የኪስማዩ ውጊያ እና የሶማልያውያን አስተያየት | አፍሪቃ | DW | 01.10.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኪስማዩ ውጊያ እና የሶማልያውያን አስተያየት

አዲሱ የሶማሊያ መንግስትና የአፍሪቃ ህብረት ጥምር ጦር የአሸባብ የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታ የሆነችው ኪስማዩን ይዟል። የጥምር ኃይሉ ባሳለፍነው ዓርብ በዓየር፣ በባህርና በእግረኛ ጦር የአሸባብ ኃይሎች በወሰደው ጥቃት ከተማይቱ ከአሸባብ ቁጥጥር ስር ነጻ ብትወጣም፣

ምናልባት አሸባብ የበቀል ጥቃት ይወስዳል የሚል ፍራቻ አይሏል። በሌላም በኩል የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ከአስር ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያ የሆነውን ሶማሊያ ላይ ያተኮረ ዘገባ አውጥቷል።

አራት መቶ ሃምሳ የሚሆኑ የሶማሊያና የአፍሪካ ህብረት ጦር ዛሬ በኪስማዩ መሃል ከተማ መታየታቸውን ከወደ ሶማሊያ የሚመጡ ዘገባዎች አመልክተዋል። አሸባብ ምናልባት የኪስማዩን አሸዋ ክምር ስር ፈንጂ ቀብሮ ይሆናል በሚል ፍራቻ የጥምር ኃይሉ ከተማዋ ከመግባት ተቆጥቦ ነበር። አሸባብም ኪስማዩን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የኪስማዩ መንገዶች ወደ ጦር አውድማ እቀይራለሁ ሲል አስፈራርቷል። ነዋሪዎቿ በፍራቻ ምክንያት ከቤታቸው ስለማይወጡ የኪስማዩ መንገዶች ጭር ብለው ውለዋል።


የኪስማዩ ነዋሪዎች የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ኪስማዩ መግባት ላይ የተለያዩ አስተያየቶች አሏቸው። የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት የሶማሊያን ሉዓላዊነት አሳልፎ ይሰጣል ብሎ የሚያምኑ ሲኖሩ የውጭ ሀገር ጣልቃ ገብነት አሸባብ እያደረሰብን ካለው ችግር አይበልጥም የሚሉም አሉ።
ነዋሪነቱ በሶማሊያ ሞቃዲሾ የሆነው ጋዜጠኛ መሐመድ ቺኔ አብዛኛው የሶማሊያ ህዝብ የውጭ ሀገርን ጣልቃ ገቢነት በጥሩ ዓይን እንደሚያይ ይናገራል።

«የውጭ ሀገሮች የሶማሊያ ውስጥ መግባት በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አለው። ምክንያቱም አሸባብ እያደረሰ ካለው በደል ጋር ስታነጻጽር ህዝቡ በወታደሮቹ መምጣት ደስተኞች ናቸው። አሸባብን ከሶማሊያ ለማጥፋት ሁሉም የአፍሪቃ ሀገራት ወታደሮቻቸውን እንዲልኩ ይፈልጋሉ። አሸባቦች እያደረሱ ያሉት በደል በጣም ዘግናኝ ነው። ብዙ ሰዎችን አርደዋል፣ ብዙዎችንም አንገታቸውን ቀልተዋል። ምላስ እስከ መቁረጥ የደረሱ ዘግናኝ ስራዎችን ይፈጽሙ ነበር። ስለዚህ ሰዎች አሸባብ የያደረሰባቸውን ነገር እንዲወገድላቸው የአፍሪካ ሀገራትና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ወታደሮቻቸውን እንዲልኩ ይሻሉ።»


የአሸባብን ከኪስማዩ መውጣት ተከትሎ በተለያዩ ተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል የባህር ወደብ ከተማይቱን ለመቆጣጠር የሚፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ የጎሳን ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ፍራቻም ተፈጥሯል። የኪስማዩ ነዋሪዎች በጥብቁ የሻርያ ህግ ስር ይተዳደሩ ስለነበር ከወደቡ ከሚገኘው ጥቅም ተጠቃሚዎች አልሆኑም።ኪስማዩ እስካሁን ካሉት የአሸባብ ይዞታዎች ውስጥ የመጨረሻው ትልቅ ይዞታ ቢሆንም ከኪስማዩ ሸሽት መውጣቱ የአሸባብን የሽንፈት ዜና አያበስርም ተብሎ ይታመናል። ጋዜጠኛው መሐመድ ቺኔ አሸባብ ከሙሉ የጦር ኃይሉ ጋር ኪስማዩን መልቀቁ አሁንም አስጊ ነው ባይ ነው።

«እስካሁን ድረስ የሶማሊያም ሆነ የአፍሪቃ ህብረት ጦር ከአሸባብ የማረኩት የጦር መሳርያ የለም። አሸባቦች አሁንም ታንኮች፣ ከባድ የጦር መሳሪያዎች፣ ጸረ አውሮፕላን ሚሳዬሎችና ትናንሽ መሳሪያዎች አሏቸው። ስለዚህ ይህ በሶማሊያ የአሸባብ ፍጻሜ ነው ማለት አንችልም። ወደ ሌላ ሀገር ተንቀሳቅሰው የደፈጣ ጥቃት ሊያካህዱ ይጥሉ ይሆናል»

ከዚሁ ከሶማሊያ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በእንግሊዘኛው ምህጻሩ UNDP ከአስር ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያ በሆነው ሶማሊያ ላይ ባተኮረው ዘገባው፣ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑ የሶማሊያ ወጣቶች ከሶማሊያ መሸሽ እንደሚፈልጉ ዘግቧል። 70 በመቶ የሚሆኑ ህዝቦቿ ከሰላሳ ዓመት እድሜ በታች በሆኑበት በሶማሊያ ግጭት፣ ሙስናና ውጥንቅጡ የወጣ አስተዳደር ወጣቶች የስደት ኑሮን እንዲመኙ አድርጓቸዋል። ስራ አጥነትም ወጣቶች አሸባብ በዘረጋው መረብ ውስጥ እንዲገቡና የባህር ውንብድናን እንዲቀላቀሉ መንገድ ከፍቷል። ሶማሊያ ካለማችን አስከፊ የጾታ ጥቃትና መገለል ከሚታዩባቸው ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት።

ገመቹ በቀለ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic