የካራዲች ፍርድ፤ ምክንያቱና እንድምታዉ | ዓለም | DW | 28.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የካራዲች ፍርድ፤ ምክንያቱና እንድምታዉ

አዉሮጳ ስደተኛ ማስተናገድ ጠልቶ እየተጠላለፈ ነዉ። ከዓለም ምጣኔ ሐብት 20 ትሪሊዮን ዶላር የምትዝቀዉ ዩናይትድ ስቴትስ የነዶናልድ ትራምፕን ዘረኛ እፅ በሕዝቧ መሐል ለማፅደቅ እየኮተኮተች ነዉ።ዘረኛ ብሔረተኞችን መከላከያዉ ፖሊሲ፤ የአስተሳሰብ ለወጥ እና ፍትሐዊነት ሳይኖር «ከእንግዲሕ አይደገምም» ብሎ መፈክርም ለዉጤት አለመብቃቱ ሐቅ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:53

የካራዲች ፍርድ፤ ምክንያቱና እንድምታዉ

ከሕዳር 1945 እስከ ጥቅምት 1946 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኑረንበርግ ጀርመን ያስቻለዉ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በናትሴ-ጀርመን ባለሥልጣናት ላይ የወሰነዉ ፍርድ በእስከዚያ ዘመኑ የፍርድ ቤት ታሪክ «ታላቅ» እና «ታሪካዊ» ተብሎ ነበር።ብይኑ የናትሴ መሪዎች የፈፀሙት ግፍ እንደማይደገም ማረጋገጪያ ሆኖ የጦርነቱም፤ የፍርዱም ተሳታፊዎች «ጨርሶ አይደገምም፤ Never again» የሚል ቃል ገብተዉም ነበር።ይሁንና 50ኛ ዓመቱ ከአፍሪቃዋ ሩዋንዳ እስከ አዉሮጳዋ ይጎዝላቪያ የተፈፀመዉ ጭፍጨፋ የዚያ አስተምሕሮ፤ የቃል፤ ምሕላዉ ጋጋታ ለመብነኑ ጉሉሕ ምልክት ነበር።ከዩጎዝላቪያዉ ጭፍጨፋ መሪዎች በአንዱ ላይ ባለፈዉ አርብ የተላለፈዉ ብይን አዉሮጶችን ማቃራኑ፤ ከሶሪያ እስከ ደቡብ ሱዳን፤ ከአዉሮጳ-እስከ አሜሪካ ካለዉ ሐቅ ጋር ሲዳመር በጭፍጨፋ ማግስት ቃል የሚገባላት ዓለም ከጭፍጨፋ ዑደት ላለመላቀቅዋ አብነት እንዳይሆን ነዉ ሥጋቱ።ፍርዱ መነሻ፤ ተቃርኖዉ ማጣቀሻ፤ ሥጋቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

አሜሪካኖች የወደፊት መሪያቸዉን ለመምረጥ እየተከራከሩ፤ እየመከሩ፤ ለየዕጩዎቹ ድምፅ እየሰጡ ነዉ።ያሁኑ መሪያቸዉ ኩባ ነበሩ።የዓለም ልዕለ ሐያል ሐገር ሕዝብ፤ ፖለቲከኞች፤መሪም የዚያን ቀን ከዕጩ መረዎች ምርጫ እስከ ትንሽ፤ ዉብ፤ ጎረቤታቸዉ፤ ግን የረጅም ጊዜ ጠላቸዉ ኩባ ከማሰብ ማብሰልሰል ካለፉ፤ አንድም ከብራልስ-ሽብር አለያም ከሶሪያ ጦርነት በላይ ብዙም የሚያስጨንቃቸዉ አልነበረም።

የአዉሮጳ ፖለቲከኞችም ሆኑ መሪዎች ርዕሰ-ከተማቸዉ ብራስልስ ላይ ለደረሰዉ ሽብርና መከላከያዉ ሰበብ ከመደርደር አልፈዉ መሠረታዊ ምክንያቱ እንዳይጋለጥ በሚባትሉበት መሐል የመጥፎ ታሪካቸዉ አንድ ምዕራፍ ዘሔግ-ኔዘርላንድስ ዉስጥ ሲተረክ ለማድመጥ ጊዜ አልነበራቸዉም።ታሪኩ አንዲት ግዛት፤ ቦስኒያ ሔርሶጎቪና የተፈፀመ፤ የሰወስት ዓመት ክስተት ነዉ።ከ1992 እስከ 1995።አጭር-ጊዜ ግን ዉስብስብ፤ አደናጋሪ ግን ዘግናኝ-ዘር ማጥፋት።ዘ-ሔግ ኔዘርላንድስ ያስቻለዉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የመሐል ዳኛ አጠቃለሉት።

«ችሎቱ ከዚሕ ቀጥሎ እርስዎን፤ ራዶቫን ካራዲችን በአርባ፤ 4-0-ዓመት እስራት ቀጥቶዎታል።»ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ባወደማት ሞንቴንግሮ ፍርስራሽ መሐል ጦርነቱ በይፋ በቆመ በወሩ ነዉ የተወለዱት።ሰኔ 1945።ራዶቫን ካራዲች።የናትሴዎችን ጭፈጨፋ፤ በጨፍጫፊዎች ላይ የተላለፈዉን ፍርድ፤ ከሁሉም በላይ አዉሮጳ ምድር «ሁለተኛ አይደገምም» የሚለዉን የዓለም ሐያላንን ቃል-ኪዳን እያዳመጡ ነዉ ያደጉት።

ችግር-ስደትን ከሌሎች ሰምተዉ ሳይሆን ከሞንቴኔግሮ-ሳራዬቮ፤ከሳራዬቮ ቤልግሬድ፤ ከቤልግሬድ ፓሌ ግዛት ከተማ ሲያቀያይሩ ነዉ ያደጉት።ዉልደት፤ ዕድገት፤ የኑሮ ልምድ አስተሳሰብ እምነት፤ ምግባርን የሚበይን ቢሆን ኖሮ የካራዲችን ያክል ዘረኝነትን የሚጠላ፤የሚታገል፤ ለስደተኛ እና ችግረኛ የሚያዝን ባልኖረ ነበር።

ትምሕርት የሰዉን አዕምሮ ለበጎ ዓላማ ብቻ የሚሞርድ ፤ የመግደል፤ ማስገደል፤ማሰደድ ማፈናቀልን አስተሳሰብ የሚያግድ ቢሆን ኖሮ የሰዉ ሕይወትን ለማትረፍ ሕክምናን፤ የሰዉን አዕምሮ ለማረቅ ሥነ-ልቡና (ሳይካትሪ)ን ከይጎዝላቪያ-እስከ ዩናይትድ ስቴትስ ድረስ የተማሩ፤ የተመራመሩት ሐኪምም፤የስነ ልቡና አዋቂም ከዚያ እልቂት እጃቸዉን ባልዶሉ ነበሩ።

ረጅሙ፤ ጎፈሬዉ፤ ሰርቡ ዶክተር ሕክምናዉን በፖለቲከ ለዉጠዉ፤ በነጭ ገዋናቸዉ ምትክ-ፋቲግ ለብሰዉ በኪኒን ፋንታ ቦምብ፤ ጥይት እያደሉ፤ ሕዝብ አስጨርሱ።ያደጉ፤የተማሩ ለወግ ማዕረግ የበቁበትን የሳራዬቮን ሙስሊምና ክሮአት ሕዝብ አስከብበዉ በዉሐና ምግብ እጥረት ፈጁት።ባልን ከሚስቱ፤ ልጅን ከናቱ እያስነጠሉ መቶ ሺዎችን አስጨፈጨፉ።ዛሬም ግን ያጠፋሁት የለም ባይ ናቸዉ።

የቦስኒያዉን ጦርነት በመዘገቧ ስም ዝና ያተረፈችዉ የአሜሪካ ቴሌቪዥን (CNN) ጋዜጠኛ ክርስቲያን አማንፑር እንዳለችዉ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ባለፈዉ አርብ ያሳለፈዉ ብይን ራዶቫን ካራዲች እና የተባባሪዎቻቸዉ ክሕደት መሠረት እንደሌለዉ የሚያረጋግጥ ነዉ።

«ይሕ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ለአዉሮጳ በጣም አስፈላጊና ትልቅ ፍርድ ነዉ።ሃያ ዓመት በልጦታል።የቦስኒያ ሕዝብ ፍትሕ ለማየት ለረጅም ጊዜ ናፍቋል።ካራዲች አሁንም በመጨረሻዉ ሰዓት ወንጀሉን አልፈፀምኩም፤ ስለ ግድያዉ የማዉቀዉ የለም፤ ከኔ ጋር ምንም ግንኙነት የለዉም ብለዋል።ዛሬ ዘ-ሄግ ያስቻለዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔ ግን አነዚሕ ሁሉ ዉሸት መሆናቸዉን የሚያረጋግጥ ነዉ።»

በ1990ዎቹ

መጀመሪያ የእስከያኔዋ ይጎዝላቪያ ፌደሬሽን ሪፐብሊኮች የየራሳቸዉን ነፃነት ሲያዉጁ የቦስኒያ ሔርሶጎቪና ሶሻሊስታዊት ሪፐብሊክ ሕዝብም የሌሎቹን ሪፐብሊኮች ፈለግ የማይከተልበት ምክንያት አልነበረም።ከሪፐብሊኪቱ ህዝብ 45 ከመቶዉ ሙስሊም፤ 30 በመቶዉ የኦርቶዶክስ ሰርብ፤ አስራ-ሰባት ከመቶዉ ካቶሊክ ክሮአት ነበር።

የካቲት ማብቂያ 1992 በተደረገዉ ሕዝበ-ዉሳኔ የቦስኒያ ሔርሶ ጎቪና ሕዝብ ነፃነቱን አወጀ።በሕዝበ ዉሳኔዉ ድምፃቸዉን ያልሰጡት የሰርብ ፖለቲከኞች ዉሳኔዉን ተቃወሙት።የአዉሮጳ ማሕበረሰብ እና ዩናይትድ ስቴትስ ግን በሕዝበ ዉሳኔዉ መሠረት ለተመሠረችዉ ለቦስኒያ ሔርሶ ጎቪና ሪፐብሊክ የመንግሥትነት እዉቅና ሰጧት።

ብዙም አልቆየ።ራዶቫን ካራዲች እና ብጤዎቻቸዉ ሰርቦች በሚበዙበት የቦስኒያ ሔርሶ ጎቪና አዉራጃ ሪፐብሊካ ስርፕስካ የሚል መንግሥት መሠረቱ።የሰርቦቹ ሪፐብሊካ ስርፕስካ እና የይጎዝላቪያ ጠንካራ ጦር ሙስሊሞችን እና ክሮአቶችን ይገድል ገባ።ካቶሊኮቹ ክሮአቶች ወደ ክሮኤሽያ የመሰደድ ዕድል ስለነበራቸዉ የሰርቦች ንዴት፤ጥይትም ማብረጃ የሆኑት አብዛኞቹ ሙስሊሞች ናቸዉ።

ጄኔራል ራትኮ ሚላዲች እንደ ጦር አዛዥ፤ ዶክተር ራዶቫን ካራዲች እንደ የሰርፕስካ ፕሬዝደንትም የጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥም፤የዩጎዝላቪያዉ ፕሬዝደንት ሶሎቮዳን ሜሎሶቪች እንደ ጠንካራዉ የይጎዝላቪያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ባንድ አብረዉ ያዘመቱት ጦር መቶ ሺዎችን ፈጀ።አብዛኛዉ ሙስሊም ነዉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ በሰወስቱ የሚመራዉ የሰርቦች ጦር በተለይ ሰሬብሬኒሳ በተባለችዉ ከተማ ከስምንት ሺሕ በላይ ትጥቅ አልባ ወንዶችን አዋቂ ከልጅ ሳይሉ በጅምላ ጨፍጭፏል።ሐኪሙ፤ ሳይካትርስቱ ዶክተር እና ተባባሪዎቻቸዉ የሚመሩት ጦር ርዕሠ-ከተማ ሳራዬቮን ከብቦ በሽተኛዉን በመድሐኒት እጦት፤ ሕፃን አዛዉንቱን በዉሐ እና በምግብ እጥረት ፈጅቷል።

ሰዉዬዉ ግን ያን ዘግናኝ ድርጊት ከፈፀሙ ወይም ካስፈፀሙ ከ20 ዓመት በኋላ አሁንም አልተፀፀቱም።ያሁሉ መረጃ፤ ያሁሉ ሰነድ፤ የመቶ ሺዎች አስከሬን ከየጉርጓዱ እየተዛቀ፤እየተከመረም ሐኪሙ፤ የሥነ-ልቡና አዋቂዉ ዶክተር-ፖለቲከኛ ሊፀፀቱ ቀርቶ በጠበቃቸዉ በኩል ይግባኝ ለመጠይቅ ወስነዋል።«ዶክተር ካራዲች በ(ፍርዱ) በጣም አዝነዋል፤ ተገርመዋል።ችሎቱ (ለፍርዱ) ከመረጃ ይልቅ ስሜትና ጫናን መሠረት ያደረገ ነዉ የሚል እምነት ሥላደረባቸዉ ይግባኝ ለመጠየቅ ወስነዋል።»

የስሬብሬንስካዉ የዘር ማጥፋት አስረኛ ዓመት በ2005 ሲዘከር የያኔዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን እንዳሉት ለጭፍጨፋዉ ከሜሎሶቪች እስከ ሚላዲች እስከ ከካራዲች ያሉ የሰርብ ፖለቲከኞችና የጦር አዛዦች ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች ቢሆኑም «ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ» የሚባለዉ ሐያል ዓለምም ተጠያቂ ነዉ።

የሰርብ ወታደሮች ስሬብሬንሳ ዉስጥ አዋቂዉን ከሚስቱ፤ ልጁን ከናቱ እየነጠሉ፤ እንደ ጆንያ ደርድረዉ ሲረሽኑት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያዘመታቸዉ የኔዘርላንድስ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጠመንጃቸዉን ታቅፈዉ ዘግናኙን እርምጃ እንደ ጥሩ ትርዒት ይመለከቱት ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ራሱ የተመሠረተዉ የዓለም አድራጊ ፈጣሪዎች በ1945 ከእንግዲሕ በቃ ያሉትን እልቂት ፍጅት ለመከላከል ነበር።አስከፊዉ ጦርነት ባበቃ በሐምሳኛ ዓመቱ በዚያ ጦርነት ትቢያ ላይ በተመሠረተችዉ አዉሮጳ ዉስጥ ያን መሰሉ ጭፍጨፋ መፈፀሙ የድርጅቱን ዓላማ ዳግም አስተዛዛቢ አድርጎቷል።ጭፍጨፋዉን ያዩ ወይም ዘመድ ወዳጆቻቸዉን ያጡ ወገኖች በካራዲች ላይ የተላለፈዉ ዉሳኔ ከመዘግየቱ ማነሱ፤ ከማነሱ ካራዲች ይግባኝ እጠይቃለሁ ማለታቸዉን እንደተጨማሪ ግፍ ነዉ ያዩት።

«ዘር የጠፋዉ ስሬብሬንሳ ብቻ አይደለም።በመላዉ ቦስኒያ ሄርሶ ጎቪና ዘር ማጥፋት ወንጀልም፤ ግድያ ግድያም፤ ሥቃይም ሁሉንም ዓይነት ግፍም ተፈፅሞብናል።»ጭፈጨፋዉ፤ ጋዜጠኛ ክርስቲያን አማንፑር እንደታዘበችዉ የነራዶቫን ካራዲች አረሜናዊ አስተሳሰብ ዉጤት ብቻ አይደለም።የምዕራቡ ዓለም ቸልተኝነት ነፀብራቅ ጭምር እንጂ።

«እኒያን ሰለቦች ምንም ነገር አይመልሳቸዉም። ምዕራባዉያን በ21ኛዉ ክፍለ-ዘመንም ፖለቲካዊ ፍቃደኝነት ባለማሳየታቸዉ፤ ጣልቃ ለመግባት ባለመፈለጋቸዉ ፤ሰዎች የከፈሉትን አላስፈላጊ መስዋዕትነት ያሁኑ ፍርድ አያስቀረዉም።ፍላጎቱ ሥለሌ ወይም አቅም ስለሌለ ብቻ ያን መሠሉ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል።ሚሊዮኖች ወደ ሌላ የአዉሮጳ ሐገራት ተሰደዋል።ይሕ በሃያ አንደኛዉ ክፍለ ዘመን ከተፈፀሙት ጭፍጨፋዎችና ጅምላ ስደቶች የመጀመሪያዉ ነዉ። አሁን ደግሞ በጣም በከፋ መልኩ ሶሪያ ዉስጥ እያየን ነዉ።»

ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላም ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ የዓለም ዘዋሪዎች ባለመፈለጋቸዉ ዓለም አመታት ለመጠበቅ ተገድዳለች።

ራዶቫን ካራዲች ሰዎችን ማስጨፍጨፉ ሲበቃቸዉ ወደ ሰርቢያ ተሻግረዉ እዚያ ይኖሩ ነበር።አሜሪካ መራሹ ጦር ከስልጣን ያስወገዳቸዉን ሳዳም ሁሴንን በወራት እድሜ ሲይዛቸዉ የሰርቦቹ ዶክተር-ፖለቲከኛ ጢማቸዉን አንዠርግገዉ እንደ ጥሩ ሐኪምም እንደ በሳል የሥነ-ልቡና አማካሪም ይሠሩ ነበር።

ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ሚርኔስ ኮቫች ባለፈዉ ሳምንት እንደፃፈዉ አዉሮጳ የካራዲችን ያክል በራስዋም ላይ ነዉ-ያስፈረደችዉ።ምክንያቱም ጭፍጨፋዉን ለማስቆም ብዙም የጣረ አልነበረምና።ከጭፍጨፋዉ በኋላም ካራዲችን ለመያዝ ሐያሉ ዓለም አስራ-ሰወት ዓመት አንቀላፍቷል።ሥላልቻለ አይደለም።ሥላልፈለገ-እንጂ፤ ጋዜጠኛዉ እንደታዘበዉ።

ዛሬም ከፍርዱ በሕዋላ የመብት ተሟጋቾች ፍርዱን የዘገየም ቢሆን ለፅንፈኛ ብሔረተኞችና ለዘረኞች ጥሩ ማስጠንቀቂያ ሲሉት ሩሲያ ፖለቲካዊ ጫና ያየለበት በማለት ተቃዉማዋለች። ከአምስት መቶ ሚሊዮን የሚበልጠዉ ሐብታሙ የአዉሮጳ ሕዝብ አንድ ሚሊዮን ስደተኛ ማስተናገድ ጠልቶ የአሐጉሪቱ ፖለቲከኞች እየተጠላለፉ ነዉ።

ከዓለም ምጣኔ ሐብት 20 ትሪሊዮን ዶላር የሚሆነዉን የምትዝቀዉ ዩናይትድ ስቴትስ የነዶናልድ ትራምፕን ዘረኛ እፅ በሕዝቧ መሐል ለማፅደቅ እየኮተኮተች ነዉ።ዘረኛ ብሔረተኞችን መከላከያዉ ፖሊሲ፤ የአስተሳሰብ ለወጥ እና ፍትሐዊነት ሳይኖር «ከእንግዲሕ አይደገምም» ብሎ መፈክርም ሆነ ማስጠንቀቂያ ለዉጤት አለመብቃቱ ሐቅ ነዉ።ሐቁ ነዉ ሥጋቱም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic