የኦፌኮ መሪ መረራ ጉዲና ታሰሩ | ኢትዮጵያ | DW | 01.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

 የኦፌኮ መሪ መረራ ጉዲና ታሰሩ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በርካታ አባላቱ እና አራት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱ ከዚሕ በፊት ታስረዉበታል።ዶክተር መረራ አምስተኛዉ መሆናቸዉ ነዉ።አቶ ገብሩ ገብረማርያም  «ትግሉ ይቀጥላል» ባይ ናቸዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:58
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:58 ደቂቃ

ዶክተር መረራ ታሰሩ

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር እና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መድረክ (መድረክ) ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር መረራ ጉዲና ታሰሩ።የሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እንዳስታወቁት ዶክተር መረራ የተያዙት በአዉሮጳ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቅቀዉ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ትናንት ማታ ነዉ።ሮይተርስ ዜና አገልግሎት የኢትዮጵያ ኮማንድ ፖስት የተባለዉን መስሪያ ቤት ጠቅሶ እንደዘገበዉ ዶክተር መራራ የተያዙት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመሪያ በመተላለፋቸዉ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።

ዶክተር መረራ ከመፀሐፎቻቸዉ ባንዱ እንደገለፁት  በ1960ዎቹ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ተለይተዉ አያዉቁም።ያሁኑ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮም እንደ ፖለቲካል

ሳይንቲስት ፖለቲካን በማስተማር፤ ሥለፖለቲካ በማጥናት፤ፖለቲካዊ አስተያየት፤ ትችትና ምክር በመስጠት፤ እንደ ፖለቲከኛ የፖለቲካ ፓርቲ በማደራጀት እና በመምራት ፖለቲካን ርቀዉ አያዉቁም።
                                
ይላሉ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ዓላማ ተጋሪያቸዉ አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም።አቶ ገብሩ ዶክተር መረራ የሚመሩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) እና ባጭሩ መድረክ የተሰኘዉ የፓርቲዎች ጥምረት ምክትል መሪ ናቸዉ።
ዶክተር መረራ በደርግ ዘመን ታስረዉ ነበር።አሁንም እንደገና ታሰሩ።ትናንት ማታ።የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ  እንደሚሉት ዶክተር መረራ መታሰራቸዉ እንጂ የታሰሩበት ምክንያት በግልፅ አይታወቅም።
                           
ዶክተር መረራ የታሰሩበትን ምክንያት ለማወቅ ኮማንድ ፖስት የተሰኘዉ መስሪያ ቤት እና የመንግስት ኮሚኒኬሽን የተባለዉን መስሪያ ቤት ባለሥልጣናት በስልክ ለማነጋገር ሞክረን ነበር።አንዳቸዉ ሌላቸዉን እንድናነጋግር ሲያቀባብሉን አሰልችተዉ ሰዓታችን አለቀ።።ሮይተር ዜና አገልግሎት እንደዘገበዉ ግን ዶክተር መረራ የታሰሩት በአስቸኳይ አዋጁ የተደነገገዉን ደንብ ጥሰዉ የኢትዮጵያ መንግስት «አሸባሪ» ከሚላቸዉ ቡድናት ጋር በመገናኘታቸዉ ነዉ።ዶክተር መረራ ተገናኙዋቸዉ የተባሉት ቡድናትን ማንነት የሮይተርስ ዘገባ አልጠቀሰም።ዶክተር መረራ የተያዙት ብራስልስ-ቤልጂግ ዉስጥ ከአዉሮጳ ሕብረት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዉ እንደተመለሱ ነዉ።«ጧት አዲስ አበባ ገቡ፤ ማታ እስር ቤት።» ይላሉ አቶ ገብሩ
                               
በብራስልሱ ወይይት ላይ የአርበኞች-ግንቦት ሰባት መሪ ዶክተር ብርሐኑ ነጋም ተካፍለዉ ነበር።የአንጋፋዉ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ መታሰር ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ሌላ ዉድቀት ነዉ።ሌለኛዉ አንጋፋ ተቃዋሚ

ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ እንደሚሉት  እርምጃዉ ኢትዮጵያ ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ አሁንም ሩቅ መሆንዋን የሚያረጋግጥ ነዉ።
                 
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በርካታ አባላቱ እና አራት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱ ከዚሕ በፊት ታስረዉበታል።ዶክተር መረራ አምስተኛዉ መሆናቸዉ ነዉ።አቶ ገብሩ ገብረማርያም  «ትግሉ ይቀጥላል» ባይ ናቸዉ።

 

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

                     

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች