የካንጋሮ እናቶች ክብካቤ ለሕጻናት | ጤና እና አካባቢ | DW | 28.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የካንጋሮ እናቶች ክብካቤ ለሕጻናት

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተለያዩ ምክንያቶች ያለጊዜያቸው የሚወለዱ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ የጤና ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ  በማድረግ ላይ ነው። ለዚህ አላማ ተግባራዊ ከተደረጉት የጤና ፕሮጀክቶች መካከል በደቡብ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች በሙከራ ደረጃ የሚገኘው የካንጋሮ እናቶች  ክብካቤ  በቀዳሚነት  ይጠቀሳል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:55

ፕሮጀክቱ በደቡብ ክልል በሥራ ላይ ውሏል

የዓለም ጤና ድርጅት እንደአውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጣር በ2016 ዓ ም ባካሄደው ጥናት በየዓመቱ ይህችን ዓለም ከሚቀላቀሉ ሕጻናት መካከል  15 ሚሊዮን ያህሉ ከአማካኝ ክብደታቸው በታች ሆነው የሚወለዱ ናቸው። በድርጅቱ ጥናት መሠረት ከእነኝሁ ጨቅላ ሕጻናት መካከል 2 , 6 ሚሊዮን ያህሉ ለሞት ይዳረጋሉ። የጨቅላ ሕጻናት ሞት ያሳሰባቸው የህክምና ባለሙያዎች የካንጋሮ እናቶች ክብካቤን በአማራጭ መፍትሄነት ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ጥቂት አስርተ ዓመታትን አስቆጥረዋል።
ካንጋሮ በመባል የምትጠራው እንስሳ በተፍጥሮ ለግልገሎቿ ከምታደርገው አያያዝና ክብካቤ የተቀዳው ይሄው የህክምና ዘዴ  የጨቅላ ሕጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር  በደቡብ ፣ በአማራ ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች ውስጥ ለሙከራ በተመረጡ አካባቢዎች ከባለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የካንጋሮ እናቶች ክብካቤን ተግባራዊ እያደረገ ነው።
በተለይም በደቡብ ክልል የካንጋሮ እናቶች ክብካቤን  ፕሮጀክት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ኮሌጅ አስተባባሪነት በሀዋሳ ከተማ ፣ በሸበዲኖ እና በዳሌ ወረዳዎች እየተሠራ ይገኛል። በዩኒቨርሲቲው የሕጻናት ሀኪምና የካንጋሮ እናቶች ክብካቤ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሄኖክ ታደለ የፕሮጀክቱን ጠቀሜታና አጀማመር እንዲህ ይገልዳሉ።


<<የዚህ የካንጋሮ እናት ክብካቤ በዓለም ደረጃ ከተጀመረ ወደ 50 ዓመት ሆኖታል። በዋናነት ደግሞ የሚሰጠው ሲወለዱ ኪሏቸው  አናሳ ሆኖ ለሚወለዱ ሕጻናት ነው። ሁለት ኪሎ ግራም እና ከዚያ በታች ሆነው ለሚወለዱ ሕጻናት ነው። ኪሎ ደግሞ ሕጻናት በሚወለዱበት  ወራት ነው አብሮ የሚያያዘው። ስለዚህ ሁለት ኪሎ ግራም እና ከዚያ የሆኑት ባብዛኛው ያለ ጊዜያቸው የተወለዱ ሕጻናት ናቸው። እንደእኛ ባላደጉ ሃገራት ደግሞ የተለያዩ ማሽኖችን ፣ የተለያየ የሕክምና ዕቃዎችን ማግኘት በማንችልባቸው ሁኔታዎች ደግሞ እነዚህ የካንጋሮ እናት ክብካቤ ወጪ የማያስወጣ፣ ከቤተሰብ አባላት ማንኛውም ሰው መስጠት የሚችለው ደግሞ ፍቱን መሆኑ በጣም የተረጋገጠ ነው።>>
በክልሉ የካንጋሮ እናቶች አንክብካቤ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየታቸውን ም ዶክተር ሄኖክ ይናገራሉ።


የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ ትዝታ አዳነ ትዳር በመሠረተች ማግስት እንደአብዛኞቹ እናቶች ወልዳ የመሳም ጉጉቷ የበረታ ነበር። ይሁንእንጂ በአርግዝና ላይ እንዳለች በድንገተኛ ያጋጠማትን የሆድ ህመም ለመታክም በአቅራቢያዋ ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ ታመራለች። ምርመራ ያደረጉላት ሀኪሞችም የህመሞ ምክንያት በሆዷ የሚገኘው ፅንስ መሆኑን በመግለፅ ሕይወቷን ለማትረፍ በቀዶ ህክምና መውጣት እንዳለበት ይነግራታል ።
በተካሄደው ቀዶ ህክምና የትዝታን ሕይወት ማትረፍ ቢቻልም የስድስት ወር ፅንስ የሆነችው እና 800 መቶ ግራም ብቻ የምትመዝነው ጨቅላ ሕጻን በሕይወት የመኖር ዕድሏ አጠራጣሪ መሆን ግን የልጅ እናት የመሆን ተስፋዋን አጨልሞባት እንደነበር ትናገራለች ።

ሆኖም በዚህ የካንጋሮ እናቶች ክብካቤ ልጅዋ ሊያድግላት መቻሉን ትናገራለች። እሷ ብቻ ሳትሆን አሁን ብዙዎችም ይህን እንዲጠቀሙ በመርዳት ጤናማ ልጆችን እንዲያሳድጉ እያደረጉ መሆናቸውን እማኞች ይናገራሉ።

ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ፤

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic