የከፋ ዞን እና የአካባቢዉ የታሪክና ባህል ምሁር በጀርመን
ሐሙስ፣ ኅዳር 12 2017የከፋ ዞንን እና የአካባቢዉ የታሪክና ባህል ምሁር በጀርመን
« የኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ ሥነ-ዘዴ ትንሽ ችግር ያለበት ነዉ። የኢትዮጵያ ታሪኮች ተብሎ የተጻፈዉ፤ ከጥንት ጀምሮ እስከ አብዮቱ ድረስ፤ በተለይ ፖለቲካዊ ታሪኮች እና የነገሥታትን፤ የጀግንነት ታሪክ እና የጦርነት ታሪክ የሚያሳይ ብቻ ነዉ በአብዛኛዉ።»
ይህን የተናገሩት፤ በጀርመን ኤርፉርት ዩንቨርስቲ ጎታ ከተማ ከሚገኘዉ የባህል ጥናቶች ተቋም በቅርቡ በዶክትሬት ማዕረግ የሚመረቁት፤ ዘገየ ወልደማርያም አንቦ ነበሩ። ፤ ጀርመን ከመጣሁ ሦስተኛ ዓመቴን እያገባደድኩ ነኝ ያሉን ዘገየ ወልደማርያም አምቦ፤ ለዶክትሬት ማዕረግ በከፋ ብሎም በደቡብ ኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ባህል እና ታሪክ ጥናት ላይ ምርምራቸዉን የጀመሩት በመቀሌ ዩንቨርስቲ ነበር። ይሁንና በትግራይ በተቀሰቀሰዉ ጦርነት ምክንያት በመቀሌ ዩንቨርስቲ የጀመሩትን ትምህርታቸዉን መቀጠል ባለመቻላቸዉ፤ ወደ ጀርመን ኤርፉርት ዩንቨርስቲ ጎታ ከተማ በሚገኘዉ የባህል ጥናቶች ተቋም መዛወራቸዉን ነግረዉናል።
«ዘገየ ወልደማርያም አምቦ እባላለሁ። ጀርመን አገር ከመጣሁ ሦስተኛ ዓመቴን ልጨርስ ነዉ። ወደ ጀርመን የመጣሁትም በመቀሌ ጀምሪዉ የነበረዉን የ PHD ትምህርቴን ለመጨረስ ነዉ። እንደሚታወቀዉ ትምህርቴን የጀመርኩት መቀሌ ዩንቨርስቲ ነበረ፤ ይህ ከጦርነቱ በፊት ማለት ነዉ። ጦርነቱ ሲቀሰቀስ፤ የጀመርኩት የትምህርት ፕሮግራም ከጀርመን ተቋም ጋር የተጣመረ ስለነበር፤ አማካሪዬም ጀርመናዊ ፕሮፌሰር ስለነበረ፤ እዚህ አመቻቸ እና ጀርመን አገር ትምህርቴን ተምሪ ለመጨረስ መጣሁ። በአሁን ሰአት በኤርፉርት ዩንቨርስቲ ስር በሚገኘዉ እና ጎታ በምትባል ከተማ ዉስጥ ባለዉ የባህል ጥናቶች ማዕከል ትምህርቴን እየተከታተልኩ ነዉ። የ PHD መመረቅያዩን በከፋ ታሪክ ላይ፤ ጽፊ ወደማጠናቀቅ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ።»
ከፋ በተለያዩ ሥርዓቶች የተለያዩ መጠርያዎች እንደነበርዋት የነገሩርን አቶ ዘገየ ወልደማርያም አምቦ ፤ ከፋ በአሁኑ ወቅት ስድስት ዞኖችን ይዞ በተዋቀረዉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዉስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ቦንጋ ከተማ የአዲሱ ክልል የፖለቲካ የአስተዳደር ማዕከል እና ታሪካዊ ከተማም እንደሆነ ነዉ የገለፁት።
«ቦንጋ ከተማ ታሪካዊ ከተማ ነዉ። ቀደም ብሎ የከፋ ስርወ-መንግሥት በነበረበት ወቅትም፤ ታሪካዊ የነበረ ከተማ ነዉ። በአሁኑ ወቅት በኤርፉርት ዩንቨርስቲ ስር በሚገኘዉ የባህል ጥናቶች ተቋም ስለከፋ ዞን ታሪክ ባህል እና የማኅበረሰብ አኗኗር ጉዳዮች በማጥናት ላይ የሚገኙት ዘገየ ወልደማርያም አምቦ፤ ዉርሰ ኢትዮጵያ የተባለዉ በጀርመን የተቋቋመዉ ድርጅት ኤርፉርት ጎታ ከተማ ላይ በተዘጋጀዉ የኢትዮጵያ ጥናት አባት ተብለዉ የሚጠሩት የጀርመናዊዉ ሊቅ የሂዮብ ሉዶልፍ 400 ኛ ዓመት መታሰብያ ዝግጅት ላይ ስለ ከፋ እና ስለደቡብ ኢትዮጵያ ታሪክ ጥናታቸዉን በከፊል አቅርበዋል። አቶ ዘገየ ወልደማርያም አምቦ፤ እንደሚሉት እስካሁን እያየነዉ ያለዉ የኢትዮጵያ የታሪክ አፃጻፍ፤ ፖለቲካዊ፤ ብዝሃ ማኅበረሰብን ያላገናዘበ ፤ አብዛኛዉ የጦርነት ታሪክ ነዉ ሲሉ ገልፀዉታል።
የኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ ሥነ-ዘዴ ትንሽ ችግር ያለበት ነዉ። የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የሚገኘዉ ጽሑፍ ከጥንት ጀምሮ እስከ አብዮቱ ድረስ፤ በተለይ የነገሥታትን የፖለቲካ፤ የጀግንነት እና የጦርነት ታሪክን ነዉ በብዛት የምናገኘዉ። አብዛኛዉን የኢትዮጵያ ብዘሃ ማኅበረሰብ፤ ብዘሃ ታሪክ እና ብዘሃ ባህል፤ ግንዛቤ ዉስጥ ያስገባ የአጻጻፍ ዘዴ አይደለም። የኢትዮጵያ ታሪክ ፖለቲካዊ እና የተሰነደ ምንጭን እንደ ታሪክ አጻጻፍ ዋና ማዕከል አድርጎ የሚያሳይ ነዉ። በአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ በቀረበ ሰነድ ላይ የተጠቀሙት የነገስታትን ዜና መዋል፤ ገድላት፤ እና በእጅ የተጻፉ ነገሮችን በዋናነት፤ ትኩረት ያደረገ ነዉ። የነገሥታት ዜና መዋል ጸሐፊዎች ጥለዉ ያለፉት መረጃ ላይ ትኩረት ያደረገ ነዉ። ኢትዮጵያ ብዘሃ አገር ነች። ብዘሃ ባህል፤ ብዘሃ ታሪክ ያለባት፤ አገር ነች። እነዛ ታሪኮች በተለያየ መንገድ የቆዩም ናቸዉ። አብዛኞቹ በአፈ-ታሪክ፤ በባህላዊ ቁሳቁሶች እና በመሳሰሉት ላይ ታሪኮች ይገኛሉ።»
አቶ ዘገየ ወልደማርያም አምቦ፤ ጥናት በአቀረቡበት መድረክ ስለ ከፋ ሥርወ-መንግሥት የተለያዩ ታሪኮች፤ በከፋ የክርስትና አመጣጥ ታሪክን አቅርበዋል። ዘገየ ወልደማርያም አምቦ ፤በቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባህል መምህር ሆነዉ አገልግለዋል። ከዝያም የዶክትሬት ትምህርታቸዉን በመቀሌ ዩንቨርስቲ ለአንድ ዓመት ተከታትለዉ፤ በትግራይ ጦርነት ምክንያት ወደ ጀርመን ተዛዉረዉ በኤርፉርት ዩንቨርስቲ ጎታ የባህል ጥናቶች ተቋም ትምህርታቸዉን ቀጥለዋል። አቶ ዘገየ እንደነገሩን ከፋ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበዉ ፤ የዱር ወይም ወፍ ዘራሹ እና ኮፊ አረቢካ የሚባለዉ ቡና ከፍተኛ አምራች አካባቢም ነዉ።
ከአንድ ወር ገደማ በኋላ የዶክትሬት ማዕረጋቸዉን ከጀርመን ኤርፉርት ዩንቨርስቲ የሚቀበሉት አቶ ዘገየ ወልደማርያም አምቦ ፤ ለሰጡን ቃለ-ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉዉን ቅንብር እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ