የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ትምህርት የማስጀምር ውሳኔ | ኢትዮጵያ | DW | 23.09.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ትምህርት የማስጀምር ውሳኔ

ሰሞኑን 45 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮችን በማሳተፍ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጅማ ዩንቨርሲቲ ሲካሄድ የቆየው የሦስት ቀናት ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ተጠናቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:13

«ኮቪድ 19ን ከመከላከል ጋር ትምህርት እንዲጀመር መወሰኑ»

ሰሞኑን 45 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮችን በማሳተፍ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጅማ ዩንቨርሲቲ ሲካሄድ የቆየው የሦስት ቀናት ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ተጠናቋል። በውሳኔውም ለስድስት ወራት ተቋርጦ የቆየው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቅድመ ምረቃ ትምህርት ዳግም እንዲጀመር መወሰኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደቻሳ ጉርሙ ለዶይቼ ቨሌ ተናግረዋል። በዚህም ለመማር ማስተማር ሂደቱ ዝግጁነት ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች እስከ ተያዘው ወርሃ መስከረም መጨረሻ ዝግጁነታቸውን አጠናቀው ለተማሪዎች ጥሪ እንዲደረግ ውጥን ተይዟል። በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያና ምርመራ ማዕከላት ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ለትምህርቱ ፈጥኖ መጀመር እንደ ስጋት ተነስቷል። በመሆኑም በአማራጭ ጉዳይ ላይ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመምከር ለጊዜው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚገኙት 700 ሺህ ተማሪዎች ገደማ ቁጥራቸው ከ100 ሺህ የሚለቀውን ተመራቂዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ወደ ትምህርት ገበታው እንዲመለሱ ነው የተወሰነው። በቀጣይነትም ከኮሮና ወረርሽኝ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መልኩ ተለዋዋጭ እቅዶችን በመያዝ ቀሪዎቹ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ እንደሚሠራም ተገልጿል። በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ወጥነትን ሳይጠብቁ ቀድመው ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ ዩኒቨርሲቲዎች ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለተመራቂ ተማሪዎች ጥሪ በማድረግ ወደ መማር ማስተማር ሥራው እንዲገቡ ጉባኤው ወስኗል። ለተማሪዎች ጥሪ ከተደረገ በኋላ ከመጓጓዣ ሂደት ጀምሮ በየዩንቨርሲቲዎቹ በሚኖራቸው ቆይታ ወረርሽኙ እንዳይዛመት ከፍተኛ ዝግጅት መደረግ አለበትም ተብሏል። ከኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ባልተናነሰ አምና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ፈተና ሆኖ የከረመው የፀጥታ መደፍረስ እንዳያጋጥም ከአምና ልምድ መወሰዱን ጉባኤው የመከረበት ሲሆን፤ ጉዳዩ አሁን ለጊዜው ስጋት ባይሆንም መዘናጋት ሳይፈጠር ዩንቨርሲቲዎች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እንዲሠሩበት እቅድ መያዙ ተገልጿል። 
ስዩም ጌቱ 
ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች