የኧል በሽር ዉዝግብ የጋረደዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ | አፍሪቃ | DW | 15.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኧል በሽር ዉዝግብ የጋረደዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ

25 ኛዉ የአፍሪቃ ሕብረት መንግሥታ የመሪዎች ጉባዔ ከትናንት ጀምሮ በደቡብ አፍሪቃ ጆሃንስበርግ ተካሄደ። በ« አይ ሲ ሲ» የሚፈለጉት የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኧል በሽር ከደቡብ አፍሪቃ እንዳይወጡ አንድ ደቡብ አፍሪቃ ፍርድ ቤት ቢወስንም፤ ኧል በሽር ዛሬ ከቀትር በፊት ሃገሪቱን ጥለዉ ካርቱም ገብተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:15

የኧል በሽር ዉዝግብ የጋረደዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ

የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በደቡብ አፍሪቃ ጆሃንስበርግ ላይ የተካሄደዉን የሁለት ቀን ጉባኤ በይፋ የከፈቱት በአፍሪቃ ጦርነት መቆም አለበት የሚል ጥሪን በማሰማት ነበር። ጆሃንስበርግ ላይ ለሁለት ቀናት የተሰየመዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጉባዔ ግን ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት፣ «አይ ሲ ሲ » የእስር ማዘዣ ያስተላለፈባቸው እና በጉባዔው የተካፈሉት የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦመር ኧል በሽር ሀገር ለቀው እንዲወጡ አንድ ባሳለፈው ውሳኔ የተነሳ ተጋርዶ ነዉ የዋለዉ።


የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት «አይ ሲ ሲ » ለእስር የሚፈልጋቸዉ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦመር ኧል በሽር ትናንት ደቡብ አፍሪቃ ጆሃንስበርግ ላይ በጀመረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ ለመሳተፍ ቅዳሜ እለት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ማቅናታቸዉ ጉባኤዉ በኧል በሽርና በ«አይ ሲ ሲ » ዉዝግብ እንዲጋረድ ዳርጎአል። ትናንት እሁድ አንድ የደቡብ አፍሪቃ ፍርድ ቤት የሲዳኑ ፕሬዚዳንት ኧል በሽር ደቡብ አፍሪቃን ጥለዉ መዉጣት አይችሉም ሲል ወሰኔን ቢያስተላልፍም፤ የሱዳን የብዙኃን መገናኛዎች ኧል በሽርን የያዘዉ አዉሮፕላን ከፕሪቶርያ መነሳቱን ከቀጥር በፊት ቀደም ብለዉ ነበር ይፋ ያደረጉት። እንደ አብዛኞች እምነት ደቡብ አፍሪቃም ሮም ላይ የተረቀቀዉን ሕግ በፊርማ ያፀደቀች ሃገር በመሆዋ ኧል በሽርን ይዛ ለዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ተመልካች ፍርድ ቤት ማስረከብ አለባት አለባት የሚል ነበር። ደቡብ አፍሪቃ የአፍሪቃ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዴቪድ ሆለ እንደሚሉት፣ ግን ደቡብ አፍሪቃ በአፍሪቃ ሕብረት ተስማምታ የፈረመችዉ ረቂቅ ፕሬዚዳንቶች ተይዘዉ እንዳይሰጡ የሚከላከል መድሕንን የሚሰጥ አንቀፅ አለ።
« ደቡብ አፍሪቃ የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሃገራት ከ«አይ ሲ ሲ »ጋር እንዳይተባበሩ በሚያዘው ውሳኔ ላይ ድምፅ በተሰጠበት ጊዜ ነበረች፣ ውሳኔውንም በድምፅዋ አጽድቃለች። በዚህም ምክንያት የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት በመጀመርያ ደረጃ እንደ እንደ ሕጋዊ የሕብረቱ አባል ሃገር ውሳኔውን የማክበር ግዴታ አለበት። »

በጉባኤዉ መክፈቻ የወቅቱ የአፍሪቃ ሕብረት መሪና የዚምባቢዉ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤ በአፍሪቃ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ሃገራት ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አስምተዋል። ሙጋቤ ያለ ሰላም የአፍሪቃ የኤኮኖሚ አጀንዳ ስኬታማነት አይኖረዉም ሲሉም ተናግረዋል።


« በአንዳንድ የአህጉራችን ክፍሎች የሚታየዉ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ፀጥታ መጓደል፣ የአፍሪቃ ሕብረት የተጠንቀቅ ጦር ርምጃ መውሰድ የሚችልበትን ሁኔታ ባስቸኳይ ማመቻቸት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን አጉልቷል። ይህ ደግሞ እስከ ጎርጎረሳያዊዉ 2020 ዓ,ም ድረስ በአህጉሩ ማንኛዉም ጦርነት ለመግታት የያዝነዉን እቅዳችንን ከግብ በማድረሱ ጥረት ላይ ዋነኛ ርምጃ ነዉ።»
ሙጋቤ ሴቶች በአህጉሪቱ ለሚታየዉ ልማት ያላቸዉን አስተዋፅኦ በማወደስ ሴቶችን በንቁ ለማሳተፍ አፍሪቃ በቀጣይ ስልጣን ልትሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የአፍሪቃ ሃገራት በምዕራብ አፍሪቃ የተከሰተዉን ኤቦላ ተኃዋሲን ለመዋጋት ያደረጉትን ጥረት አወድሰዋል። እንድያም ሆኖ በአፍሪቃ እያሻቀበ የመጣዉ ድሕነት፤ ሥራ አጥነትና ግጭቶች አህጉሪቱን ሥጋት ላይ መጣላቸዉ አልቀረም ሲሉ ነዉ የገለፁት። በዚህም ምክንያት በሽዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃዉያን ብሩህ ሕይወትን ፍለጋ ወደ አዉሮጳ ለመግባት ሜዲተራንያን ባህር ላይ ያልቃሉ ሲሉ ድላሚኒ ዙማ ተናግረዋል።


«ሕዝባቻችንን በሳይንስ፣ በምሕንድስና ፣ ቴክኖሎጂ እና በሂሳብ ትምህርት፣ እንዲሁም በምርምር ስራ ብናሳትፍ እና ብናሰለጥን ህዝባችን በሳህል በረሃ እና በሜዲተራንያን ባህር አደገኛ ጉዞን ያቆማሉ። »
የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በበኩላቸዉ በሁለቱ ቀናት ጉባኤ መሪዎቹ አህጉሪቱን ለመቀየር በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ ይነጋገራሉ።

« አፍሪቃ በአዲስ የልማትና እድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች፤ ይህ ደግሞ በዓለም የፖለቲካ መድረክ ለመሳትፍ የሚሳችላት አቅጣጫ ነዉ።» ኧል በሽር ላይ የደቡብ አፍሪቃዉ ፍርድ ቤት ያሳለፈዉን ዉሳኔ ተከትሎ የደቡብ አፍሪቃ ገዥ ፓርቲ « ANC» ትናንት እሁድ «ICC» ጥቅም የሌለዉ ተቋም ነዉ ሲል ዉሳኔዉን ማስተባበሉ ይታወቃል። እስካሁን ወደ 20 የሚጠጉ አፍሪቃዉያን ኔዘርላንድስ፣ ዴንሃግ በሚገኘዉ የጦር ወንጀለኞች ተመልካች ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተባቸዉ ሲሆን ፤ ከነዚህ መካከል የቀድሞ ኮት ዲቯር ፕሬዚዳንት ሎር ባግቦን ጨምሮ እስካሁን ሁለት ክሶች ብይን ማግኘታቸዉ ይታወቃል።
የአፍሪቃ ሕብረት መንግሥታትና ርዕሳነ ብሔራት ደቡብ አፍሪቃ ላይ ትናንት የጀመሩት ጉባኤ ዛሬ ምሽት ላይ በይፋ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። በጉባኤ ላይ ከተነሱት በርካታ የመነጋገርያ ነጥቦች መካከል አሸባሪነትን፤ ስደትንና ድህነትን ማጥፋት የተሰኙት ርዕሶች ይገኙበታል።

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic