የኬንያ ምርጫ አስተምህሮ | አፍሪቃ | DW | 18.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኬንያ ምርጫ አስተምህሮ

ኬንያ ምርጫ ካካሄደች ስድስት ሳምንታት ተቆጠሩ። አዲሱ ፕሬዝደንቷ ቃለመሃላ ከፈፀሙ ደግሞ አንድ ሳምንት ሆናቸዉ። በምርጫዉ ሂደት የድምፅ ቆጠራዉ የገጠመዉ እክል እንዳለፈዉ ጊዜ በሀገሪቱ የቀሰቀሰዉ የከፋ አመፅ ባይኖርም ዉዝግቡ ገና አልሰከነም።

ማክሰኞ ዕለት የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተመረጡት ፕሬዝደንትን አስመልክቶ ላሳለፈዉ ብያኔ መነሻ የሆነዉን ባለ አንድ መቶ ገፅ ዘገባ ይፋ አድርጓል። የኬንያ ምርጫ ምን አመላክቷል? ወደፊትስ ሊወሰድ የሚገባዉ ጥንቃቄ በሚል ምሁራን እየተወያዩ ነዉ። ኬንያ ከምርጫ ማግስት ሁከት እንዳይቀሰቀስ ያደረገችዉ ጥረት በትላልቅ ባለስልጣናት ዘንድ ቀዳሚዉን ስፍራ መያዙ ነዉ የታየዉ። በሳምንቱ መጀመሪያ የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ጊ ሙን ኬንያ የምርጫ ዉዝግቡን የፈታችበት ሰላማዊ መንገድ ለሌሎችም አርአያ እንደሚሆን መናገራቸዉን የኬንያዉ ዘ ዴይሊ ኔሽን ዘግቦታል። በካናዳ ኦታዋ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ስቴፈን ብራዉን አገላለፁ አልጣማቸዉም። እሳቸዉ የኬንያን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ላለፉት አስር ዓመታት በቅርብ ሲከታተሉ ቆይተዋል።

Porträt - Prof. Stephen Brown

ፕሮፌሰር ስቴፈን ብራዉን

እንደታዘቡትም ከዚህ ቀደም የደረሰዉ ዓይነት ደም መፋሰስና ዉዝግብ እንዳይቀሰቀስ መገናኛ ብዙሃኑም ሆኑ ገለልተኞቹ ሲቪክ ድርጅቶች በምርጫዉ ዝግጅት ላይ ትችት ከመሰንዘር ተቆጥበዋል።

«በእርግጥ በምርጫ ዝግጅቱ ላይ ትልቅ ትኩረት ተደርጎ ነበር። ሆኖም የምርጫ ኮሚሽኑን በመከታተሉ ረገድ በተለይም በቴክኒካዊ ዝግጅቱ ረገድ ምን ያህል ለምርጫዉ ተዘጋጅቶ እንደነበር ለማሳየት በበቂ ሁኔታ የተደረገ ክትትል አልነበረም።»

በእርግጥም እዚህ ጋ ችግሩ ጎልቶ ይታያል። ድምፅ በሚሰጥበት ቀን የመራጮችን ማንነት የሚለየዉ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ከአገልግሎት ዉጭ ሆነ። ቆየት አለና ደግሞ የየጣቢያዉን የተቆጠሩ ድምፆች እየቀመረ የሚያስተላልፈዉ መሣሪያ ተሰናከለ። ሁለቱም ስልቶች ይበልጥ የምርጫዉን ግልፅነት በማረጋገጥ ከመጭበርበር ይታደጋሉ ተብለዉ ነበር። የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዑሁሩ ኬንያታን ፕሬዝደንትነት ቢያፀድቅም ስለዉሳኔዉ በዘረዘረበት ዘገባዉ ለተከሰቱት ቴክኒካዊ ችግሮች ቴክኒዎሎጂዉን በመረጠና በተጠቀመዉ አካል ላይ ከብቃት አልፎም ከወንጀል ጋ በተገናኘ ምርመራ እንዲካሄድ ጠቁሟል። በርካታ ታዛቢዎች የኬንያ ተቋማት ከአሠራት ግልፅነት ይልቅ ላለፉት አራት ዓመታት አቅማቸዉን ለማጠናከር መጨነቃቸዉን ይስማሙበታል። ያ ግን የጠቀማቸዉ አይመስልም፤

«በርካታ የተቃዋሚ ደጋፊዎች ቁልፍ በተባሉ ተቋማት ላይ እምነት አጥተዋል። ይህም ላሸነፈዉ መንግስት ለወደፊት አንድ ፈተና ነዉ የሚሆን።»

ይላሉ በብሪታንያ ዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የኬንያ ጉዳይ ተመራማሪ ጋብሪየል ሊንች። ከኬንያ ሲቪል ማኅበራት ጋ በቅርበት የሚሠሩት ሊንች አብዛኞቹ ኬንያዉያን የሚታየዉን ሰላም የይስሙላ ነእንደሚሉት ነዉ የሚገልፁት። ከአመፅ መታቀብ ማለት እዉነተኛ እርቀ ሰላም ወርዷል ማለት አለመሆኑንም ያመለክታሉ።

Porträt - Dr. Gabrielle Lynch

ጋብሪየል ሊንች

በዚያ ላይ የኬንያታ ተፎካካሪ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች በሚኖሩበት አካባቢ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ አስከባሪ ኃይል መሰማራቱን ልብ ይሏል። ይህ ደግሞ ፍርድ ቤት ያሳለፈዉን ዉሳኔ በመቃወም ሰልፍ እንዳይካሄድ አግዷል። ሌላዉ የኬንያ መንግስት ተግዳሮት የሚሆነዉ ከማዕከላዊነት በተለየዉ የየወረዳዉ አስተዳደር ላይ ነፍስ የመዝራቱ ርምጃ ነዉ። በጎርጎሮሳዊዉ 2010ዓ,ም የፀደቀዉ አዲሱ ህገመንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ 47 ወረዳዎች የየራሳቸዉን ጉዳይ ራሳቸዉ እንዲወስኑ ይደነግጋል። ለዚህም ኬንያዉን በመጋቢት ወር የአካባቢ ምክር ቤቶችን፤ አገረ ገዢዎችና ሴናተሮችን መርጠዋል። ሊንች ይህን አዲሱን የመንግስት መዋቅር በስጋት ነዉ የሚያዩት፤

«የክፍለ ሀገር አስተዳደር የሚል አዲስ ስያሜ የተሰጠዉ በመንግስት የአዉራጃ አስተዳደር ዉስጥ የሚገኝ መዋቅር አለ። ይህ ደግሞ በሁለቱ የአስተዳደር እርከኖች መካከል በሚኖረዉ ፉክክር ግጭት ይኖራል። ኬንያዉያን የመንግስት ማዕከላዊ መዋቅር መፍረስ ልማት፤ አዳዲስ የስራ እድሎችና የሃብት ድልድል ያስከትላል የሚል ከፍተኛ ተስፋ አሳድረዋል። ይህ ግን በጣም ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነዉ የሚሆነዉ።»

በኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጠበቃነት ለሚያገለግሉትና በአዲሱ ህገመንግስት ቀረፃ ለተሳተፉት ለኢኩሩ አዉኮት ደግሞ ከማዕከላዊ አሠራር የተላቀቀዉ የኬንያ መንግስት መዋቅርና እጅግ ሰፊዉ ምክር ቤት የሚፈተሽበት ወቅት ነዉ።

«በቅድሚያ ወጪዉ መሰላት ይኖርበታል። ያኔ ምናልባት ኬንያዉያን ይባንኑና ለመሆኑ ይህን የሚያህል ምክር ቤት ያስፈልገናል ወይ ብለዉ ይጠይቁ ይሆናል። ራሳችንን ማሞኘት የለብንም። ወጪዉ ከኤኮኖሚ እድገታችን ጋ መገናኘት ይኖርበታል ብዬም አላምንም።»

አያይዘዉ ስለኬንያ ምርጫ የገለፁት አዉኮት አንድ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም ሲንቀሳቀስ ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ ጣልቃ ከመግባት ቢቆጠብ መልካም ነዉ ይላሉ። ከምንም በላይ ምዕራባዉያን ሀገሮች ኬንያዉያን ዑሁሩ ኬንያታንና ምክትላቸዉን እንዳይመርጡ እስከመምከር መድረሳቸዉንና ያ ከሆነም ሊያስከትል ይችላል ባሉት መዘዝ ማስፈራራታቸዉን ጠቅሰዋል። በእርግጥ በምርጫ ያሸነፉት ሁለቱ የኬንያ መሪዎች የዛሬ አምስት ዓመት በምርጫ ማግስት ሀገሪቱ ዉስጥ ከተከሰተዉ አመፅና ጉዳት ጋ በተገናኘ ዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ችሎት እንደሚቀርቡ ይታወቃል። ካናዳዊዉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ስቴፈን ብራዉንም እንዲሁ በዚህ በኬንያዉ ምርጫ ምዕራባዉያን ሀገሮች ከስረዋል ባይናቸዉ፤

«ለጋሾች ከኬንያን ጋ መሥራታቸዉን ለመተዉ የተዘጋጁ አይመስልም። ይህም ሌላዉ የለጋሾች ባዶ ማስፈራሪያ ብቻ እንጂ የማይፈፅሙት መሆኑን አሳይቷል። ይህ ደግሞ ይበልጥ ተዓማኒነታቸዉን እየቀነሰዉ ሄዷል። ያም በምንም ዓይነት የፖለቲካ ድርድር ጠቃሚም ቢሆን ለምሳሌ ሙስናን በመዋጋቱ ረገድም ቢሆን አቅም እንደሌለ አሳይቷል።»

ማያ ብራዉን

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic