የኬንያው ምርጫና በጀርመን የሚኖሩ ኬንያውያን፤ | አፍሪቃ | DW | 07.03.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኬንያው ምርጫና በጀርመን የሚኖሩ ኬንያውያን፤

በውጭ ሃገራት የሚኖሩት ኬንያውያን ቁጥር ፤ እንደ ሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ግምት፣ 3 ሚሊዮን ገደማ ይሆናል። ብዙዎቹ የሚኖሩት በዩናይትድ እስቴትስ ነው። ቁጥራቸው አነስተኛ የማይባልም በአውሮፓ ይገኛሉ ፣ በጀርመን ጭምር። ታዲያ ፤ በኬንያ ታሪክ

ለመጀመሪያ ጊዜ እነዚሁ በውጭ ሃገራት የሚገኙ ተወላጆቿ ፣ የምርጫ ተሳታፊዎች ለመሆን እንደሚፈቀድላቸው ተስፋ ነበራቸው። ይሁን እንጂ ዕድሉ የተሰጠው፣ በምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ አባል ሃገራት ለሚኖሩ ኬንያውያን ብቻ ነው። በጀርመን የሚኖሩ ኬንያውያን ፣ በትውልድ ሀገራቸው ስለተካሄደው ምርጫ ምን ይላሉ? የዶቸ ቨለ ባልደረባ ካርል ኦፎሪ ጥቂቶቹን አነጋሯል። ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

በጀርመን ከሚኖሩት ኬንያውያን መካከል አብዛኞቹ፣ ኮምፒዩተር ላይ ዓይናቸውን ተክለው የዘንድሮውን ምርጫ ተከታትለዋል። ከሞላ ጎደል የምርጫው ተሳታፊዎች መሆናቸውም ተሰምቷቸዋል። ማክሰኞ ማታ ግልጽ የሆነ የምርጫ ውጤት አልተገኘም። ግምቱ ግን ጠንከር ያለ ነበረ። ክርስቲን ቡካንያ፣ በ DW አካደሚ፣ ጋዜጠኝነት ተማሪ ናት። የአሁኑን የኬንያ ምርጫ፣ እ ጎ አ በ 2007-2008 ከተካሄደው ጋር እንዲህ ታነጻጽረዋለች።

«ይኽኛው፣ እጅግ የተወሳሰበ ነው። ለብዙ መናብርት ነው ህዝቡ ድምፅ የሰጠው። እንደሚመስለኝ፤ ለብዙ የምርጫ ካርዶች፣ ዋጋቢስ መሆን አስተዋጽዖ ሳያደርግ አልቀረም። ባ,ሁኑ ጊዜ ህዝቡ ይበልጥ በተደራጀና በተባበረ መንፈስ ነው በምርጫ የተሳተፈው። በመምረጣቸው የተኩራሩም አልታጡም። ስለሆነም ይበልጥ በአዎንታዊ መልኩ ነው የተጠናቀቀው።

ከ 2007 ቱ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር የጎሳ ስሜት የቱን ያህል በኬንያውያን ላይ ተጽእኖ አሳድሮአል? ለዚህ ጥያቄ ሌላው ኬንያዊ ሂልሪ ሳንግ መልስ አላቸው። ሳንግ፣ ቦን በሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት የፋይናንስ ረዳት ባለሙያ ናቸው።

«ኬንያ፣ ከበፊቱ አሁን እርምጃ አሳይታለች። እንዳለፈው ጊዜ በጎሳ እይታ ባተኮረ መንፈስ መምረጥ ዐቢይ ግምት አልተሰጠውም። ይሁንና ሰዎች፣ እንዴት እንደሚመርጡ ጠንከር ያለ ተጽእኖ ያሳደረበት ሁኔታ አልተወገደም። »

በዛ ያሉ በውጭ የሚኖሩ ኬንያውያን አሁንም ቢሆን፣ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ደኅንነት ይዞታ ያሳስባቸዋል። ቲተስ እንዱንዳ በተባበሩት መንግሥታት የምርምር ረዳት በመሆን የሚሠሩ ሲሆን፣ አንዳንድ ዋስትና የሚሰጡ ዜናዎችን ማዳመጣቸው አልቀረም።

«ወንድሜን የማነጋገር ማለፊያ ዕድል ገጥሞኝ፣ ሁሉም በተስተካከለ ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ነገረኝ። እርሱ መርጧል። ሂደቱ የተሣካ ነበረና የፀጥታ ሥጋት አላጋጠመም። እናም ማንኛውንም ነገር ለመቆጣጠር ተችሏል።»

ምርጫው በአጠቃላይ በሰላም ቢጠናቀቅም፣ ብዙዎች ኬንያውያን ብሩኅ ተስፋ ያሳድሩ እንጂ አሁንም ቢሆን፤ የአገሪቱ የፀጥታ ይዞታ ያሳስባቸዋል። ቲተስ እንዱንዳ፤ ማንም ከፍተኛውን ሥልጣን ያያዝ ፣ ይህ የአዲሱ ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ አጀንዳ መሆን ይኖርበታል ይላሉ ።

« እኔ እንደማስበው ፕሬዚዳንቱ ለጸጥታ አጠባበው ላቅ ያለ ግምት መስጠታቸው በጣም ጠቀሚ ነው። ከዚያም፤ ኤኮኖሚ በአጅጉ ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ለወጣቱ ሥራ መፍጠር! ምክንያቱም፣ በዛ ያሉ ወጣት ባለሙያዎች አገሪቱን እየለቀቁ በውጭ የተሻለ፣ የተደላደለ ኑሮ ያሻሉና!»በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኬንያውያን፣ ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ከየትኛውም ጎሳ ይሁን፤ ደንታ የላቸውም። አጥብቀው የሚመኑት፣ መጪው መሪ ኬንያን እመርታ በሚያንጸባርቅ አመላካከት፣ የጎሳ ሁከትን ምዕራፍ ከእነአካቴው እንዲዘጋ ያደርግ ዘንድ ነው። ይህ ቀና አመለካከታቸውና ምኞታቸው እስከምን ይሠምርላቸው ይሆን?

Global Media Forum Session 4 Plenarsaal Itai Mushekwe

የተፈራው የ 2007 ምርጫ መዘዝ ያገረሽ ይሆን?አይታወቅም። ሥጋቱ ግን አልተወገደም። ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት ጠ/ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ፤ ረዳታቸውም ሆኑ ምክትላቸው ካሎንዞ ሙሲዮካ ፣ የድምፅ ቆጠራው እንዲገታ በዛሬው ዕለት ከመጠየቃቸውም፤ ምርጫው ከተካሄደ ከ 3 ቀናት ወዲህ የድምፅ ቆጠራው ሂደት ሐቀኝነት እንዳጠራጠራቸው ገልጸዋል። ሙሲዮካ፣ የሆነው ሆኖ ሒሳቸው ፣ ህዝብ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አለመሆኑን አስገንዝበዋል። የድምጽ ቆጠራው ዓርብ መጠናቀቅ ቢችልም እስከመጪው ሰኞ ሳይዘልቅ እንደማይቀር፤ የነጻው የምርጫና የወሰኖች ጉዳይ ኮሚሽን ሊቀመንበር አህመድ ኢሳክ ሐሰን አስታውቀዋል።

በኬንያ ፣ ከ 14,3 ሚሊዮን ብቁ መራጮች መካከል፣ ከ 70 ከመቶ በላይ አደባባይ ወጥተው ሳይመርጡ አልቀሩም።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 07.03.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17tBw
 • ቀን 07.03.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17tBw