የከሰል ጡብ ስራ በኬምስትሪ ተመራቂዎች | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 05.09.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የከሰል ጡብ ስራ በኬምስትሪ ተመራቂዎች

በሳይንሱ ዘርፍ የከፍተኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለመመረቂያ የሚያዘጋጇቸው ጥናታዊ ጽሁፎቻቸው መደርደሪያ ከማሞቅ የዘለለ ጥቅም አይሰጡም የሚል ትችት በተደጋጋሚ ሲቀርብ ይደመጣል። የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ አምስት ተማሪዎች የጥናታቸውን ውጤት ወደ ተግባር ለውጠው ጭስ አልባ ከሰል እያመረቱ ይገኛሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:21
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:21 ደቂቃ

የመመረቂያ ጥናታቸውን ወደ ተግባር የለወጡ እንስቶች

ወጣት ናቸው፤ ሃያ አምስት ዓመት እንኳ ያልሞላቸው። ከትግራይ፣ ከጎንደር፤ ከሰሜን ሸዋ እና ከአዳማ የተሰባሰቡ አምስት እንስቶች። ያገናኛቸው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ፣ የተማሩት ደግሞ ኬምስትሪ ነው። ከተመረቁ ሁለት ዓመት ቢሞላቸውም አሁንም ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ቅጽር ግቢ አይጠፉም። በዚያ የቆዩት ለተጨማሪ ትምህርት አሊያም ለማስተማር አይደለም፤ የተማሩትን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንጂ።

እንስቶቹ የመመረቂያ የጥናት ጽሁፋቸውን ለማዘጋጀት ሲነሱ ከብዙ ኢትዮጵያውያን ጓዳ የማይጠፋውን ከሰልን መረጡ። በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያስከትለውን የተለምዶ የከሰል አመራረት በትምህርታቸው በቀሰሙት የተለየ አካሄድ ተክተው አተገባበሩን ለማጥናት ወሰኑ። ጥናቱን ለማድረግ የተስማሙት አስር ተማሪዎች ለሁለት ተከፍለው ተቧደኑ። ጥናቱን ካደረጉት ተማሪዎች አንዷ የነበረችው ይብራለም ሰላማዊ አካሄዱን መለስ ብላ ታስታውሳለች።

“አንደኛው ቡድን ጥሬ ዕቃ አለ ወይስ የለም? በሚለው ላይ ዳሰሳ ነበር የሚሰራው። የአካባቢ ግምገማ ማለት ነው። አንደኛው ቡድን ደግሞ በዳሰሳ የተገኘውን ጥሬ ዕቃ በቤተ ሙከራ የሚያረጋግጥ ነበር። መጨረሻ ላይ የመመረቂያ ጽሁፋችንን ስናቀርብ እኛ ክፍል ብዙ አጥኚዎች ነበሩ የተመደቡልን እና ይህን ስራ ለሀገሪቱ ይጠቅማልና በብዛት ቢሰራ ተባለ። ወደ ዩኒቨርስቲው አስተዳደር፣ ወደ ፕሬዝዳንቱ ቢሮ መቅረብ አለበት ተብሎ እንደገና ሁለተኛ ስናቀርብ ‘ይሄን ነገር መስራት አለባችሁ። መነሻ ካፒታል ተሰጥቶ፣ ወደ መሬት ወርዶ፣ በስፋት መሰራት አለበት’ ተብሎ በስፋት እንድንሰራ አደረገን” ትላለች።

ዩኒቨርስቲው ቃል እንደገባው ከምርቃት በኋላ ለአምስቱ እንስት ተማሪዎች ድጋፍ እንዳደረገላቸው ይብራለም ትገልጻለች። ተመራቂዎቹ ጥናታቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ ተቋሙ ገንዘብ በመስጠት፣ የመኖሪያ እና የምግብ አገልግሎት በዩኒቨርስቲው እንዲያገኙ በማድረግ አግዟቸዋል። እነ ይብራለም ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ያገኙትን 17 ሺህ ብር መነሻ ይዘው የምርት ሙከራ ምርምር እና የአዋጭነት ጥናት ለአንድ ዓመት ሲያካሄዱ ቆይተዋል። 

“በ2009 ዓ. ም. ምርምር ላይ ነው የቆየነው። እንሰራለን፣ ዝም ብለን ለሰው በነጻ እንሰጣለን፣ አስተያየት እንቀበላለን፣ ያንን እያደረግን ነበር የቆየነው። ከዚያ በኋላ ሚያዝያ 2009 ዓ. ም. አካባቢ ወደ ትክክለኛ ምርት ገባን። በአዲስ አበባ በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ቤተሙከራ ተፈትሾ ጥራቱን እና የተለያዩ መስፈርቶች ተለክቶ በጣም አዋጭ ስለሆነ በብዛት እንድንሰራ ተደረገ ማለት ነው” ትላለች ስለአጀማመራቸው ስታስረዳ።  

እነ ይብራለም ማምረት የጀመሩት ጭስ አልባ የከሰል ጡብ የተለያዩ ተረፈ ምርቶችን እና ደረቅ ቆሻሻዎችን በመደባለቅ የሚሰራ ነው። ለከሰል ጡቡ በግብዓትነት ከሚያገለግሉት ውስጥ የእንጨት ፍቅፋቂ (ሰጋቱራ)፣ የወዳደቁ ቅጠላ ቅጠሎች፣ የቡና አተላ፣ ሳር፣ የሙዝ ልጣጭ እና ወረቀት ይገኙበታል። የከሰል ጡቡ የአመራረት ሂደት ምን እንደሚመስል ይብራለም እንዲህ ታብራራለች።

“መጀመሪያ ጥሬ ዕቃ እንሰበስባለን። ማንኛውም አይደባለቅም፤ ለየብቻው ነው የሚሰራው። አሁን ለምሳሌ ከባህር ዛፍ  ስንሰራው መጀመሪያ ባህር ዛፉ በደንብ ይደርቃል። ጸሀይ ማግኘት አለበት። ከዚያ በኋላ carbonizer የሚባል የሚያቃጥል ማሽን አለ። ከዚያ ወደ ማቀጣጠያ እናስገባዋለን። ጠቅላላ አመድ እንዳይሆን፣ እንደገና ደግሞ ጥሬ እንዳይኖረው፣ የኦክሲጅን መጠንን በመለካት ከስርም፣ ከላይም እንደፍነዋለን። ከዚያ በኋላ ትንሽ ቆይተን ቀዝቀዝ ሲል እናወጣዋለን ማለት ነው። ጥሬም አይሆንም፤ አመድም አይሆንም። እርሱን ካወጣነው በኋላ መፍጫ ማሽን አለ በእርሱ እንፈጨዋለን። ከፈጨነው በኋላ እንደነወረቀት አይነት የተለያዩ ማጣበቂያዎች አሉ። እንዲጣበቅልን [እነርሱን] እንጠቀማለን። ከዚያ በኋላ ከውሃ ጋር እንደባልቀዋለን። ገንዳ አለ፤ በማኑዋል ማሽን press አድርገን እናወጣዋለን ማለት ነው” ስትል ሂደቱን ትተነትናለች።

እነ ይብራለም እንዲህ ያመረቱትን ክብ የከሰል ጡብ አነስተኛ በሚባል ዋጋ ለተጠቃሚዎች ያቀርባሉ። ክብ ቅርጽ ያላቸው እና በውስጣቸው አየር እንደልብ እንዲተላለፍ ቀዳዳዎች የተበጁላቸው ጡቦች በሁለት ዓይነት መጠን ተዘጋጅተዋል። ስድስት ብር የሚሸጠው አነስ ያለው የከሰል ጡብ እስከ አራት ሰዓት እየተቀጣጠለ መቆየት ይችላል። ከፍ ያለ መጠን ያለው እና ስምንት ብር የሚያወጣው የከሰል ጡብ ደግሞ እስከ አምስት ሰዓት ትርክክ እንዳለ ይቆያል። አራቱን የከሰል ጡብ የገዛ ቀኑን ሙሉ ስራውን ያለ ችግር ማከናወን ቻለ ማለት ነው።

የከሰል ምርቱ በዋጋ ርካሽ፣ ለሰዓታት አገልግሎት መስጠት የሚችል ቢሆንም በርካታ ተጠቃሚዎች ግን ማግኘት አልቻለም። አምስቱ የኬሚስትሪ ተመራቂዎች በመጀመሪያ ምርታቸውን በብዛት ለማስረከብ ተስማምተው የነበረው በአዲስ አበባ ለሚገኝ የስደተኞች መጠለያ እንደነበር ይብራለም ትናገራለች። የጣቢያው ሰዎች ሀሳባቸውን በመቀየራቸው ግን ያቀዱት እንዳልተሳካ ትገልጻለች። በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ውስጥ ካለው ማምረቻቸው እየመጡ የሚገዙ ግለሰቦችም አነስተኛ እንደሆኑ ታስረዳለች።

“ያው ብዙ የገበያ ትስስር አላገኘንም። የማስተዋወቅ ስራ በእኛ አቅም [አልቻልንም]። አላስተዋወቅንም ማለት ይቻላል። አሁን ለምሳሌ እዚህ ደብረ ብርሃን ብዙ ተጠቃሚ የለም ማለት ይቻላል። አብዛኛው ቤት ቁጭ የሚል የለም፤ ያለማቋረጥ የሚጠቀምም የለም። አንዳንዴ ለቅዳሜና እሁድ እና ለበዓል ብቻ ነው የሚገዙት” ትላለች ይብራለም።

አረቄ በብዛት በሚወጣባት ደብረ ብርሃን ከተማ ለሰዓታት ያለማቋረጥ መቀጣጠል የሚችል አንድ የኃይል ምንጭ እምብዛም ተቀባይነት አለማግኘት እንግዳ ነገር ይመስላል። የደብረ ብርሃን ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ጥበበ ጣፌ ላለፉት 25 ዓመታት አረቄ ሲያወጡ ቆይተዋል። መጠጡ ለመስራት የሚውሉ ግብዓቶችን ለማዘጋጀትም ይሁን ራሱን አረቄውን ለማውጣት ማገዶ ይጠቀማሉ። ወ/ሮ ጥበበ የአረቄ አወጣጡን ሂደት እንዲህ ያስረዳሉ።

“መጋገሪያው በፍግ እና በኩበት ነው የሚጋገረው። ለማንጠሪያው፣ ለሚነደው፣ ለአረቄው ማንቆርቆሪያ በኩበት እና በእንጨት ነው የምንጠቀመው። እንስራው ይጣድና ያው ኮዳ እና መሳቢያ የሚባል አለ። እርሱ ላይ ቀስ እያለ እየነደደ ይንጠባጠባል።  ከዚያ ጀሪካን ውስጥ ይጨመርና ጀሪካኑ ሲሞላ ያው አረቄው ይሸጣል። እና ማጣራት የሚባለው እንደዚያ ነው። አተላ ለብቻ ይቀራል። ጠረቄው ውስጡ ይንቆረቆራል። ወርዶ አረቄ እስከሚሆን፣ አንድ ጠርሙስ ከግማሽ እስኪሞላ ከሁለት ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ተኩል ይፈጃል” ይላሉ የደብረ ብርሃኗ ነዋሪ።

ወ/ሮ ጥበበ አረቄ ለማውጣት የሚገለገሉበትን ኩበት የሚያዘጋጁት ራሳቸው ናቸው። ከሁለት ላሞቻቸው የሚያገኙትን አዛባ ወደ ኩበት ለመቀየር ቢያንስ 15 ቀናት ይወስድባቸዋል። ለአንድ በርሜል አረቄ ማውጫ የሚውለው እንጨት ደግሞ 100 ብር ያስወጣቸዋል። በሳምንት ከሁለት እስከ ሶስቴ አረቄ የሚያወጡት ወ/ሮ ጥበበ የማገዶ ፍጆታቸውን የሚቆጥብላቸው አማራጭ የኃይል ምንጭ ቢያገኙ እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ። አረቄ ለማውጣት ከሰልን የመጠቀም ሀሳብ ሲነሳባቸው ግን “የሚሆነው በእንጨት እና በኩበት ብቻ ነው። ከሰልን እኛ የምንጠቀመው ለወጥ መስሪያ፣ ለቡና ማፍያ፣ ለተለያዩ   ማንዳጃ ላይ ለማድረግ ነው እንጂ ለቀረቄ ከሰል አይሰራም። እንዲህ አድርገህ ብታነደው አይሰራም። ማንደጃ ላይ ሆኖ አየር በሚያገኝበት ቦታ ላይ ነው የሚሰራው። አያሰማውም” ሲሉ ቁርጥ ያለ ምላሽ ይሰጣሉ።

የእነ ይብራለም የከሰል ጡብን ተጠቅመው ቡና ለማፍላትም ሆነ ወጥ ለመስራት የሚፈልጉ ነዋሪዎች ስራቸውን ሲጨርሱ እሳቱን አጥፍተው ድጋሚ መጠቀም አለመቻላቸውን በችግርነት ያነሳሉ። የከሰል ጡቡን በመጀመሪያ ያመርቱ የነበረው በአነስተኛ የማሽን እርዳታ፣ በራሳቸው ጉልበት መሆኑ የችግሩ ምንጭ እንደሆነ ይብራለም ትናገራለች። አሁን ግን ከቻይና የመጣ ዘመናዊ ማሽን መጠቀም በመጀመራቸው የሚያመርቱት የከሰል ጡብ እንደ ተለምዶአዊው ሁሉ ፈረካክሶ በልክ መጠቀም ይቻላል ትላለች።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ባገኙት 500 ሺህ ብር ብድር እንዲህ አቅማቸውን ለማደርጀት የሞከሩት አምስቱ የኬምስትሪ ተመራቂዎች የከሰል ማምረቻቸውንም በይፋ አስመዝግበዋል። ድርጅታቸውን እፎይታ በለጤ እና ጓደኞቻቸው የተለያዩ የኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ውጤቶች መፈብረክ የሽርክና ማህበር ብለውታል። እፎይታ እና በለጤ ከአምስቱ የድርጅቱ መስራቾች የሁለቱ ስም ነው። ድርጅታቸው ከከሰል ሌላ በተጓዳኝ የሚያመርተው የኃይል ቆጣቢ ምዳጅንም “እፎይታ” ሲሉ ሰይመውታል። ስለ ኃይል ቆጣቢ ምርቶች ስልጠና በወሰዱ ጊዜ የቀሰሙትን ዕውቀት ተጠቅመው ምጣድ ማምረትም ጀምረዋል። 

አምስቱ እንስቶች ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ ቢደርሱም ገና በመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ውጤታቸው ደካማ በመሆኑ በትርፍ ጊዜ የሚያግዟቸው መምህር ተመድቦላቸው ነበር። ውጤታቸውን ማሻሻል ሲጀምሩ እገዛቸውን ያቆሙት መምህር በመመረቂያ ጽሁፋቸው ዝግጅት ላይ በድጋሚ አሻራቸውን አሳርፈዋል። አቶ ዩሴፍ ሽፈራው የሚባሉት የእኚህ መምህር ጥረት እና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ እርዳታ ባይተከልበት ኖሮ “ተስፋ ቆርጠን እንቀር ነበር” ትላለች ይብራለም። ያለፉበትን ውጣ ውረድ  ደግሞ እንዲህ ታስረዳለች።  

“ይህንን እንድንጀምር ያደረገን መጀመሪያ አንድነት ነበረን። ያው ተመርጠን ስናልፍ ሁሉም ጠንካራ ነው የነበረው። ሁሉም ያነባል እንደገና ደግሞ አብኛው ግለሰብ ፍላጎቱ ወደ መንግስት ስራ ሳይሆን የራሴ የሆነ ኢንቨስትመንት፣ ድርጅት  ቢኖረኝ የሚል ነበር። ከእኛ በላይ ደግሞ መምህሩ ‘በስነ ስርዓት ሰርታችሁ ወደ ተግባር የሚለወጥ ፕሮጀክት መቅረጽ አለባችሁ’ በሚል ሀሳብ እርሱ ነበር በበላይነት ምክር የሚሰጠን። መምህሩ ቦታ ባይሰጠን እና ቦታ ባያመቻችልን ኖሮ እኛ ተስፋ እንቆርጥ ነበር በተለያየ ምክንያት። አንድ ዓመት [ገደማ] ያለምንም ክፍያ፣ ያለ ምንም ደሞዝ፣ መቶ ብር እንኳ ሳይኖረን ኖረናል፤ ካፌ ልክ እንደተማሪ እየበላን ማለት ነው። እና ዋናው መሰረቱ መምህሩም ነው፤ ቀጥሎ ዩኒቨርስቲውም ነው። 

በተለያየ ምክንያት የተለያየ ጫና ነበረ ግን እኛ አምስታችን ላይ ፍቅርም አለ፣ ያው አንደባበቅም፣ እንረዳዳለን፣ እንተጋገዛለን፣ በስራም አንለያየም። ብዙ የጉልበት ስራም ነበረው እርሱን ስንሰራ ነበርና በጣም ብዙ ተግዳሮቶች አለ። ‘እችላለሁኝ’ ካልክ ደግሞ የማይሰራ ነገር የለም። የማይቻል ነገር የለም ማለት ነው። እና ብዙ ተግዳሮት ነበር፤ አሁን አልፈነዋል። ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ የሆነ ፈተና ሲያጋጥመንም ያንን ለማለፍ በተለያየ አቅጣጫ አስበን ማለፍ እንችላለን የሚል አቋም ነው ያለን” ስትል በልበ ሙሉነት ታጋራለች። 

 
ተስፋለም ወልደየስ 

አዜብ ታደሰ 

Audios and videos on the topic