የካሌ ስደተኞ መነሳት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 24.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አብዛኞቹ ስደተኞች ከኢትዮጵያ፤ ኤርትራና ሱዳን የመጡ ናቸዉ

የካሌ ስደተኞ መነሳት

ፈረንሳይ ወደ ብሪታንያ ለመሻገር በድንበር ግዛትዋ ካሌ ዉስጥ ድንኳን ተክለዉ የሚኖሩትን በሽዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የማዛወር ሥራን ዛሬ ጀመረች። ስደተኞቹን ከቦታዉ የማስለቀቅ ሥራ በጀመረበት በዛሬዉ ዕለት ብቻ ከ2000 እስከ 2500 ስደተኞች በስድሳ አዉቶቡሶች እንደሚወሰዱ ተመልክቶአል።

በዚሁ ቦታ ላይ ስደተኞቹ የተከሏቸዉ ድንኳኞችና ከእንጨትና ላስቲኮች የሠሯቸዉ ቤቶች በነገዉ ዕለት እንደሚፈርሱ ተገልጿል።  ከፈረንሳይዋ ካሌ ከባህር በታች ምድር ለምድር ወደ ብሪታንያ በሚምዘገዘገዉ ባቡር ሃዲድ አቅጣጫን አስታከዉ የሰፈሩት በርካታ ስደተኞች ፤ ወደ ብሪታንያ የመግባታችን እድል የመነመነ ይሆናል ሲሉ ወደ ሌላ የፈረንሳይ ክፍል መዛወራቸዉን አልተቀበሉትም። በዚህ ምክንያትም ከፍተኛ ረብሻ ይነሳል የሚል ስጋት መኖሩም ተመልክቶአል። ስደተኖቹን በመርዳት ተግባር የተሰማራዉ የኬር 4 ካሊስ ድርጅት  መስራች ኬሪ ሞስሊ ስደተኞቹ ወደ ሌላ ቦታ ከመዛወራቸዉ በፊት ብዙ መረጃ ይሰጣቸዋል ይላሉ። 
«ከነሱ ጋር በመነጋገር የተቻለንን ሁሉ መረጃዎች እንሰጣቸዋለን ምክንያቱም ይህንን ስናደርግ ፤ የሚኖሩበትን ለቀዉ ሲሄዱ ምን ይገጥመናል የሚለዉን ፍራቻቸዉን ንዴታቸዉን በመቅረፍ ደህንነታቸዉን እናረጋግጥላቸዋለን። ያም ሆነ ይህ ይህ ቀን እንደሚመጣ ማወቅም ይኖርባቸዋል።» 
 በሌላ በኩል አንድ በስፍራዉ የሚኖር አፍሪቃዊ ስደተኛ ዝዉዉሩ የተሻለ መሆኑን ይናገራል። 
«ወደዚህ ስፍራ አዉቶቡስ መቶ ወደ ሌላ ቦታ ይወስደናል። ይህ ለኛ የተሻለ ነዉ። ምክንያቱም ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሕጋዊ የስደተኞች ማዕከል ነዉ የምንመጣዉ። » 
ትናንት ለዛሬ አጥብያ በርካታ ስደተኞች በፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወር ግጭት ማስነሳታቸዉና በአንጻሩ ፖሊስ አስለቃሽ ጢስ መተኮሱ  ተዘግቦአል።  በካሌ የስደተኞች መንደር ከሚኖሩት ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ ኤርትርያ ከሱዳንና አፍጋኒስታን የመጡ መሆናቸዉም ተዘግቦአል። 

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ

ተዛማጅ ዘገባዎች