የኬንያ ምርጫና የሴቶች ተሳትፎ | አፍሪቃ | DW | 03.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኬንያ ምርጫና የሴቶች ተሳትፎ

በኬንያ የፊታችን ሰኞ እአአ መጋቢት አራት፡ 2013 ዓም የሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ፡ ምክር ቤታዊ እና ሀገረ ገዢዎች ምርጫ ያካሂዳሉ። ፕሬዚደንታዊው ምርጫ በሀገሪቱ አንድ ትልቅ ለውት ሊያስገኝ ይችል ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ምክንያቱም በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን የተወሰኑ የምክር ቤት መንበሮች ለሴቶች ብቻ ተመድበዋልና።

በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎን ለማበረታታት የተወሰደው ይኸው ርምጃ በቀላሉ የማይታይ ነው። እስካሁን እንደታየው ኬንያውያቱ በሀገሪቱ ፖለቲካ የያዙት ሚና ያን ያህል የጎላ አይደለም።
በኬንያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ ወይዘሮ ማርታ ካሩዋ በተወዳዳሪነት የቀረቡ  ብቸኛዋ ሴት ዕጩ ሲሆኑ፡ የመመረጥ ዕድላቸው የመነመነ ነው። ሰሞኑን በመጨረሻ የወጡ የሕዝብ አስተያየት መመዘኟ መዘርዝሮች እንዳሳዩት፡ ከመራጩ ሕዝብ መካከል አንድ ከመቶ ብቻ ነው ድምጹን እሳቸውን የሚመርጠው።

በኬንያ ፖለቲካ ለከፍተኛው የሀገሪቱ ሥልጣን ትልቁ ፉክክር የሚካሄደው በወንዶቹ መካከል ነው። ከካሩዋ ሌላ በዕጩነት የቀረቡት ሰባት ኬንያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ፤ ምክትላቸዉ ዑሁሩ ኬንያታ፤ ፒተር ኬኔዝ፤ ጄምስ ኦሌ ኪያፒ፤ ፓዉል ሙቲ፤ ሙሳሊያ ሙዳያዲ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ መምህር የሆኑት ሞሐመድ አብዱባ ዲዳ ናቸዉ።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚደረገው ፉክክርም ቢሆን በጣም አዳጋች ነው። ኬንያዊትዋ ራሄል ዬጎን በቀጣዩ አዲሱ ምክር ቤት ውስጥ የእንደራሴነትን ቦታ መያዝ ይፈልጋሉ። በምዕራባዊ ኬንያ በሚገኘው በኬሪቾ ከተማ ባለተቋም የሆኑት የጎን በብዙዎቹ ኬንያውያት አንፃር ጥሩ የገቢ ምንጭ ያላቸው ናቸው።
« ይህ ነው ትልቁ ችግር። ሴቶች በምጣኔ ሀብቱ ዘርፍ ተሳታፊዎች አይደሉም። በመጀመሪያ ደረጃ በፖለቲካው ዘርፍ መሳተፍ ትችል እንደሆን የባሏን ፈቃድ ማግኘት ይኖርባታል፤ ያ ከሆነ በኋላ ለመንቀሳቀሻ የሚያስፈልጋትን ተሽከርካሪ፡ ገንዘብ እና ሌላ ብዙ ቁሳቁስ ለማግኘት በየጊዜው መጠየቅ አለባት። እና ወንዱ በዚህ ስለሚሰላች ሴቷን ለማበረታታት አይፈልግም። »
በኬንያ የምርጫ ዘመቻ በጣም ውድ ስለሆነ ገንዘብ የግድ አስፈላጊ ነው። ከመጓጓዣ ወይም የተፎካካሪው ሥዕልና መፈክር ከሚታይበት ሰሌዳ ጎን በዕጩነት ለመመረጥ፡ በመገናኛ ብዙኃን ለሚወጡ ማስታወቂያዎች እና ድምፁን የሰጣል ተብሎ ለሚታሰብ መራጭ ሕዝብ የገንዘብ ስጦታ ማድረግ ይጠበቃል።


ሴቶች በፖለቲካው ዘርፍ ላለው ንዑሱ ተሳትፎ የሴቶቹች ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃም ተጠያቂ ነው። ከፍተኛ ሥልጣን ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ይጠይቃል። በዚህም የተነሳ በተለይ ከመዲናይቱ ናይሮቢ ራቅ ብለው በሚገኙት በሰሜን ኬንያ እና በባህሩ ዳርቻ ከሚገኙት አካባቢዎች፡ እንዲሁም፡ በደቡባዊ ኬንያ ከሚኖረው የማሳይ ሕዝብ መካከል ለምክር ቤት እንደራሴነት ቦታ የሚወዳደሩት  ሴቶች ቁጥር በጣም ንዑስ ሊሆን እንደሚችል የምርጫ ታዛቢዎች ሠግተዋል። ከሁለት ዓመት በፊት በወጣው አዲሱ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት፡ መጀመሪያ ላይ ብዙ ሴቶች በኬንያ ምክር ቤት እንዲወከሉ ለማድረግ ነበር የተወሰነው። ማንኛውም ፆታ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ፡ በምክር ቤት ጭምር ካሉት ቦታዎች ውስጥ የሚይዘው ቦታ ከሁለት ሦስተኛው እንዳይበልጥ የ 2010 ዓምሕረቱ ሕገ መንግሥት ያዛል። ይሁንና፡ ባለፈው ታህሳስ 2012 ዓም የኬንያ ላዕላይ ፍርድ ቤት ይኸው የሕገ አንግሥቱ አንቀጽ ከሚቀጥለው ሣምንቱ አጠቃላይ ምርጫ በኋላ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ አሳልፎዋል። ያም ቢሆን ግን በኬንያ ምክር ቤት ውስጥ የሴቶች እንደራሴዎች ቁጥር መጨመሩ አይቀርም። እስከሁን በምክር ቤቱ ካሉ 222 መንበሮች በተጨማሪ ለሴቶች 47መንበሮች፡ ማለትም፡ ለየምርጫው አካባቢ አንድ መንበር እንዲመደብ መወሰኑን የወደብ ከተማ ሞምባሳ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ዕጩ ሀሰን ኦማር ገልጸዋል።
« በኬንያ የሴቶች እንቅናቄ በጣም ቅር ተሰኝቼአለሁ። አሁን ተጨማሪ የእንደራሴ በመመደቡ፡ ብዙዎቹ ሴቶች በዚሁ የምክር ቤት መንበሮች ላይ ብቻ በማትኮር ያላቸውን ሌላውን ሰፊ የምርጫ ዕድል ችላ ብለዋል። »


ወይዘሮ ራሄል ዬጎን ላካባቢያቸው ለተመደበው የምክር ቤት መንበር ከአንድ ወንድ አቻቸው ጋ ይፎካከራሉ። ፉክክሩ ጠንካራ መሆኑን ነው የገለጹት።
ባህሉ ሴቶችን ይጨቁናል። ብቃት እንደሌላቸው አምነው እስኪቀበሉ ድረስ ይጨቁናል። ብዙ ገደብ አለባቸው ለምሳሌ በቤት ውስጥ ሁሉን የሚሰሩት እነሱ በመሆናቸው እንደልብ ተደራሽ አይደሉም። ልጆቻቸው ያደጉ ብቻ ናቸው ሊንቀሳቀሱ የሚችሉት።
ሴቶች በምክር ቤት በሰፊው መወከል ሲችሉ ብዙ ስራ ሊሰሩ እንደሚችሉ በናይሮቢ የሚገኘው የጀርመናውያኑ የሀይንሪኽ በል ተቋም ባልደረባ ኬንያዊትዋ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ጆን ቢሪካ በርግጠኝነት ገልጸዋል።
« በምክር ቤት የተወከሉት ሰባቱ ወይም ስምንት ወይም ዘጠኝ ከመቶ ሴቶች እንደራሴዎች ስራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ያከናወኑትን ስራ፡ ማለትም ያቀረቡዋቸው ረቂቅ ሀሳቦች ሕግ እና ፖሊሲዎች ሆነው እንዲወጡ ምን ያህል ተፅዕኖ ማሳረፍ እና ለውጥ ለማስገኘት እንደቻሉ ለማየት እንችላለን። ለወትሮው ትኩረት የማያገኙ ሰዎችን ምን ያህል ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻሉ ይታያል። ለምሳሌ የአልክሆል መጠጥን አጠቃቀምን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች ወጥተዋል። በሕገ ወጡ የአልክሆል መጠጥ የተነሳ በወጣቱ ዘንድ ትልቅ የስራ አጥነት ችግር አለብን። እና አዲስ ከወጡት ሕጎች አሁን ሴቶች እና ወንዶች ተጠቃሚዎች ሆነዋል። »
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሯ ጆን ቢሪካ  ኬንያውያኑ ሴቶች በወንዶች አንፃር  ጎሣዊ እና ባህላዊ ድንበሮችን ማስወገድ ስለማይከብዳቸው የጎሣን ውዝግብ በመቋቋም ትኩረታቸውን በፖለቲካው አጀንዳ ላይ ማሳረፍ እንደሚችሉ ተስፋ አድርገዋል።

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን 

Audios and videos on the topic