የካሌ ስደተኞች እጣ ፈንታ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የካሌ ስደተኞች እጣ ፈንታ

የፈረንሳይ መንግሥት ከዚህ ቀደም ባወጣው እቅድ መሠረት ፣ በጫካው ውስጥ የሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ድንኳኖችን የክርታስ እና የላስቲክ ደሳሳ ጎጆዎችን ዛሬ ማፍረስ ጀምሯል ።ከትናንት ጀምሮ ስደተኞቹን እየመዘገበም 170 በሚደርሱ አውቶብሶች ወደ ሌሎች የፈረንሳይ ከተሞች እየወሰደ ነው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:16
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:16 ደቂቃ

የካሌ ስደተኞች ዕጣ ፈንታ

 

የፈረንሳይ መንግሥት ካሌ በተባለው ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ የነበሩ የስደተኞች ደሳሳ መጠለያዎችን ዛሬ ማፍረስ ጀምሯል ። በጫካው ውስጥ ይኖሩ የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞችም ፈረንሳይ ውስጥ ወደ ሚገኙ የተለያዩ ጊዜያዊ የማረፊያ ማዕከላት በአውቶብሶች እየተወሰዱ ነው ። ለአካለ መጠን ካልደረሱት የተወሰኑትንም ወደ ብሪታንያ እየተላኩ ነው ።የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን በካሌ ስደተኞች እጣ ፈንታ እና በፈረንሳይ እርምጃ ላይ ያተኩራል ።ከፈረንሳይ ከተሞች ከብሪታንያ በቅርብ ርቀት የምትገኘው የሰሜን ፈረንሳይዋ የወደብ ከተማ  ካሌ ዋነኛ የትራንስፖርት እና የንግድ ማዕከል ናት ። በአሣ ሃብት እና በንግድ ማዕከልነትዋም የምትታወቀው ካሌ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በአቅራብያዋ በሚገኘው ስደተኞች ወደ መጠለያነት በቀየሩት ጫካ ይበልጡን ስሟ ይነሳል ። ካሌ በርካታ ስደተኞች ወደ ብሪታንያ ለመሻገር አማራጭ አድርገው የሚወስዷት ስፍራ ከሆነች ዓመታት ተቆጥረዋል። የካሌው ጫካ ፣ ስደተኞች ከካሌ ወደ ብሪታኒያ በሚሄዱ የጭነት እና የቤት መኪናዎች ተሸሽገው ፣ በመርከቦች ወይም በባቡሮች ብሪታንያ የመግባት ሙከራ ለማድረግ አድፍጠው የሚጠባበቁት ስፍራ ነው ። በዚህ መንገድ ብሪታንያ መድረስ የቻሉ ቢኖሩም አንዳንዶች ደግሞ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ሆነው ቀርተዋል ። በሙከራ ወቅት በመኪና አደጋ የሞቱ  በፖሊስ ተይዘው የተመለሱ እና የተያዙም ጥቂት አይደሉም ። የካሌ ጫካ ይህን ሙከራ ለማድረግ የሚጠባበቁ ኢትዮጵያውያንን  ጨምሮ ቁጥራቸው 8 ሺህ የሚገመት ስደተኞች መኖሪያ ነበር ።  ከአሁን በኋላ ግን ጫካው የስደተኞች መጠለያነቱ በነበር የሚወሳ ወደ መሆን ተቃርቧል ። የፈረንሳይ መንግሥት ከዚህ ቀደም ባወጣው እቅድ መሠረት ፣ በጫካው ውስጥ የሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ድንኳኖችን  የክርታስ እና

የላስቲክ ደሳሳ ጎጆዎችን ዛሬ ማፍረስ ጀምሯል ።ከትናንት ጀምሮ  ስደተኞቹን እየመዘገበም 170 በሚደርሱ አውቶብሶች ወደ ሌሎች የፈረንሳይ ከተሞች እየወሰደ ነው ። ከመካከላቸው ለአካለ መጠን ካልደረሱት ስደተኞች የተወሰኑት ወደ ብሪታንያ እየተላኩ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ተለይተው እንዲቀመጡ ተደርጓል  ። ሀምዛ ከዛሬ አራት ወር አንስቶ ካሌ ጫካ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ነው ። ከ5 ከሚበልጡ ቢጤዎቹ ጋር ይኖርባት ከነበረው ደሳሳ መጠለያ  ከቀናት በፊት ወጥቶ አውላላ ሜዳ ላይ ሲያድር ቆይቶ አሁን ወደ ኮንቴይነር ተዛውሯል ። ርሱ እንዳለው ይህን እድልያገኘው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ወጣት ተብሎ በመመዝገቡ ነው ። ከዚህ በኋላ ግን ምን እንደሚጠብቀው አሁን በርግጠኝነት የሚያውቀው ነገር የለም ። ሀምዛ ጀንግል በሚለው ጫካ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም በርሱ አባባል አብዛኛዎቹ ፈረንሳይ ውስጥ መቆየት አይፈልጉም ። ካሌ ከፈረሰ ምርጫ ስለማይኖራቸው ሳይፈልጉ የተባሉትን እያደረጉ ነው ። ትናንት ወደ ተለያዩ የፈረንሳይ ጊዜያዊ  የስደተኞች ማዕከላት ከተወሰዱት ውስጥም ብዙ ኢትዮያውያን ይገኙበታል ። ሆኖም ይህን ያልፈለጉ እና ከአካባቢው የሸሹ ኢትዮጵያውያንም አሉ እንደ ሀምዛ  ። ከኢትዮጵያ ሱዳን ፣ ከሱዳን በበረሃ አቋርጦ ግብጽ ከደረሰ በኋላ ከ15 ቀናት አደገኛ የሜዴትራንያን ባህር ጉዞ ተርፎ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ነው ሀምዛ አውሮጳ የገባው ። ሀምዛ እንዳለው በተለይ በባህር ጉዞ ላይ ከ600 ሰዎች በላይ አሳፍራ የነበረችው የተጫነባት መርከብ የባህር ኃይል ድንበር ጠባቂዎች ደርሰው የኢጣልያዋ ሲሲሊ ከተማ ድረስ ባይወስዷቸው ኖሮ ኖሮ የባህር ሲሳይ ሆነው ሊቀሩ ይችሉ ነበር ። የሀምዛ ጉዞ ግን በኢጣልያ ብቻ አልተገታም ከገባበት የሲሲሊ መጠለያ ጣቢያ አምልጦ በተለያዩ የኢጣልያ ከተሞች አቆራርጦ ለፈረንሳይ ከሚቀርብ ከተማ በእግር ተጉዞ ነው ከ4 ወራት በፊት ፈረንሳይ የገባው ። ሌሎችም ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በተመሳሳይ አደገኛ ጉዞ

ነው የባሰ ስቃይ እና እንግልት ወደሚጠብቃቸው ወደ ካሌ የሚሄዱት ። በዶቼቬለ የአማርኛው ክፍል በልምምድ ላይ የሚገኘው ተስፋአለም ወልደየስ  በቅርቡ የካሌን ጫካ ጎብኝቶ የስደተኞች ኑሮ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ዘገቢ ፊልም ሰርቷል ። ተስፋለም ካሌ ከመሄዱ በፊት የነበረው ግምት ፣ከሄደ በኋላ ካየው ጋር ፍጹም የሚገናኝ አለመሆኑ አስደንግጦኛል ይላል ።  

ተስፋለም እንዳለው ወጣቶች የሚያመዝኑባቸው የካሌ ስደተኞች ምንም አይሰሩም ። ኢትዮጵያውያን ድንኳኖች እና ፕላስቲኮችን ተጠቅመው የሰሩት የጀንግሉ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለአንዳንዶቹ የመንፈስ እረፍት የሚያገኙበት ቦታ ነበር። በዚያ የሚገኙት የኦሮሞ ክምዩኒቲ አባላት ደግሞ የራሳቸው የቋንቋ ትምህርት ቤት ነበራቸው ። ተስፋለም ካነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን የካሌ ስደተኞች አብዛኛዎቹ ከሀገራቸው ተሰደድን ያሉበት ምክንያት ተመሳሳይ ነው ።

ጁልየት ላየንስ ካሌ የሚገኙ ስደተኞችን በሚረዳ «ኬር ፎር ካሌ»በተሰኘ ድርጅት አማካይነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስትሰጥ ቆይታለች ። የህግ ምክር አገልግሎት እንደምትሰጥ እና ህክምና የሚያስፈልጋቸው ካሉ እየተዘዋወረች የሚረዱበት ን መንገድ እንደምታመቻች ትናገራለች ። ላየንስ የፈረንሳይን መንግሥት የኃይል እርምጃ ከሚቃወሙት አንዷናት ። ካሌን መዝጋት ችግሩን አያስወግድም ትላለች

««ሁሉም ወደ አውቶብሶች ገብተው ወደ ተዘጋጁላቸው ቦታዎች ከተወሰዱ ችግሩ በሙሉ ይቃለላል ብለው ይገምታሉ ሆኖም አሁንም ወደካሌ ለመምጣት የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ መዘንጋrte የለባቸውም ። እነዚህንም እንዲሁ ወደ ሌላ ቦታ መውሰድ ይኖርባቸዋል ። ።ይህ ይሆናል ብለው ስለሚገምቱም አጭር መስራት ይጀምራሉ ። እናም የካሌውን ካምፕ ለመዝጋትም ሆነ አጥር ለመገንባት የደረሱበት ውሳኔ ርስ በርሱ የሚቃረን ነው ። ፍላጎቱ ካለ መንገድ አይጠፋም ። ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ መዘዋወር ከባድ አይደለም ።»

እንደ ጁልየት  ፈረንሳይ እና ብሪታንያ ብዙ ከማውራት ይልቅ ተባብረው ቢሰሩ መፍትሄው ሊገኝ ይችላል ። መፍትሄውም የአጭር ጊዜ ሳይሆን ዘላቂ ሊሆን ይገባል ። ከትናንት አንስቶ ከካሌው ጫካ ወደ 2700 የሚጠጉ ስደተኞች ወደተለያዩ የፈረንሳይ መጠለያዎች ተወስደዋል ። ጫካ ውስጥ የሚገኙት የስደተኞች መጠለያዎችም መፍረሳቸው ቀጥሏል ። ስደት የመጀመሪያው አይደለም የሚለው ሀምዛ ከካሌ በኋላ ምን እንደሚገጥመው አያውቅም ። ግን ከሀገሩ ያለበትን ቦታ ይመርጣል ። ሆኖም ሌሎች የርሱን ፈለግ እንዲከተሉ ግን አይመክርም።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic