የኪነጥበብ ለጤና አገልግሎት | ጤና እና አካባቢ | DW | 30.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የኪነጥበብ ለጤና አገልግሎት

በግጥም ምሽት የኪነጥበብ አድናቂዎችን ሲያዝናኑ ወራት አስቆጥረዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የካንሰር ታማሚ ህፃናትን መደገፍ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ስለበሽታዉ ያለዉን ግንዛቤ ለማስፋት እየጣሩ ነዉ።

ተሰጥኦ ችሎታቸዉን ለበጎ ተግባር ማነቃቂያ ሲያዉሉት የመጀመሪያቸዉ አይደለም። ከወራት በፊት «ጥበብ ለተፈጥሮ» በሚል መሪ ሃሳብ ባለፈዉ ዓመት የተተከሉ ችግኞች ክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸዉ ያሳሰበ የግጥም ምሽት አካሂደዋል። ትናንት ደግሞ የካንሰር ታማሚ ሕጻናትን ለመደገፍ ከሚንቀሳቀስ መንግስታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ጋ በመተባበር «እየተዝናኑ በካንሰር በሽታ የሚሰቃዩ ህፃናትን ይታደጉ» ሲሉ ግጥሞቻቸዉን በጃዝ ሙዚቃ አጅበዉ ለታዲሚዉ አቅርበዋል።

የካንሰር ታማሚ ሕጻናት በጥቁር አንበሳ ሃኪም ቤት ከሚሰጣቸዉ ህክምና በተጓዳኝ የሚያታዘዙላቸዉን መድሃኒቶች በመግዛት፤ ወደየመጡበት አካባቢ የሚመለሱበትን የመጓጓዣ ወጪ በመሸፈን ይረዳል። በመቀጠልም ታማሚዎቹ መድሃኒቱን ለመዉሰድ አቅማቸዉን ለማጠናከር እንዲችሉም ምግብ እንዲያገኙ ለማስቻል ያለመ እንቅስቃሴ በማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ማኅበረሰብ አማካኝነት ለማካሄድ መታለሙን ገጣሚ አበባዉ መላኩ ይገልጻል።

ለካንሰር ህሙማን ህጻናት መርጃ በተካሄደዉ የግጥም ምሽት ከተሳተፉት አንዷ ገጣሚ ምሥራቅ ተረፈ የግጥም ዝግጅቱን ለምግባረ ሠናይ ተግባር የማዋሉ ሃሳብ ከድርጅቱ መምጣቱን ገልጻልናለች። ዓላማዉን ገጣሚያኑ ስለደገፉትም ለመሳተፍ ወደኋላ እንዳላሉም አመልክታናለች። በእነሱ አስተዋጽኦ ስለበሽታዉ ሰዉ ምን ያህል ተረድቷል የሚለዉ የሚለካዉ ግን በሚያከናዉነዉ ተግባር ይሆናል ባይ ናት።

በዝግጅቱ ሶስት ገጣሚያን ተሳትፈዋል፤ አንድ ተዋናይ ማለትም ግሩም ዘነበ ደግሞ የሁለት ገጣሚያንን የግጥም ሥራዎች በማቅረብ ለዝግጅቱ ድምቀት እንደሰጠ ከገጣሚ አበባዉ ተረድተናል። አርቲስት ስለሺ ደምሴ በክራር ጨዋታዎቹ፤ ወጣት ኮሜዲያን አዝመራዉም እንዲሁ ለዝግጅቱ መሳካት የየበኩላቸዉን ተሳትፎ ማድረጋቸዉንም ገልጾልናል። በግብረ ሰናዩ ድርጅት የዝግጅቱ አስተባባሪ ዶክተር የትናየት አበበ ህጻናቱን ለመደገፍ ከሚሰባሰበዉ ገንዘብ በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ መድረክ የሰዎችን ግንዛቤ ያዳብራል ይላሉ።

የካንሰር ታማሚ ህጻናት ቁጥራቸዉ ይህ ብቻ አይደለም በአገሪቱ። እንዲያም ሆኖ ዶክተር የትናየት እንደሚሉትም በጥቁር አንበሳ ሃኪም ቤት ህክምናቸዉን የሚከታተሉ ከሃምሳ በላይ ታማሚዎች ይሆናሉ፤ ሆኖም አንዳንዶች ሳያጠናቅቁ ወደክፍለ ሀገር የሚመለሱበት ሁኔታም ያጋጥማል።

እነሱ ድጋፍ የሚያደርጉላቸዉ ቤተሰቦቻቸዉ አቅም የሌላቸዉ እንደመሆናቸዉ ህክምናዉን ጀምረዉ እንዳያቋርጡ የቤተሰቦቻቸዉ የኑሮ ሁኔታም እንዳይናጋ ቀደም ሲል ከገለጹት ተጨማሪ ህመምተኞቹን አዲስ አበባ ዉስጥ መጠለያ በመስጠት የሚያስተናግዱበትን ማዕከል የማቋቋም ዓላማ ሰንቀዋል።

በማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ማኅበረሰብ የሚረዱት ህፃናት ከ12 ዓመት እድሜ በታች ሲሆኑ በሙሉ ሃኪም ቤት የተኙ አይደሉምና ለህክምናዉ በየጊዜዉ ወደዋና ከተማዋ አዲስ አበባ መሄድ ይጠበቅባቸዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic