ ይዘት የሚወዛገቡት ተቀናቃኝ ወገኖች በሕዝበ-ዉሳኔዉ ሒደትና ድምፁን በሚሰጠዉ ሕዝብ ቁጥርም አልተግባቡም።

የዛሬ አምስት አመት የተሰየመዉ የኬንያ ሕገ-መንግሥት አሻሻይ ኮሚሽን ባደረገዉ ጥናት መሠረት ኬንያ ነፃ ከወጣትችበት ከ1955 ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ ከፕሬዝዳንት ጆሞ ኬንያታና ከዳንኤል ቶሪቺ አራፕ ሞይ በስተቀር ሌላ መሪ የማያዉቀዉ ሕዝብ በየመሪዎቹ ከመበዝበዝ-መረገጥ በስተቀር ያተረፈዉ ነገር አልነበረም።

በጥናቱ መሠረት አብዛኛዉ ሕዝብ ለየመሪዎቹ ፈላጭ ቆራጭነት የሚመቸዉ ሕገ-መንግሥት እንዲለወጥ ይሻል።ተለዋጩ ሕገ-መንግስት ሥልጣን በአንድ ሰዉ እጅ መማከሉን አስወግዶ ለብዙ እንዲከፋፈል አብዛኛዉ ሕዝብ የሚፈልግ መሆኑ አጥኚዎቹ አረጋግጠዋል።

ከሁለት አመት በፊት የተመሠረተዉ ሕገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን የሚያረቀዉ ሕገ-መንግሥት ዋና መሠረት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያዉ ኮሚሽን የደረሰበት ጥናት ዉጤት ነበር።ከመንግስት፣ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ከሲቢል ማሕበረሰብ ተቋማት የተወከሉት ስድስት መቶ ሃያ-ዘጠኝ ያርቃቂ ኮሚሽኑ አባላት ሥብጥራቸዉ፣ ክርክራቸዉ፣ ግራ-ቀኙን ለማማከል ያደረጉት ጥረት ሁሉ ምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ሐገር ለብዙዎቹ ብጤዎችዋ የዲሞክራሲ፣የፍትሕ የበላይነት ተምሳሌት ሆነች አሰኝቶ ነበር።

ኮሚሽኑ ያቀረበዉ ረቂቅ እስካሁን ድረስ በኬንያ የማይታወቅ የጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣን ከፍቷል።በቀድሞዉ ሕገ-መንግስት ፕሬዝዳንቱ ይቆጣጠሩት ከነበረዉ ያስፈፃሚነት ሥልጣን ገሚሱን ለጠቅላይ ሚንስትሩና ለምክር ቤቱ ያደላደለ ነዉ።ለኮሚሽኑ በወጣዉ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ኮሚሽኑ የመጨረሻ ረቂቁን ማቅረብ ያለበት ለሐገሪቱ ምክር ቤት ነዉ።ምክር ቤቱ ረቂቁን እንዳለ የመቀበል-አለያም እንዳለ የመጣል እንጂ ከረቂቁ አንቀሶች አንዱን ጥሎ ሌላዉን የማንጠልጠል መብት የለዉም።

የዛሬ አመት የመጨረሻዉ ረቂቅ ለምክር ቤቱ ሲቀርብ ግን የነበረዉ ሁሉ እንዳልነበር ሆነ።ረቂቁ የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን መሸንሸኑ ያስከፋቸዉ፣ ፕሬዝዳንት ምዋዪ ኪባኪና ባለሥልጣኖቻቸዉ ፓርቲያቸዉ የሚቆጣጠረዉ ምክር ቤት የሕገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽኑን ረቂቅ አንቀፅ ባንቀፅ የመርመመር ያሻዉን የመሻር-የማሻሻል ሥልጣን እንዲኖረዉ አደረጉ።ምክር ቤቱ ረቂቁን ሰርዞ ደልዞ-ለጠቅላይ ሚንስትሩና ለምክር ቤቱ የተደነገገዉን ሥልጣን በሙሉ ለኪባኪ ደረበላቸዉ።

ባለፈዉ ሐምሌ ያዉ ምክር ቤት በሚፈልገዉ መንገድ ዳግም የፃፋዉን ረቂቅ በአባላጫ ድምፅ ሲያፀድቅ የተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፣ የሲቢል ማሕበረብ አባላትን፣ የፍትሕና የመብት ተቆርቋሪዎችን ቁጣ ቀስቅሷል።ቁጣዉ ለተቃዉሞ ሠልፍ ያሳደመዉ የናይሮቢ፤ የሞንባሳና የኪሱሙ ሕዝብ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ተጋጭቶ ሕይወት ጠፍቷል።የተደበደበ፣ የታሰረም ነበር።

የመንግስትን አሠራር የሚቃወሙ ወገኖች በፍርድ ቤት ለመሟገት ፋይል ከፍተዉ ነበር።የሐገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ-ግን ክሱን አቀዛቅዘዉታል።ተቃዉሞዉ ቢያልም የኪባኪ መንግሥት ሕገ-መንግስቱን በሕዝበ-ዉሳኔ ለማፀደቀ ሰሞኑን ዘመቻ ብጤ ጀምሯል።ፕሬዝዳንት ኪባኪ ሕዝቡ ይሁንታዉን እንዲፀጥ ዘመቻዉን እንደሚመሩ አስታዉቀዋል።ተቃዋሚዎች በፋንታቸዉ ሕዝቡ ረቂቁን እንዳይደግፍ እየቀሰቀሱ ነዉ።ዉጤቱ ያዉ ሕዳር ነዉ የሚለዉ።