የከሸፈዉ መፈንቅለ መንግሥትና የቡሩንዲ መመሰቃቀል | አፍሪቃ | DW | 15.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የከሸፈዉ መፈንቅለ መንግሥትና የቡሩንዲ መመሰቃቀል

የቡሩንዲ ጦር ሠራዊት፤ የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት ያወጁትን ሜጀር ጀኔራል ጎድፍሯ ኒዮምባሬ ን ዛሬ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ሲገልጽ ፤ ለምክክር ካገር ውጭ የነበሩት ፕሬዚዳንት ፒየር እንኩሩንዚዛ ም ፤ ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውን ቃል አቀባያቸው ፤

ይፋ አድርገዋል። ሜጀር ጀኔራል ኒዮምባሬ የተያዙት ፣ በቡሩንዲ መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱን በአንድ የግል ራዲዮ ጣቢያ ባወጁ በሁለተኛው ቀን ነው። ቡሩንዲ ፤ በጎሣ በመከፋፈል በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉበት አሠቃቂ ውዝግብ ከተገላገለች 10 ዓመት ገደማ ቢሆንም፤ ለ 3ኛ ጊዜ ለምርጫ እጩ ሆኔ ካልቀረብሁ ብለው በጉልበት የተነሣሱት ፕሬዚዳንት እንኩሩንዚዛ ፤ አገሪቱን ዳግመኛ ወደ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይገፏት አሥግቷል።ፕሬዚዳንት ፒየር እንኩሩንዚዛ፤ ሕገ መንግሥቱን በመጋፋት፤ ለ 3ኛ ጊዜ እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የሙጥኝ ማለታቸው፤ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ ከ 10 ዓመት በፊት ብዙኀኑ ሁቱዎች፤ የደፈጣ ተዋጊ ኃይል አቋቁመው የሃዳጣኑን ቱትሲዎች መንግሥት እንደወጉት ሁሉ ዛሬም ያ ዓይነቱ ግጭት እንዳይከሠት ሥጋት አለ። የቡሩንዲ ጦር ሠራዊት በአሁኑ ጊዜ የተሠባጠረ ቢሆንም የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ፤ ክፍፍል መኖሩን ሳይጠቁም አልቀረም። እንኩሩንዚዛ ፣ ሰኔ 19 ቀን 2007 በሚካሄደው የፕሬዚዳንትና ፓርላማ ምርጫ ራሳቸው እጩ ፕሬዚዳንት አድርገው ለማቅረብ መነሣሣታቸውን ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎችም ርዳታ ለጋሽ ምዕራባውያን መንግሥታት አልደገፉላቸውም ። አንዳንድ የአፍሪቃ አገሮች፤ የአፍሪቃ ሕብረት ጭምር ነቀፌታ ሠንዝረዋል።

በ« በሁከት ሥልጣን ለመያዝ መሞከርም የሚወገዝ ተግባር ነው» ብሏል የአፍሪቃ ሕብረት ።

የውጫ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከሆነም፤ እስካሁን ከፍተኛውን የሥልጣን ዕርፍ ለመጨበጥ ትንንቅ ያለ ቢመስልም፤ ውዝግቡ ከቀጠለ፤ የቀድሞው የጎሣ ቁርሾም ሆነ ቁስል እንዳያመረቅዝ ያሠጋል። ውጥረቱ አለመርገቡም ይህን ሥጋት ከፍ ያደርገዋል። ለዴሞክራሲ፤ ፍትሕና ርትእ ከሚታገሉ 300 ያህል የሲቭል ማሕበረሰባዊ ቡድኖች መካከል፤ «ፎኮድ» የተሰኘው ማሕበር መሪ ጎርዲየን ንዩንጌኮ ግን ፤ ንቅናቄው፣ ተሞከረ ከተባለው መፈንቅለ መንግሥት ጋር አንዳች ግንኙነት እንደሌለውና ተቃውሞውን ወደፊት ከመግፋት እንደማይቦዝን ነው ያስረዱት።

የቡሩንዲውን ወቅታዊ ውዝግብ የቀሰቀሱት ፤ ለ 3ኛ የሥልጣን ዘመን በእጩነት እወዳደራለሁ ብለው የተነሣሱት የፕሬዚዳንት እንኩሩንዚዛ፣ ትናንት ከታንዛንያ ወደ ትውልድ ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላ፣ ከገጠር መኖሪያ ቤታቸው ተነስተው ዛሬ ቡዙምቡራ ቤተ መንግሥት መግባታቸው ተነግሯል። ቃል አቀባያቸው ፤ ጌርቬስ አባየሆ እንደገለጹት፤ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል ብለው አውጅወ የነበሩት ሜጀር ጀኔራል ጎድፍሯ ኒዮምባሬ፤ ተያዙ እንጂ እጅ አልሰጡም ።

3 ሌሎች ጀኔራሎችም ተይዘው መታሠራቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ከ 105 ሺ የሚበልጥ ሕዝብ በመኮብለል ድንበር ተሻግረው ጎረቤት አገሮች ሩዋንዳ ጭምር ገብተዋል። ሩዋንዳ በ 1986 በእርስ-በርስ ጦርነት 800 ሺ ቱትሲዎችና ለዘብ ያለ አቋም የነበራቸው ሁቱዎች የተገደሉባት ሀገር መሆኗ የታወቀ ነው።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic