የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ባለሥልጣን ተገደሉ | አፍሪቃ | DW | 01.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ባለሥልጣን ተገደሉ

በመጪው ነሐሴ 2 ቀን መሪዎቿን የምትመርጠው ኬንያ ውጥረት ነግሶባታል። የኬንያ የኤሌክትሮኒክ ምርጫ ሥርዓትን በበላይነት ይቆጣጠሩ የነበሩት ክሪስ ምሳንዶ መገደል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የመብት ተሟጋቾችን አስቆጥቷል። ራይላ ኦዲንጋ በሥልጣን ላይ የሚገኙት ኡሑሩ ኬንያታ ምርጫውን ለማጭበርበር ቆርጠው ተነስተዋል ሲሉ እየወነጀሉ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:15

የኬንያ ምርጫ ውጥረት ነግሶበታል

በመቶዎች የሚቆጠሩ የኬንያ የመብት ተሟጋቾች ዛሬ ለተቃውሞ ወደ ናይሮቢ አደባባይ አቅንተዋል። የመብት ተሟጋቾቹን ያስቆጣቸው ወደ አደባባይም የመራቸው የክሪስ ምሳንዶ ድንገተኛ ሞት ነው። የኬንያን የኤሌክትሮኒክ የምርጫ ስርዓት የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለባቸው ክሪስ ምሳንዶ አስከሬን በሳምንቱ መገባደጃ ከናይሮቢ ከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኝ ቦታ ወድቆ ተገኝቷል። በምሳንዶ ገላ ላይ የግርፋት ምልክት የታየ ሲሆን በላያቸው አንዳች ልብስ አልነበረም። በኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ደጃፍ በተካሔደው የተቃውሞ ሰልፍ የታደሙት የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዳይሬክተር ጆርጅ ኬጎሮ ግድያው እጅግ ካሳሰባቸው አንዱ ናቸው። በምርጫ ዋዜማ እንዲህ አይነት ግድያዎች የተለመዱ ናቸው የሚሉት ኬጎሮ ተመሳሳይነታቸው ደግሞ አስፈሪ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል። 

ብሔራዊ ከፍተኛ አንድነት (the National Super Alliance) የተሰኘው የተቃዋሚዎች ጥምረት መሪዎች አንዱ የሆኑት ሙሳሊ ሙዳቫዲ ግድያው የኬንያን ዴሞክራሲ "ለማዛባት" የተወጠነ ሲሉ ወቅሰዋል። ክሪስ ምሳንዶ የመራጮችን ማንነት ማረጋገጥ፤የምርጫ ውጤት ክምችት እና አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት እንደነበረባቸው ያስታወሱት የጥምረቱ መሪ ገዳዮቻቸው የምርጫውን ውጤት በፈለጉት መንገድ ለመምራት አስፈሪ መልዕክት ልከዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

"ባለፈው ሳምንት ክሪስ የኬንያ የተቀናጀ ኤሌክትሪኒክ የምርጫ አስተዳደር ሥርዓት በአግባቡ እንደሚሰራ በቴሌቭዥን ማረጋገጫ ሰጥተው ነበር። ገዳዮቻቸው ድርጊታቸውን አደጋ ለማስመሰል ምንም ጥረት አላደረጉም። ምክንያቱም የሚፈልጉትን የምርጫ ውጤት ለማግኘት ምንም የሚያቆማቸው ነገር እንደሌለ መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልገዋል።"

ክሪስ ምሳንዶ ሞታቸው ከተሰማ በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታኒያ አምባሳደሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ ግድያው አብዝቶ እንዳሳሰባቸው ገልጠዋል። ለምርመራውም እጃቸውን በእርዳታ ዘርግተዋል። ሰውየው የኬንያ የምርጫ ቀን እየተቃረበ ሲመጣ በተደጋጋሚ ወደ ቴሌቭዥን ብቅ እያሉ በበላይነት የሚቆጣጠሩት እና በ2013ቱ ምርጫ እክል ገጥሞት የነበረው የኤሌክትሮኒክ የምርጫ ሥርዓት በአግባቡ እንደሚሰራ ለኬንያውያን ማረጋገጫ ይሰጡ ነበር። አስከሬናቸው ወድቆ በተገኘበት ዕለተ-ሰኞም ሙከራ የማድረግ እቅድ ነበራቸው። 

ምርጫ በኬንያ ሁሌም ውዝግብ አያጣውም። በየምርጫ ጣቢያዎች ማጭበርበር ተፈጽሟል፤ድምፅ ሰጪዎች ተሸማቀዋል የሚሉ ክሶች ይሰማሉ። ሲጣሩ አንዳንዶቹ እውነት ይሆናሉ፤የሐሰት ክሶችም አይታጡም። በመጪው ማክሰኞ የሚካሔደው ምርጫም ከዚህ የራቀ አልሆነም። በድኅረ ምርጫ ኹከት ከ1,100 በላይ ሰዎች ከተገደሉ ከአስር አመታት በኋላም የምርጫ ሥርዓት መጓደል ሥጋት በኬንያ ሰማይ እያንዣበበ ነው። የኬንያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ጆርጅ ሞራራ ይኸንን ጠንቅቀው ያውቁታል። ኃላፊው  "የሞተ ከመቃብር ወጥቶ ለምርጫ ድምፅ ይሰጣል፤ከዚያም ወደ መቃብር ይመለሳል" የሚል የኬንያውያንን ተሳልቆ ይጠቅሳሉ። 

የኬንያ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ዋፉላ ቼቡካቲ የሥራ ባልደረባቸው በሰው እጅ ተሰቃይተው ለመገደላቸው ጥርጣሬ አልገባቸውም። የአስከሬን ምርመራ እንደሚደረግ አውቃለሁ። አሁን እኛን እንደኮሚሽን የምናስበው ብቸኛ ነገር ማን እና ለምን ገደለው የሚለው ጥያቄ ነው። ይኸ ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ ነው። ለምርጫ የቀሩን ጥቂት ቀናት ናቸው። መንግሥት ለሁሉም ኬንያውያን የጸጥታ ጥበቃ ማቅረብ እንዳለበት ሁላችንም እናውቃለን። በተለይ በዚህ ጊዜ ለኬንያውያን ነፃ እና ፍትኃዊ ምርጫ እንድናቀርብ ለሁሉም የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ሰራተኞች መንግሥት የጸጥታ ጥበቃ እንዲያቀርብ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።"

በኬንያውያን የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ዘንድ በቢቢሲ እና ሲኤንኤን ስም የተዘጋጁ ሐሰተኛ የምርጫ ቅድመ-ትንበያዎችም ባለፈው ሳምንት ሲዘዋወሩ ከርመዋል። ፖርትላንድ የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም በሰራው የዳሰሳ ጥናት ከ10 ኬንያውያን ዘጠኙ መጪውን ምርጫ የተመለከቱ ሐሰተኛ ዜናዎችን ተመልክተዋል። 

ብሔራዊ ከፍተኛ አንድነትን ወክለው ከኡሑሩ ኬንያታ የሚገጥሙት ራይላ ኦዲንጋ ለፕሬዝዳንትነቱ ስልጣን ለምርጫ ሲቀርቡ አራተኛቸው መሆኑ ነው። የ72 አመቱ ፖለቲከኛ በተለይ በጎርጎሮሳዊው 2007 እና 2013 ዓ.ም. በተካሔዱት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች ውጤት ተነጥቂያለሁ የሚል ስሞታ አላቸው። የኬንያ የመጀመሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ልጅ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ ዘንድሮም ኡሑሩ ኬንያታ ምርጫውን ሊያጭበረብሩ ቆርጠው ተነስተዋል የሚል ክስ ያሰማሉ። ተቀናቃኛቸው ባይቀበሉትም። 


እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ 

Audios and videos on the topic